ከገበታው መቋደስ ተጀምሯል

የተፈጥሮ ሀብታችን እምቅ ነው፤ ያውም ገና ያልተነካ፡፡ ወዲህ የአየር ንብረቱ የተስተካከለ መሆን፣ ወዲያ ደግሞ ምቹ የሆነ የመሬት አቀማመጥ እንከን የሚወጣለት አይደለም፡፡ በገጸ ምድር ያለውን ውሃ ጨምሮ በከርሰ ምድርም ሆነ ያልተናጠበ የዝናብ ፍሰቱ በኢትዮጵያ ማልማትም ሆነ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት የሚያስችሉ ስለመሆናቸው ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በእጅ ያለ ወርቅ…ሆኖብን እንጂ ማን እንደ ኢትዮጵያ ምድር የሚያሰኝ የተፈጥሮ ሀብታሞች ነን፡፡

ዛሬ ለመግለጽ የወደድኩት ነጥብ በጽሑፌ መግቢያ ላይ ነካ ያደረግኩትን ቱሪዝምን ነው፤ ይሁንና ገለጻዬ በቃሉ ዙሪያ ብያኔና ማብራሪያ ለመስጠት አይደለም፤ ነገር ግን ለቱሪዝም መዳረሻነት ተገንብተው ያለማቋረጥ በተከታታይ ለምረቃ የበቁትን የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች በተመለከተ ጥቂት ጉዳይ ለማለት ያህል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ ሲነሳ ተፈጥሮን በማድነቅም ሆነ በጥሩ ሁኔታ ገንብተው ሌሎች እንዲያደንቁት ከመጓጓት ጋር ተያይዞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን አለመጥቀስ አይቻልም፡፡ እርሳቸው ተፈጥሮን ነጥሎ ማየት የሚችል ሦስተኛ ዓይን ያላቸው ይመስላል። በተንቀሳቀሱበት የሀገራችን ክልል፤ ልዩ የሆነውን የተፈጥሮ መስሕብ ማየታቸውንና ባዩት ነገር ተደምመው ማስረዳታቸውን ብዙ ጊዜ ለማስተዋላችን በርከት ያለ ዋቢ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ውብ የተፈጥሮ ገጽታና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስተዋል አብረው የሚዳሰስ፤ የሚታይና የሚጎበኝ ሀብት ሰጥተውናል፡፡

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው የአዲስ አበባ ከተማን ማራኪና ሳቢ በማድረግ ለቱሪስቶች ስህበት እንዲኖራት በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ2011 መገባደጃ ላይ “ገበታ ለሸገር” በሚል አንድ መርሐግብር ማዘጋጀታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ መርሐግብርም ተወጥኖ የነበረው የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማትና የዚሁ አካል የሆኑትን ፓርኮችና መሰል ሥራዎችን መሥራት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ይህ የ”ገበታ ለሸገር” ውጥን ባማረ ሁኔታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ጉብኚዎች ምስክር ናቸው፤ ገቢ በማስገኘት ደረጃም ላቅ ያለ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ታዲያ፣ በ“ገበታ ለሸገር” የተጀመረው ታላቅ ሥራ ውጤቱ ያመረ መሆኑ ለሌላ ትልልቅ ሥራ በር መክፈት ችሏል፡፡ እሱን ተከትሎ የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች መወጠኑ የሚታወቅ ነው፤ በዚህ መርሐግብር የመጀመሪያው ዙር “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች ውስጥ የተካተቱት ሦስት ቦታዎች ሲሆኑ፣ እነርሱም፤ ጎርጎራ አማራ ክልል፣ ወንጪ ኦሮሚያ ክልል እና ኮይሻ በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ክልል ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዓይናቸው ያዩትን የተፈጥሮ ውበት ልክ በእዝነ ልቦናቸው እንደሳሉት መሬት ማውረድ መፈለጋቸውን በየአጋጣሚው ንግግራቸው መሐል ጣል ሲያደርጉ ስናስተውል ቆይተናል። ሕልማቸውም ያለ መንግሥት በጀት እውን እንዲሆን በመፈለጋቸው በ“ገበታ ለሀገር” ባለሀብቶች የሚሳተፉበት ራት ማዘጋጀታቸው የሚታወስ ነው፡፡

እርሳቸው በነደፏቸው በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተሳታፊዎቹ ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም ዐሻራውን እንዲያሳርፍ የተለያየ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልት መበጀቱ ይታወቃል፡፡ ድር ቢያብር… እንዲሉ በአሁኑ ወቅት በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቶቹ በተባበረ ክንድ እውን መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ ይኸው የ“ገበታ ለሀገር” የአንድ ሰሞን ጥሪ እውን ሆኖ ከገበታው መጉረስም ተጀምሯል፡፡

እርግጥ ነው ይህ ስኬት የመጣው ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ በመሆናቸው አይደለም፡፡ አንዳንዱ አካባቢ ከሠላሙ መታጣት የተነሳ ሥራው እንዳይጓተት አይከፍሉ መስዋዕትነት እየተከፈለ የተሠራ ከመሆኑ በተጨማሪ አንዳንዱ ዘንድ ደግሞ ከካሣ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያጋጥም የነበረን እሰጥ አገባን በጥንቃቄ ማለፍ በመቻሉም ነው፡፡

ስኬታማ ለመሆን የሚከፈል መስዋዕትነት አለ፤ ምክንያቱም ስኬት በምኞት አይመጣም፤ ውጥንም ተስፋ በማድረግ ብቻ ውጤት አይሆንም፡፡ የገንዘብ፣ የጊዜ እና የጉልበት መስዋዕትነትን የግድ የሚል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ተገኝተው ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን በመረቁበት ወቅት ወደ ጎርጎራ 17 ጊዜ መመላለሳቸውን ገልጸዋል። እንዲህ አይነቱ ምልልስ ለጉዳዩ የሰጡትን ትኩረት አመላካች ነው፤ ምክንያቱም ወዲህ የእርሳቸውን መገኘት የሚሹ ጠንከር ያሉ ውይይቶች፤ ወዲያ ደግሞ ይሁንታቸውን የሚፈልጉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ሰቅዘው ይዙዋቸው ባለበት ሁኔታ ውስጥ ያደረጉት ምልልስ ስለመሆኑ አያጠያይቅምና ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ምረቃ ላይ አንድ የተናገሩት ነጥብ፤ “በአሁኑ ወቅት ጎርጎራ ፊደል ሆኖ ማንም ሊሰርዘው የማይችል ታሪክን ጽፏል” የሚል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሀገር በእጆች እንጂ በምላሶች እንደማትሠራም በወቅቱ ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህ አባባል እውነታው የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት አካል የሆነውና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ፣ የ“ገበታ ለሀገር” የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው ጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና የ“ገበታ ለሀገር” አካል የሆነው ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በፍጥነትና በጥራት መሠራታቸው ዋና ምስክር ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)ተመርቀውም በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ያለ ዋጋ መክፈል ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህ ከቱሪዝም መዳረሻነቱ አኳያ ድርሻው ከፍተኛ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ ፋይዳነቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለሌሎች ሀገራት በማስተዋወቁ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ነው። ፕሮጀክቶች በያሉበት አካባቢ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድልም የፈጠሩ መሆናቸው የሚዘነጋ አይሆንም፡፡

ታዲያ ከውጭ ሀገርም ሆነ ከሀገር ውስጥ ወደየፕሮጀክቶቹ የሚጓዙትን ቱሪስቶች በዚያ እንዲሰነብቱ የሚያደርጓቸውን መላ መቀየስ የሀገር ወይም የመንግሥት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የየአካባቢው ማኅበረሰብም ኃላፊነት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ በየመዳረሻዎቹ ቦታ እንዲቆዩ ማድረግ ደግሞ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡

ወደስፍራው የሚመጣውን ጎብኚ መልካም ሥነ ምግባር ማሳየት ወደ አካባቢው ደጋግሞ እንዲመጣ ከማድረጉም በላይ ወደመጣበት ሲመለስ ለብዙዎች መረጃ መስጠቱ በዋዛ የሚታለፍ መሆን የለበትም። በየአካባቢዎቹ የተመረቁት የቱሪስት መዳረሻዎች የአካባቢው ሕዝብ ንብረት እንደመሆናቸው ደግሞ በጥንቃቄ ሊያዙ የግድ ነው፡፡

ከምንም በላይ ሠላም ወሳኙ ነገር እንደመሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ የአከባቢውን ሠላም በማስ ጠበቅ በኩል የላቀ ሚናውን መጫወት ይኖርበታል። ፕሮጀክቶቹ በየጊዜው ገንዘብ የሚያመነጩ እንደመሆናቸው የየአካባቢው ማኅበረሰብ በእኔነት ስሜት ሊይዛቸውና ከሚያስገኙት ገቢ ተጠቃሚ ሊሆንም ይገባዋል፡፡ በጠንካራ የአመራር ብቃት የተዘጋጀውን ገበታ በአብሮነትና በፍቅር መቋደስ ለዘላቂ አንድነት ሚናው የጎላ ነውና ለዚህ የሁሉም ትብብር አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሰላም!

ወጋሶ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You