ኢትዮጵያ በወርቅ ማዕድኗና ምርቷ ትታወቃለች፤ መታወቅ ብቻም አይደለም ከማዕድኑ በሰፊው ተጠቃሚ እየሆነችም ትገኛለች፡፡ የወርቅ ማዕድኑ በአብዛኛው በባሕላዊ መንገድ የሚለማ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው ይነስ እንጂ በኩባንያ ደረጃም የሚለማበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡
ለተለያዩ ጌጣጌጥ መሥሪያነት የሚውሉ እንደ ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ አጌት እና ኳርትዝ የመሳሰሉ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት በብዛት እንዳሏት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በኦፓል ማዕድኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታተወቅ ስትሆን፣ ከአውስትራሊያ ቀጥሎ ለዓለም የኦፓል ማዕድን በማቅረብ ሁለተኛዋ ሀገር መሆኗን መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡ በዓለም የትኛውም አካባቢ የማይገኝ ጥራት ያለው ብርቅዬ ጥቁር ኦፓል የሚገኘው በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑም ይገለጻል፡፡
እነዚህ በከበሩ ማዕድናት ያሏት ሀብቶቿ በደንብ ተለይተው ያልታወቁ፣ ብዙ ያልተሰራባቸው እና ገና ያልተነኩ በመሆናቸው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ኖረዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሀገሪቱ ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማዕድናት በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው በደንብ ተለይቶ ባይታውቅም፣ በባሕላዊ መንገድ እየተመረቱ ጥቅም ላይ እየዋሉም ናቸው፡፡
አሁን ላይ ወርቅና ሌሎች መሰል ማዕድናት በመጠኑም ቢሆን ጥቅም ላይ ከዋሉ ማዕድናት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና ከወርቅ የበለጠ ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉና በሀገሪቱ በብዛት እንደሚገኙ የሚነገራላቸው የከበሩ ማዕድናት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ ማዕድናቱ ግን በባሕላዊ መንገድ እየተመረቱ ለዓለም ገበያ እየቀረቡ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት አሏት። እነዚህ ማዕድናት ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ያሉት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው በመሆኑ ሀገሪቱ ከእነዚህ ማዕድናት በሚገባ ተጠቃሚ እየሆነች አይደለችም፡፡ ከእነ ችግሩም ቢሆን ከእነዚህ የከበሩ ማዕድናት መካከል ለውጭ ገበያ እያቀረበች የምትገኘው የኦፓል ማዕድንን ነው፡፡
የአርኪዎሎጂ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ የሰው ልጅ ‹‹ኦፓል›› ከተሰኘው ማዕድን የመገልገያ መሳሪያ መሥራት የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአራት ሺ ዓመተዓለም አካባቢ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኦፓል ማዕድንም በተለይ ለጌጣጌጥ መሥሪያነት ሲያገለግል ቆይቷል፤ አሁን እያገለገለ ነው።
ኦፓል ምንድን ነው?
ከድረ ገጾች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኦፓል የሚለው ቃል ከላቲኑ ‹ኦፓለስ› የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ውድ ጌጣጌጥ ማለት ነው። በግሪክ ደግሞ ‹ኦፓሎስ› ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን፤ በብርሃን አማካኝነት የሚቀያየር የቀለም ለውጥ የሚሳይ ማለት ነው፡፡
ኦፓል ሚስጥራዊ ውበትን የሚያንጸባርቅ ውብና ልዩ የሆነ ማዕድን ነው፡፡ ከሲልካና ከውሃ የተውጣጣው ኦፓል በሊሞናይት በአሸዋ፣ በድንጋይና በባዝሌት ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡ በዝቅተኛ የሙቀት መጠን የጂኦሎጂካል ሁኔታ ሰፊ ክልል ውስጥ ይመሰረታል፡፡ ኦፓል በሀይቆች ውስጥ ዲያቶም ሲልንድር የሚባል ደለል በመፍጠር ወይም እንደቀርከሃ ባሉ የየብስ ተክሎች ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ይህ የሚሆነውም በአቅራቢያው ባለው የሙቀት ምንጭ ወይም በሃይድሮተርማል እንቅስቃሴ ምክንያት ነው፡፡
ኦፓል ውሃ አዘል የሲሊካ ማዕድን ነው፡፡ ከሶስት እስከ 21በመቶ ያለው ውሃ ውህድ መጠን በሲሊካ ቁስ ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ከስድስት እስከ 11በመቶ ድረስ ውሃ ያዘለ ሲሊካ ለጌጣጌጥነት ማዕድን አገልግሎት ይውላል፡፡ የኦፓል ውስጣዊ አካል (የውሃ ውህድ በመኖሩ) ከተለያየ አቅጣጫ ብርሃን ከገባ በኋላ ተመልሶ እንደሚወጣበት አቅጣጫና በቁሶቹ አሰበጣጠር አማካኝነት ብርሃኖች ተበታትነው ሲወጡ ያማሩና የሰውን ልጅ የሚማርኩ ውበት የሚፈጥሩ ይሆናሉ፡፡
የኦፓል ማዕድን ከፍተኛ ዋጋ እንዲያወጣ ሲባል የተለያዩ ሂደቶችን እንዲያልፍ ይደረጋል፤ በዚህም ይቆረጣል፣ በጥንቃቄ ይፀዳል። ለምሳሌ ‹‹ጠጣር›› ኦፓል በሚገባ የተቆረጠ እና በጥንቃቄ የፀዳ ኦፓል ነው። ጠጣር ኦፓል ለመሥራት የሳሳ እና ለመቆረጥ የማይበቃ ኦፓል ከሆነ ከሌሎች ማዕድናት ጋር ተቀላቅሎ የተለየ የከበረ ማዕድን ሆኖ ይዘጋጃል። ‹‹ድርብ ኦፓል›› የሚባልም አለ፡፡ ይህም ከከበረው የኦፓል ማዕድን ጋር ሲነፃፀር ጠቆር ባለ ነገር የተሸፈነ፣ ወይም አሲድ በመሰለ ነገር ወፈር ያለ ሽፍን ያለው ነው።
ኦፓል እንዴት ይፈጠራል?
ኦፓል ከሲልከንዳይኦክሳይድና ውሃ እንደ ሚፈጠር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ውሃ ወደ ምድር ሲወርድ ከአሸዋና ከድንጋይ ላይ ሲልከንን ያነሳና በስንጥቆችና ባዶ ቦታዎች ያስቀመጠዋል። ከጊዜ በኋላ ውሃው ይተናል፤ የሲልካ ክምችት ይቀራል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ኦፓል ይመሰረታል፡፡
ይህ የምስረታ ሂደት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦፓል ልዩ የቀለም ጨዋታን ያመጣል፡፡ እንደተፈጠረበት አካባቢም የተለያዩ ቀለሞች ይኖሩታል። የኦፓል የውስጠኛው ክፍሉ አፈጣጠር ብርሃንን በውስጡ ሲያልፍ የመጉበጥ ወይም የመጣመም ሁኔታ ይፈጠርበታል። ኦፓል የሚፈጠረውም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው፡፡
የኦፓል ማዕድን ነጭ፣ ግራጫ፣ ቀይ፣ ብርቱካናማ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ቀይ ቡኒ፣ ሮዝ፣ ሀምራዊ፣ ደማቅ አረንጓዴ፣ ቡና ዓይነት እና ጥቁር መልክ ይዞ ሊገኝ ይችላል። ከነዚህ ውስጥ ጥቁር ኦፓል እንደልብ አይገኝም፤ ነጭ እና አረንጓዴ ኦፓሎች ግን ለማግኘት እምብዛም የሚከብዱ አይደሉም፡፡ ኦፓል ጨርሶ ብርሃን የማያሳልፍ፣ ከፊል ብርሃን አስተላላፊ እና ነጭ ጉም የመሰለ ሽፋን ያለው በሚል በተለያዩ ዓይነቶች ይገኛል፡፡ ለጌጣጌጥነት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኦፓል ዓይነቶች
ጥቁር ኦፓል፣ የእሳት ቀለም ያለው ኦፓል፣ የወሎ ኦፓልና ቀስተ ደመና ፣ ቀይ ኦፓል ፣ ነጭ ኦፓል እና የውሃ ቀለም ያላቸው የኦፓል ዓይነቶች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ጥራት ያለው ጥቁር ኦፓል /Exclusive Quality Rare Black Fire Ethiopian Opal/ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የኦፓል ዓይነት ነው። በሀገሪቱ ለየት ያለ ጥራት ያለው ኦፓል ለመገኘቱ የመሬት አቅማመጥ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሀገሪቱ ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት ዓይነቶች መኖራቸው ይታወቅ እንጂ ያለው ማዕድን ክምችት መጠን በውል ባይታወቅም መጠኑ ከፍተኛ እና ሊሸፍነው የሚችለው ቦታ ሰፊ እንደሆነ ይገመታል። ክምችቱን ለማወቅም ሆነ የታወቁትን በአግባብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ላይ ገና ብዙ አልተሰራም፡፡
በኦፓል የሚታወቁ ሀገሮች
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከዓለም የኦፓል ማዕድን አብዛኛው የሚገኝባቸው ሀገሮች ኢትዮጵያና አውስትራሊያ ናቸው፡፡ አውስትራሊያ ኦፓል ለዓለም ገበያ በማቅረብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ የሀገሪቱ ኦፓል ምርት በውድ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ የኢትዮጵያ ኦፓል የሚያምርና በጥራቱ ከአውስትራሊያው ኦፓል የሚበልጥ ቢሆንም፣ በአነስተኛ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በማዕድኑ ላይ ብዙም ካለመሰራቱ ጋር በተያያዘ በዓለም ገበያ ላይ ብልጫውን ይዞ ተጽዕኖ መፍጠር አልቻለም፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ዘርፉ እያንሰራራና ለውጦች እያመጣ ይገኛል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ የኦፓል ማዕድንን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በሀገሪቱ የሚገኘው የኦፓል ቀለማት በተለየ መልኩ በየትኛውም የዓለም ሀገር ታይተው የማይታውቁ ዓይነት በመሆናቸው በዓለም ገበያ ተመራጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ይህ በዓለም ገበያ በኦፓል ከምትታወቀው አውስትራሊያ ቀጥሎ የሁለተኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦፓል መገኛ አካባቢ
የኦፓል ማዕድን በአማራ ክልል በወሎ አካባቢ በብዛት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በተለይም ወሎ ደላንታ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሆነ ኦፓል መገኛ ሆናለች፡፡ ኦፓል ብዙ ዓይነት ደረጃ አለው፤ እንደየደረጃው ዋጋው ይለያያል፡፡ ይህንን ማዕድን መፈለግና ማውጣት የተጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ያን ጊዜ የሚገኘው ኦፓል ከ3000 ሜትር ከፍታ ባላቸው ተራሮች ላይ ሆኖ በአብዛኛው ክሪስታል ሆኖ መልኩ ጥቁር ነበር።
የወሎ ኦፓል በቀለሙ ከተለመደው ለየት በማለቱ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ኦፓል የሚቆፈረው ከመሬት ወለል 2500 ሜትር ከፍታ ከእሳተ ጎሞራዊ አሲድነት ካለው አለት ተራራ ላይ ነው። ሁሉም ኦፓሎች የተገኙት በእሳተ ጎሞራ ከሚገኙ ድንጋዮች ሲሆን፤ ጥቁሩ ኦፓል ደግሞ እሳተ ጎሞራ ከሚፈጥረው ጥቁር አቧራ በጊዜ ርዝመት ተለውጠው የሚገኙ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የማምረቱ ሂደት
ይህ ማዕድን እስካሁን ድረስ እየተመረተ ያለው በባሕላዊ አመራርት ዘዴ ሲሆን ከአመራረቱ ጀምሮ ያለው ሂደት በቴክኖሎጂ ያልታገዘና ብዙ የሰው ጉልበት የሚጠይቅ ነው፡፡ ወደ ውጭ ገበያ የሚላከውም ቢሆን እቤት ያልተጨመረበት የሆነው ኦፓል ነው። ይህ ማለት ምንም እሴት ያልተጨመረበት (ፕሮስስ ያልተደረገ) ሲሆን፤ ይህ በዓለም ገበያ ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ካለው ምርት አንጻር አንስተኛ ዋጋ እንዲኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡
በተለይም ምንም እሴት ያልተጨመረበት (ፕሮስስ ያልተደረገ) እንዲሁ መላክ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳሉት የዘርፉ ላይ የተሰማሩ አምራቾች ይናገራሉ። እሴት ተጨምሮበት መላክ ቢቻል ተጨማሪ የሥራ እድል ሊፈጥር የሚችል ነበር፡፡ ማዕድናት ላይ እሴት ለመጨመር ፕሮስስ ለማድረግና የውጭውን ገበያ ፍላጎት ሊያረካ የሚችል የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ማምረት ቢቻል የተሻለ ለውጦች በማምጣት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይታመናል፡፡
ማዕድን የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆኑ መጠን አላቂ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም በአግባብ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ምርትና ግብይት ከሕገ ወጥ ነፃ ተደርጎ በብቃት መምራት ከተቻለ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችልና የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡
የኦፓል ምርት ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ በተለይ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ እንደሀገር ያሉትን ሀብቶች በሚገባ አውቆና አስፋፍቶ እሴት ጨመራ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ብቻ ሳይሆን ተቀዳሚና ተመራጭ የሆኑ ምርቶችን ማቅረብ ያስችላል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ ከሶስት እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደቻለች መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህም ሀገሪቷ ካላት የማዕድን ሀብት ጋር ሲነጻጻር ጥቅም ላይ የዋለው ጥቂቱ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ የተሰማሩና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም