ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን አልምታ ለመጠቀም እየሠራች ያለች ሀገር – ኢትዮጵያ

በገበታ ለሸገርና በገበታ ለሀገር የተሠሩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን ለመጠቀም በቁርጠኝነት እየሠራች ለመሆኗ የሚያሳዩ ተግባራት ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት “በገበታ ለሸገር” ፕሮግራም የአንድነት፣ የወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች ተሠርተው ለአገልግሎት ክፍት ሲሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንንም ጭምር ያስደመመ ተግባር ነበር፡፡

ቀጥሎም “በገበታ ለሀገር” ፕሮግራም የሃላላ ኬላ፣ የጨበራ ጩርጩራ እና የወንጪ ሐይቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሲደረጉም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማስፋት በትጋት እየሠራች ለመሆኗ ሌላው ማሳያ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን አልምታ ለመጠቀም አጠናክራ የቀጠለች መሆኗን ደግማ ደጋግማ አሳይታለች፡፡ ቃል በተግባር ማለትም ይሄው ነው፡፡ ሰባት የቱሪስት መዳረሻዎችንም ለመሥራት በዕቅድ መያዟ ለቱሪስት መስህቦች ትኩረት መስጠቷን አመላካች ነው፡፡ ጢስ አልባውን ኢንዱስትሪ በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማጎልበትም እንዲሁ የፕሮጀክቶቹ እቅድ አንዱ አካል ነው።

“በገበታ ለሸገር” ፕሮግራም የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች በአዲስ አበባ ከተማ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት ሲደረጉ በኢትዮጵያ ተቀዛቅዞ የነበረው የሀገር ውስጥ ቱሪዝምም መነቃቃት ጀምሮ ነበር፡፡ የአንድነት ፓርክ ተሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት በሆነ ሰሞን በ2012 ዓ.ም የተከሰተው ኮቪድ 19 ጋሬጣ ሆነ እንጂ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም ረጃጅም ሰልፎችን ተሰልፈው ሲጎበኙ እንደነበር የምናስታውስ ይመስለኛል፡፡ ይህም በሀገር ውስጥ የነበረውን የቱሪስት እንቅስቃሴ መነቃቃት ጀምሮ እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በ“ገበታ ለሀገር” ፕሮግራምም እንደ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ ሐይቅ እና ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን አልምታ ለመጠቀም እየንቀሳቀሰች መሆኗን የሚያሳዩ ተግባር ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይመስለኝም። እነዚህ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በመልማታቸውም በየአካባቢው የሚገኙ ቅርሶች ጎልተው እና አምረው እንዲታዩ በመደረጉ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ልዩ ውበት ተላብሰው በቴሌቪዥን መስኮት ስናያቸውን ሁላችንንም እጃችንን በአፋችን ላይ ያስጫነ ተግባር ይመስለኛል።

እነዚህ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ለምተውና ተውበው መታየታቸውም ቱሪስቶች ወደየአካባቢው ሄደው እንዲጎበኙ ስለሚያደርግ ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ብዙ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። የአካባቢው ሕዝብም ከተለያዩ አገልግሎቶች በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ መስክ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለአካባቢው ሕዝብ በቀጥታ የሚያገኘውን ጥቅም ለጊዜው እንተወውና ለቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ከሚሰራው መንገድ፣ ንፁሕ ውሃ፣ መብራት ወዘተ ተጠቃሚ ይሆናል ብሎ ማሰብ ይቻላል።

ስለዚህ በፌዴራል መንግሥት የለሙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የአካባቢው ሕዝብና አመራሮች ኃላፊነት ወስደው መንከባከብ አለባቸው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ቱሪስቶች ወደ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎቹ ሄደው ያለምንም ስጋት መጎብኘት እንዲችሉ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የአካባቢው ሕዝብና አመራር በትኩረት መሥራት ይኖርበታል። በሁሉም አካባቢዎች ያለው ሕዝብ ከተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ተጠቃሚ እንዲሆን የፌዴራል መንግሥት በገበታ ለትውልድ ፕሮግራምም ተጨማሪ ሰባት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለመሥራት ዕቅድ መያዙም ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን አልምታ ለመጠቀም በትጋት እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ሌላው ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ሲሰሩ ይዘታቸውን እንዳይለቁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢው ሕዝብም ለዚህ ልማት ተባባሪ መሆንም አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የፌዴራል መንግሥት በማልማቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ምንም አይጠቀምም ማለት ባይቻልም ዋናው ተጠቃሚ ግን የአካባቢው ሕዝብ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህም የመንከባከብ ኃላፊነት የአካባቢው ሕዝብና መንግሥት አመራሮች ትልቅ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ዓይን መሳብ የሚችሉ ውብና ማራኪ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች (ቱሪስቶች) ከሌሎች ሀገሮች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ በተሠሩት ፓርኮች ምክንያት የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች አሁን አሁን ጥቂት መነቃቃት ጀመሩ እንጂ አብዛኛው ሰው የሀገሩን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርስ ሄዶ የመጎብኘት ልምዱ አነስተኛ እንደነበር አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪስት መስህቦች በአግባቡ አልምታ ባለመጠቀሟ በተለምዶ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ከሚባለው የቱሪዝም ዘርፍ የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አልነበረም ማለትም ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ስላልተፈጠረ ነው፡፡ የውጭ ሀገር ዜጎች (ቱሪስቶች) ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲጎበኙና የመጡትም ረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ለቱሪስቶች ሳቢና ማራኪ ነገሮችን ማመቻቸት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ለምሳሌ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን፣ ሎጅዎችን፣ የማይቆራረጥ ቴክኖሎጂን፣ ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች የሚወስዱ ምቹና ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን፣ ንፁሕ የመጠጥ ውሃን፣ መብራትን ወዘተ በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ መሥራት ያለበት የቱሪዝም ሚኒስቴር ነው ቢባልም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መተባበር ይጠበቅባቸዋል። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ካልተባበሩ የቱሪዝም ሚኒስቴር ብቻውን የሚፈጥረው አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡

ምክንያቱም መንገድን፣ መብራትን፣ ንፁሕ ውሃን የሚመለከታቸው አካላት ካልሠሩ፣ ቴክኖሎጂን የሚመለከታቸው አካላት ካላስፋፉ፣ ሆቴሎችንና ሎጅዎችን ባለሀብቶች ካልገነቡ ቱሪዝም ሚኒስቴር ብቻውን ምን ሊያደርግ ይችላል? ስለዚህ “ጥርስና ከናፍር ሲተባበር ያምር” እንዲሉ የተቀዛቀዘው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጨምሮ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ትሩፋቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ከተፈለገ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተባብረው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ትብብሩ ግን እነዚህ አካላት ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎችን ጭምር ማካተት ይጠበቃል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ ካላት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንጻር ሲታይ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች ነበር ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከግብፅ፣ ከኬንያ፣ ከኡጋንዳና ከሌሎች የኢትዮጵያ አጎራባች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር ግን የኢትዮጵያን ያህል የቱሪስት መዳረሻ መስህቦች ሳይኖራቸው የቱሪዝም ፍሰታቸው ከኢትዮጵያ የተሻለ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨመር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኃላፊነት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለሚጎበኟቸው ቦታዎች፣ ለሆቴል ባለቤቶች፣ ለሎጅ ባለቤቶች፣ ለአስጎብኚዎች እና ለመሳሰሉት አካላትን ብቻ ሳይሆን በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ላይ ለተሠማሩ አካላት ጭምር የሥራ እድል ስለሚፈጥር ነው፡፡ ለምሳሌ መኪና ለሚያከራዩ፣ ጫማ ለሚጠርጉ፣ ባሕላዊ ዕቃዎችን አምርተው ለሚሸጡ፣ የጋማ ከብቶችን ለሚያከራዩ ወዘተ ሰዎች ሁሉ የሥራ ዕድል የሥራ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም የተከሰተው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከጎዳቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ ነው፡፡ አበው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሆነና ከኮቪድ በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠረ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጭስ አልባውን ኢንዱስትሪ ውሃ ተቸልሶበት እስካሁንም እንደተቀዛቀዘ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም በፊት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እንኳን ማግኘት ባለመቻሉ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ አካላት አሁንም ድረስ ገቢያቸው ቀንሷል፡፡ ሙሉ በሙሉ ገቢያቸው የተቋረጠባቸው አካላትም ችግር ላይ እንደወደቁ በየጊዜው ሲነገር ይሰማል፡፡

ስለዚህ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቀዛቀዘው የቱሪስቶች ፍሰት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚመለከታቸው አካላት በትብብር መሥራት አለባቸው፡፡ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ብቻ ሳይሆን ከነበረበትም ከፍ እንዲል የቱሪዝም ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት በትኩረት መሥራት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል፡፡ የውጭ ሀገር ዜጎች (ቱሪስቶች) በአንድ አካባቢ ያለውን የቱሪስት መስህብ ሊጎበኙ ሲጓዙ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ስለሚሄዱ ሁሉም የክልል መንግሥታት ኃላፊዎችም ለዘርፉ ትብብርና ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ግንብን፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥትን ወዘተ ሊጎበኙ የሚጓዙ ቱሪስቶች በሚያልፍባቸው አካባቢዎች አርፈው ቁርሳቸውን፣ ምሳቸውንና እራታቸውን በልተው ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ አልጋ ተከራይተውም ያድራሉ፡፡

ባለፉባቸው አካባቢዎች የሆቴሉን የአልጋ ክፍሎች ተከራይተው ያደሩ ቱሪስቶች ቁርሳቸውን፣ ምሳቸውን እና ራታቸውን ከመብላታቸው በተጨማሪ በአነስተኛ የሥራ ዘርፍ ለተሠማሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ስለሚፈጠር ቡና ጠጥተው፣ ጫማ አስጠርገው፤ ባሕላዊ ዕቃዎችን ገዝተው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡ የቆይታ ጊዜያቸው ረዘም ላለ ቀናትም ይሆናል። ቱሪዝም የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጠቀሜታው ብዙ ስለሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራት የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እየተሰሩ ያሉት የቱሪስት መዳረሻዎችም በተገቢው መንገድ መጎብኘትና ገቢ ማመንጨት የሚችሉት በሁሉም መልክ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ነው።

በቀጣይም በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሰባት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ለመሥራት በመታቀዱም በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ተሠርተው ሲጠናቀቁ የተለያዩ ጥቅሞችን ያስገኛሉ፡፡ አንደኛ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ሲሰፉ ብዙ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለሚጎበኙ ከቱሪዝም ዘርፉ ብዙ ገቢ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በሰፉ ቁጥርም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማግኘት በሚያልፉባቸው ቦታዎች ለሚገኙ ሌሎች ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ሦስተኛ በሁሉም አካባቢዎች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ተደራሽ ሲሆኑ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል፡፡

ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫዎች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማስፋት በመላው የሀገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ዜጎችን ሥራ ለመፈለግ ወደ ውጭ ሀገር ማማተር እንዲቀር ያደርጋል፡፡ የሀገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጠረላቸው ማለት ደግሞ ወደ ውጭ በመሄድ የሚደርስባቸውን ከእንግልትና ሞት የሚያስቀረው ስደት ታሪክ ይሆናል፡፡

ቱሪዝም በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ከተስፋፉ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ትልቅ ዕድል ይፈጥርላታል። በገበታ ለሀገር በተጀመረው ፕሮጀክት ሰሞኑን የተመረቀውን የጎርጎራን የኢኮ ሪዞርትን ጨምሮ የሃላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ ሐይቅ ተሠርተው መጠናቀቃቸው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪም ፕሮጀክቶቹ ሲሰሩም የሥራ ዕድል ስለፈጠረ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በዩኒስኮ ለተመዘገቡ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችም ትኩረት በመስጠት ይዞታቸውን ማሻሻል አስፈላጊ ነው።

የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስዋብና ማስፋፋት ብቻውን የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር በቂ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲጎበኙ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራዎችን መሥራትም ያስፈልጋል፡፡ የማስተዋወቅ ሥራዎችን ለመሥራት ደግሞ መጽሔቶችና ብሮሸሮችን(በራሪ ጽሑፎች) አዘጋጅቶ በመላው ዓለም ተደራሽ በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ሰፊ ሽፋን ባላቸው የውጭ ቋንቋዎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብዬም አስባለሁ።

ሀገርን ወክለው በውጭ ሀገር የተመደቡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የቱሪዝም ዘርፉን ማስተዋወቅ ኃላፊነት ስላለባቸው በሀገሪቱ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ ሌት ተቀን በትኩረት መሥራት አለባቸው፡፡ ሁሉም ዜጋ በየአለበትና በየተሰማራባት መስክ ሁሉ የቱሪዝም አምባሳደር መሆን ይጠበቅበታል። የዛሬን አበቃሁ፤

ቸር እንሰንብት!

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሠፈር)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You