የወደቁትን ያነሳው – «የወደቁትን አንሱ»

ኢትዮጵያ በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ በመረዳዳትና በመደጋጋፍ ፀንተው የቆዩ ፤ ሀገርንም እንዲሁ በአንድነታቸው አፅንተው ያኖሩ ሕዝቦች ያሏት ሀገር ናት፡፡ ይህ የትኛውም ማንነት የማይገድበው የመረዳዳት ባሕል ታዲያ ዘመናት ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ ልክ እንደሌሎቹ እሴቶቿ ሁሉ ለሌሎች ተምሳሌት በመሆን ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር በርካታ የዓለም ሀገራት ጎብኚዎች ይህንን አኩሪ ባሕል ምክንያት አድርገው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑን ይነገራል።

ይህ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየ የመረዳዳት ባሕል ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ስለመምጣቱ ይነሳል፡፡ በዚህ ምክንያትም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉና በቀደመ ዘመናቸው የሀገር ባለውለታ የነበሩ አረጋውያን በድካማቸው ጊዜ የሚደግፋቸው አጥተው አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ የጋሪ ፈረስ አስታዋሽ የሚያጡበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

በዚያው ልክ ደግሞ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ በጎና ቅን አሳቢዎች ይህንን የቀደመ አኩሪ ባሕል ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ማህበርና መሰል መረዳጃ ማዕከላትን በማቋቋም ጧሪ ቀባሪ ያጡ ፤ በችግርና በህመም ውስጥ ያሉ ደካሞችን የመደገፍ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከልም ‹‹የወደቁትን አንሱ›› የነዳያን የበጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት ቅን አሳቢ በሆኑ ኢትዮጵያዊ የተመሰረተ ነው። መስራቹ አቶ ስንታየው አበጀ በሕይወታቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያዩ ፤ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ብዙ አገልግሎት የሰጡ ሆነው ሳለ ድንገት ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው የሚደግፋቸው ያጣሉ፡፡ በብዙ ፈተናዎች አልፈው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ከተመለሱ በኋላ ልክ እንደ እሳቸው ድጋፍ ያጡ ሰዎችን ለመደገፍ በማሰብ ይህንን ማህበር ማቋቋማቸውን የታሪክ ማህደራቸው ያመለክታል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ከ4ሺ500 በላይ አረጋውያንና የወደቁ ህሙማንን አግዟል፡፡ ሕይወታቸው እንዲቀየርም ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ ምንም ጠያቂም ሆነ ዘመድ የሌላቸው ሰዎችን እስከ ሕይወት ፍፃሜያቸው ድረስ መጠለያ፣ ልብስና ምግብ እንዲሁም ሕክምና በመስጠት እያገዟቸው ይገኛል፡፡

ወይዘሮ ዘቢደር ኩራባቸው በማህበሩ ተጠልለው ድጋፍ ከሚያገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ግለሰቧ ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው ጅማ ከተማ ነው፡፡ የሙያ ትምህርታቸውን አጠናቀው በምግብ ሥራ ሙያ በታታሪነት ለጥቂት ጊዜያት ካገለገሉ በኋላ ሙያቸውን የሚያቁ ሰዎች በሙያቸው ውጭ ሄደው ቢሰሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይነግሯቸል፤ በዚህ ይስማሙናም ከሰዎቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ ወደ ውጭ ለመሄድ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ጉዞው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካላቸው ይቀራል፡፡ ይህ ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጣቸውና ወደ ትውልድ ቀያቸው ከመመለስ ይልቅ አዲስ አበባ ይቀራሉ፡፡

ራሳቸውን ለመቻልና ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ዘቢደር እንዳሰቡት የአዲስ አበባ ኑሮ ቀላል አልሆነላቸውም፤ ይባስ ብሎም ጤናቸው ይታወክ ጀመር፡፡ ሆኖም ለህመማቸው እጅ ሳይሰጡ ቀን ከሌሊት ኑሮን ለማሸነፈር ደፋ ቀና ማለታቸውን ቀጠሉ፡፡ ህመሙ ግን ፋታ የሚሰጥ አልነበረምና ባለሰቡትና ባልጠረጠሩት ጊዜና ቦታ ድንገት ጣላቸው። ‹‹ከምኖርበት 70 ደረጃ አካባቢ እየሰራሁ ሳለ ድንገት ጣለኝ፤ ሰዎች አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ፤ እናም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የስኳር ህመም አለብሽ ተባልኩኝ›› ሲሉ ያን ክፉ ገጠመኛቸውን ያስታውሳሉ፡፡

የብርቱዋን ዘቢደር የጤና ሁኔታ አይተውና ማንም የሚያግዛቸው እንደሌለ የተረዱት የቤት አከራይም፤ በነፃ በቤታቸው እንዲኖሩ ፈቀዱላቸው። ግን ደግሞ የስኳር በሽታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱና ሁለቱም ዓይኖቻቸው ማየት በማቆማቸው ምክንያት በወረዳውና በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር በነፃ ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው ሁሉ የሚኑረበት ቤት በልማት ምክንያት ይፈርስና መጠጊያ ያጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሌላ የመንፈስ ጭንቀትና ጫና ፈጠረባቸው፤ የስኳር በሽታውም አደገኛ በሚባል ደረጃ እንዲደርስ ምክንያት ሆነባቸው፤ ድንገትም ራሳቸውን ስተው ወደቁና ለሆስፒታል አልጋ ተዳረጉ፡፡

‹‹እኔ የበርካታ ደጋግ ልብ ያላቸው ኢትዮጵያን ውጤት ነኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ዘቢዳር፣ ከሰፈራቸው ነዋሪዎች ጀምሮ፣ የወረዳውና የከተማው ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ህክምና አግኝተው ወደ ቀድሞ ጤናቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ይገልፃሉ፡፡ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ግን የሚኖሩበት ቤትም ሆነ የሚደግፋቸው ቤተሰብ የሌላቸው በመሆኑ የወደቁትን አንሱ ወደተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት መግባታቸውን ይገልፃሉ፡፡

በድርጅቱ በቆዩባቸው ዓመታትም ልክ የቤተሰብ ያህል ድጋፍና እንክብካቤ እንደተደረገላቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይም በስኳር ህመሙ ምክንያት በሞራ ተጋርደው የነበሩት ዓይኖቻቸው ወደቀድሞ ጤንነታቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ የድርጅቱ ሠራተኞችና የጤና ባለሙያዎች ሚና የጎላ እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ ዘቢደር፣ ‹‹አሁን ላይ ሁለቱም ዓይኖቼ ሙሉ ለሙሉ ማየት ይችላሉ፤ ጤናዬም እየተመለሰ ነው›› ይላሉ፡፡

በማህበሩ ልክ እንደእርሳቸው ሁሉ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ምስኪን ኢትዮጵያውያን ከወደቁበት በማንሳት፤ በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ እምብዛም አለመሥራቱን ይናገራሉ፡፡

‹‹አሁን ካሉት አብዛኞቹ መሰል የበጎ አድራጎት ተቋማት ቀድሞ የተመሰረተ ቢሆንም፣ ብዙ ሰው አያውቀውም፤ እኔ ራሴ እዚሁ አካባቢ ኖሬ ባቅም ማህበሩን እስከምቀላቀል ድረስ አላውቀውም ነበር›› ይላሉ፡፡ የማኅበሩን በጎ ተግባር ደግፈው ከጎኑ የተሰለፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም አሁንም ብዙ ድጋፍ የሚሹ በርካታ የሀገር ባለውለታዎች በየጎዳናውና በእምነት ተቋማት ደጃፍ የሚወድቁበት ሁኔታ በመኖሩ አሁንም የበጎ አድራጊዎች እጆች እንዲዘረጉ ይጠይቃሉ፡፡

ሌላኛው በማዕከሉ ተጠልለው ድጋፍ ከሚያገኙ ሰዎች አንዱ አቶ ካሳሁን ቤዛ ነው፡፡ በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኘው ይህ ግለሰብ ወደ ማዕከሉ የገባው በተወሰኑ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ባጋጠመው የነርቭ ችግር ምክንያት ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ የማይችልና የሚረዳውም አካል ባለመኖሩ ነው፡፡ አቶ ካሳሁን እንደሚለው፤ ለእናቱ ብቸኛ ልጅ እንደመሆኑ ቶሎ ትምህርቱን አጠናቆ እናቱን ለመርዳትና በተማረበት የፋርማሲ ትምህርት ሀገሩን የማገልገል ትልቅ ህልም ነበረው፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዳጠናቀቀ ወዲያውኑ ነበር በቶከስኮሎጂ ትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪውን ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባው፡፡

 

በዘርፉ የላቀ ደረጃ የመድረስና የተቸገሩን የመርዳት እቅድ የነበረው ይህ ጎልማሳ ግን የመጀመሪያ ዓመት የማስተርስ ትምህርቱን አጠናቆ የጥናት ሥራውን ሊጀመር እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ባልጠበቀው ሁኔታ ከፊል የሰውነት ክፍሉ በነርቭ በሽታ ይመታል፡፡ እሱም ሆነ አዛውንት እናቱ ያላቸውን ሀብት ሁሉ አሟጠው ሕክምና ለማግኘት ቢሞክሩም በሽታው ከመዳን ይልቅ እየተባባሰ ይመጣል፡፡

‹‹እናቴ ዘመናዊው ሕክምና አልሆን ሲላት በፀበልም ሞክራ ነበር፤ ግን ደግሞ የፈጣሪ ፈቃድ ባለመሆኑ ልድን አልቻልኩም›› የሚለው አቶ ካሳሁን፤ ወላጅ እናቱ በእድሜም ሆነ በአቅም የተዳከሙ በመሆናቸው እሱን ማንቀሳቀስና መርዳት ከፍተኛ ፈተና ሆነባቸው፡፡ ይህንን የተመለከተው የአካባቢው ማህበረሰብ ተባብሮ ወደ ማዕከሉ እንዲገባ ማድረጋቸውን ይገልጻል፡፡

ለፍተው፣ ጥረው እና ግረው ካስተማሩት በኋላ ተመልሶ እናቱ ላይ ጫና መፍጠሩ ሁሌም ከፍተኛ ጭንቀት ይፈጥርበት እንደነበር የሚያነሳው አቶ ካሳሁን፣ ማዕከሉን ከተቀላቀለ በኋላ ግን ከምግብ ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ የሚያገኝ በመሆኑ በተለይ የማዕከሉ የጤና ባለሙያዎች በቅርበት የጤናውን ሁኔታ የሚከታተሉ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ያስረዳል፡፡

‹‹ይህ ማዕከል እንደ እኔ ረዳት ያጡና በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሕይወት የሚታደግ በመሆኑ ሁሉም እጁን ሊዘረጋና ሊደግፍ ይገባል፤ ደግሞም ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው ዛሬ ላይ ማንም ሰው የቆመ ቢመስለው ነገ ስላለመውደቁ ምንም ዋስትና የሌለው በመሆኑ የነገ ማረፊያው ለሆነው ተቋም የአቅሙን ሁሉ በማድረግ ሊደግፍ ይገባል›› ሲል ያስነዝባል፡፡

ቀሲስ ሳምሶን በቀለ ደግሞ የወደቁትን አንሱ የነዳያን የበጎ አድራጎት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ማህበሩ የተመሰረተው በ1990 ዓ.ም ሲሆን የተመሰረተውም አቶ ስንታየው አበጀ በተባሉ ግለሰብ ነው፡፡ ግለሰቡ በወቅቱ ትልቅ አቅም የነበራቸው ቢሆንም፣ በድንገት ባጋጠማቸው ህመም አልጋ ላይ ቀርተው የሚረዳቸውም ሆነ የሚደግፋቸው አጥተው ሰውነታቸው እስኪቆስል ድረስ ለከፋ የጤና ሁኔታ ተዳርገው ነበር፡፡ በፈጣሪ ርዳታ ከዳኑ በኋላ ‹እኔም ስድን የወደቁትን አነሳለሁ› በማለት ለአምላካቸው ቃል በገቡት መሠረት ማህበሩን መሰረቱት፡፡

 

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ የሚሆኑ አረጋውያንና ህሙማን የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ድጋፍ እያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 200ዎቹ በማዕከሉ ውስጥ በቋሚነት እየኖሩ ከምግብ ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በተመላላሽነት እየመጡ የምግብና የአልባሳት አገልግሎት የሚያገኙ ናቸው፡፡

ከእነዚህ በማዕከላችን ድጋፍ እያገኙ ካሉ ደካሞች መካከል ያገገሙና ራሳቸውን መርዳት የሚችሉ ሰዎች ሲኖሩ ዘመድ ካላቸው የሚገናኙበትን ሁኔታ ተቋሙ እንደሚያመቻችላቸው ቀሲስ ሳምሶን ይናገራሉ፡፡ ሕይወታቸው የሚያልፍ ከሆነም እንደየእምነታቸው ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፤ እንደ ሀገር ባህልና ወግ የክብር ሽኝት ይደረግላቸዋል፡፡ ሲሉም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስረዳሉ፡፡

የማህበሩ ዋናው ደጋፊ በጎ አሳቢ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የማህበሩን አላማ የተገነዘቡ በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉለትም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ልደት፣ ክርስትና ፣ተስካር ፣ሙት ዓመትና ዘካ የመሳሰሉ ዝግጅቶች ያላቸው በማዕከሉ ተገኝተው ከአረጋውያንና ከህመምተኞቹ በጋራ የሚያከብሩበት ሁኔታ መኖሩንም ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለምዶ 41 ኢየሱስ ራስ ካሣ ሰፈር በሚባለው አካባቢ ካለው የማህበሩ ማዕከል በተጨማሪ በእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ ባለው ማዕከላቸው ተኝተው ድጋፍ የሚደረግላቸውና በተመላላሽነት የሚገለገሉ ስለመኖራቸውም ቀሲስ ሳምሶን ይጠቁማሉ፡፡

ያለ ደጋፊ ጎዳና የሚወድቁ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመምጣቱ ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን በመረዳትም ማህበሩ የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ አንድ ሺ 80 ለማድረስ አቅዷል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ከዚያም ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ የሆነ የአረጋውያን ሕክምና እና ክብካቤ መስጫ ሆስፒታል ለመገንባት ማሰቡንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የአዋጭነት ጥናት ለማስጠናት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ የማህበሩ እቅድ ከግቡ እንዲደርስ የመላው ኢትዮጵውያን ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰቡት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ሁሉም ኢትዮጵውያን ከአንድ ብር ጀምሮ ድጋፍ በማድረግ ለእቅዱ መሳካት አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በተጨማሪ የተለያዩ የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመለገስ በተቋሙ የሚረዱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You