ስመ ገናናው የአፍሪካ ኩራት

አረንጓዴ፤ቢጫና ቀይ ዓርማን አንግቦ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ሲንሳፈፍ ግርማ ሞገሱ ያኮራል። ሰማዩን እየሰነጠቀ፤ ደመናውን እየደረመሰ ከአሕጉር አልፎ ዓለማትን ሲያዳርስ የልብ ያደርሳል። በልበ ሙሉነቱና በግርማ ሞገሱም ከሰው ልጅ አልፎ የሰማይ ላይ ከዋክብት ሁሉ ያውቁታል።

ግዙፉና ስመ ገናናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት ነው። አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምቹ፣ ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት በመስጠት በተደጋጋሚ ቁጥር አንድ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተሰኝቷል። ሽልማቶች በየዓመቱ ጎርፈውለታል።

እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ የመሳሰሉ ዕውቅና ሰጪዎችም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹ፣ ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት በመስጠት ለተከታታይ ዓመታት የ1ኛ ደረጃን በመያዝ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መሆኑን አረጋግጠውለታል።

ተደጋጋሚ ሽልማቶች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢንዱስትሪው የአቪዬሽን ኦስካር ተብሎ በሚጠራው የስካይትራክስ መድረክ ለ7ኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሽልማትን አሸንፏል። አየር መንገዱ በተጨማሪም የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል አየር መንገድ ሽልማትን ለስድስት ተከታታይ ዓመታት ማሸነፍ ችሏል ።

እንዲሁም አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ የኢኮኖሚ ክፍል አየር መንገድ ሽልማትን ለስድስት ተከታታይ ዓመት ለማሸነፍ በቅቷል። ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ክፍል ምርጥ ምግብ አገልግሎት ሰጪ አየር መንገድ ሽልማትን አግኝቷል።

ኢኮኖሚያዊ አቅም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠቃላይ በሥራ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች አሁናዊ ዋጋ አምስት ነጥብ ሃያአምስት ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ch-aviation.com ዘግቧል። ይህም በአፍሪካ ካሉት የአውሮፕላኖች ዋጋ 32 በመቶውን የሚሸፍን ነው ተብሏል።

እንደ ch-aviation.com ዘገባ በኢትዮጵያ 119 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ 89 ጠባብ እና ሰፊ አውሮፕላኖች እንዲሁም 30ዎቹ ደግሞ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ በረራ የሚውሉ መለስተኛ አውሮፕላኖች ናቸው።

14 ቦይንግ 737 ማክስ፣ 18 787 ድሪምላይነርስ እና 20 ኤርባስ ኤ350-900 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን አውሮፕላኖች የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ንብረቶች መሆናቸውን ዘገባው ያመላክታል።

የኢትዮጵያ የአውሮፕላኖች የገበያ ዋጋ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ካለችው ግብፅ በ50 በመቶ የሚጠጋ ብልጫ አለው። የአፍሪካ አየር መንገዶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት አዳዲስ እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን አውሮፕላኖች መረከብ የሚጀምሩ ሲሆን ኢትዮጵያም ቀዳሚውን ስፍራ እንደምትይዝ ch-aviation.com. ዘግቧል።

በአውሮፓውያኑ 2025 ወደ 18 ሚሊዮን መንገደኞችን የማጓጓዝም ዕቅድ ያለው ሲሆን በፈረንጆች 2035 ያለውን የበረራ ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ ከዓለም ምርጥ አየር መንገዶች ጋር ለመወዳደር አቅዶ እየሠራ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላንን በማዘዝ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አየር መንገድ ሲሆን፣ አሁን ያለበትን መመንደግ የታየውም በአውሮፓውያኑ 2005 እንደሆነ የአቪዬሽን ተንታኞች ይናገራሉ። ሆኖም በወቅቱ አየር መንገዱ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከግብፅ አየር መንገዶች አንጻር ደረጃው ዝቅ ያለ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2010 የመንገደኞቹን ቁጥር ወደ ሦስት ሚሊዮን የማሳደግ ዕቅድን በመያዝ ማሳካት ብቻ ሳይሆን የያዘውንም ዕቅድም ማለፍ ችሏል። በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በመንገደኞች ብዛት፣ በመዳረሻዎች እንዲሁም በትርፋማነቱ ስኬታማ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ አረጋግጧል። ለዚህም እውቅና እና ሽልማት ከማግኘት በላይ የተሳፋሪዎች ምስክርነት ልዩ ሽልማቱ ነው።

አየር መንገዱ በሌሎች አፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ውስጥም ድርሻዎችን በመግዛት የአህጉሪቷ ቁንጮ የአየር ትራንስፖርት ሰጪ ግዙፍ ተቋም ለመሆን ችሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስተዳደር ሚና ወይም በስትራቴጂክ አጋርነት ስድስት የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን ለማነቃቃት እየሠራ ይገኛል።

በማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ኢንቨስት ከማድረግ በተጨማሪ፣ አስካይ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሞዛምቢክ አየር መንገድ እና የዛምቢያ አየር መንገድ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ትብብርን እየተመለከተ ይገኛል።

የኮቪድ ወቅት ጀግና

ቢቢሲ እንደዘገበው የቦይንግ 737 ማክስ ስምንት አደጋ እንዲሁም የኮሮኖ ቫይረስ ወረርሽኝ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት መጥፎ ጥላን ቢያጠሉበትም ከፍተኛ ትርፍ ከማግኘት ግን አላደናቀፉትም።

ያለፈውን በጀት ዓመት በምናይበት ወቅት 79 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ትርፉ ደግሞ 90 በመቶ እንዲሁም ጭማሪ በማሳየት 937 ሚሊዮን መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ዋቢ አድርጎ ዘ ኢስት አፍሪካን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዋነኝነት ይጠቀሳል። በዚህም ከተጎዱት በአፍሪካ ተወዳዳሪ ከሆኑት የደቡብ አፍሪካና የኬንያ አየር መንገዶች የሚጠቀሱ ናቸው። ወረርሽኙ ያስከተለው ቀውስ ሳይቀረፍ የዩክሬን ጦርነት መነሳቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር እንዲሁም አየር መንገዶቹ በነበራቸው ቀውስ ላይ እንዲንኮታኮቱ ምክንያት ሆኗል።

የኬንያ አየር መንገድን (ኬኪው) ስናይ ባለፈው ዓመት እስከ ሰኔ በነበሩት ስድስት ወራት ብቻ 82 ሚሊዮን ዶላር ከስሯል፤ ከዚያ በፊት በነበረው ስድስት ወር ደግሞ 95 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማሳየቱ ተነግሯል። የኬንያ አየር መንገድ በዚህ ኪሳራ ላይ በዕዳ መዘፈቁም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት እና ለመስፋፋት ባቀደበት ወቅት የኬንያ አየር መንገድ ኪሳራውን ለመቀነስ የያዘው አቅጣጫ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር መቀነስ ነው።

በዚህም አንዳንድ የአውሮፕላኖችን የሊዝ ውል እንደሚያቋርጥም ተገልጿል። በተጨማሪም የሠራተኞችን ቁጥር መቀነስን ጨምሮ ጥገና፣ የነዳጅ እና ሌሎች ወጪዎችንም ለመቆጠብ አቅዷል። በተቃራኒው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በተለይም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ በርካታ አየር መንገዶች ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ሀገራት በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማድረስና የካርጎ አገልግሎትን በመስጠት ለአፍሪካ ሀገራት አለኝታነቱን አሳይቷል። ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስም የማይተካ ሚና ተጫውታል። በዚህ አስተዋፅዖውም ዓለም አቀፍ ሽልማትን ተቀዳጅቷል።

በማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን ጉዳት ያሸነፈበት ጥበብ

እኤአ 2021 የኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የዘገየውን የአደጋውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ጊዜ የኢቲ 302 በረራ አውሮፕላን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተሳሳቱ መረጃዎች ወደ በረራው መቆጣጠሪያ ሥርዓት በመላክ አፍንጫው የመድፈቅ ችግር ስላጋጠመው ከቁጥጥር ውጪ ሆኑ ተከስክሷል።

የአደጋ ምርመራ ሥራው በሚከናወንበት ወቅት በርካታ ጫናዎች እንደነበሩ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የመጨረሻ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት የተጠቀሰ ሲሆን ሁሉንም ተቋቁሞ የሁለቱንም ወገን ጥያቄ የሚመልስ ሥራ ተሠርቷል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገውም አንዳንድ “የጥቅም ግጭት ቢኖርም በዚህ ምርመራ ከቦይንግ ኩባንያ፣ ከአሜሪካው ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ ከብሔራዊ ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ፣ ከፈረንሳዩ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ጋር ተባብሮ መሠራቱንና የመረጃ ልውውጥ መደረጉም ተዘግቧል።

ቦይንግ 737-ማክስ 8 ሊከሰከስ የቻለው በአብራሪው ችሎታ ማነስ ሳይሆን አውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው ኤምካስ የተባለው ዘመናዊ የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ላይ በነበረ ችግር መሆኑን ለማሳመን ችሏል። ቦይንግን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት በመጀመሪያ ይህንን ለመቀበል በርካታ ጫናዎች ቢያደርሱም በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበቂ መረጃዎች ላይ ተንተርሶ ባቀረበው የቴክኒክ ማስረጃዎች ማሸነፍ ችሏል።

በመጨረሻም ቦይንግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ከደረሱ አደጋዎች በኋላ ለባለሃብቶች የአደጋውን መንስኤ በመደበቁ 200 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥቷል።

የተቋሙን ዝና ለማውረድ የሚደረጉ ዘመቻዎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍና ዘመናዊ የአቪየሽን ዘርፍ ነው። በተወዳደረበት መስክ ሁሉ የሚያሸንፍና ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ትልቅ ኩራት ሆኖ እያገለገለ ያለ ተቋም ነው። በዚሁ ስመጥር ዝናው ነገም ይቀጥላል። ሆኖም ከዚህ ግዙፍ አየር መንገድ ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ ያልቻሉና አልፎ ተርፎም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መጉዳት የሚፈልጉ ሀገራትና አካላት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአየር መንገዱን ዝና ለማጠልሸት በርካታ ዘመቻዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ጥቂቶቹን ለማስታወስ ሰኞ ነሐሴ 09 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሱዳን የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች “እንቅልፍ ጥሏቸው” መዳረሻቸውን አልፈው እንደነበር የሚያወሳ ዘገባ ተሰራጭቶ ነበር። በተደረገው ማጣራትም ዘገባው ሐሰት መሆኑ ተደርሶበታል።

ሰሞኑን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል አንዲት ተሳፋሪ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ስትጠየቅ እና ተሳፋሪዋ አልወርድም እያለች ከሠራተኞቹ ጋር የምታደርገውን የተካረረ ክርክር የሚያሳይ ምሰል ተጋርቶ ነበር። ይህንን ጉዳይ በዋነኝነት ታዋቂው ኬንያዊ የሲንኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ ጉዳዩን ከልክ በላይ ሲያጦዘው ተስተውሏል። ይህ ጋዜጠኛ በዚህ ልክ ጉዳዩን ማጦዙ ከጋዜጠኝነት ሙያው ይልቅ ጉዳዩን መወዳደር የተሳነውን የኬንያን አየር መንገድ በአቋራጭ ለመጥቀም የተደረገ ሴራ መሆኑን ልብ ይሏል።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ዝና ጥላሸት ለመቀባት የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀ መልኩ እየተፈበረኩ ነው። ከግለሰቦች አልፎም ሀገራት ጭምር ጥቃቅን ሰበቦችን እየፈለጉ የአየር መንገዱን ዝና የሚያወርዱ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ልምድ እና እውቀት ያለው ተቋም በመሆኑ በወሬ የሚረታ ቁመና የለውም። ስለሆነም እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ይነግሳል። ዛሬም እንደትናንቱ የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ መለያ ሆኖ ይቀጥላል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You