አንድ ሶስተኛ የዩክሬን ዜጎች ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ላይ በመደራደር ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ

አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወይም 32 በመቶ ዩክሬናውያን ጦርነቱን ለማቆም ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አንዳንድ ግዛቶች ላይ መደራደር አዋጭ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ተነገረ፡፡

የኬቭ ዓለም አቀፍ የማህበረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ግንቦት ወር ላይ ባደረገው ጥናት አንድ ሶስተኛ ዩክሬናውያን ጦርነቱ በፍጥነት ይቆም ዘንድ በድንበር ጉዳዮች ላይ መደራደርን እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የተወሰኑ ግዛቶች ላይ መስማማት አፋጣኝ ሰላም ለማስፈን መሠረት ነው ብለው የሚምኑ ሰዎች መጠን ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረበት በ10 በመቶ ጨምሯል፡፡

የማህበረሰብ ጥናት ተቋሙ ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት ድምጽ የሰጡ ዜጎች በግዛት ጉዳዮች ላይ መግባባትን እንደሚፈልጉ ቁጥራዊ መረጃዎችን ይፋ ከማድረግ ባለፈ፤ የትኛዎቹ አካባቢዎች እንዲሁም በምን አይነት መንገድ ስምምነት ላይ መደረስ እንደሚችል ዝርዝር ጉዳዮችን አላስቀመጠም፡፡

አንዳንድ ዜጎች ጦርነቱ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ አንጻር በመነሳት ሌሎች የግዛት አካባቢዎችን ነጻ ማውጣት በይደር እንዲቆይ ፍላጎት እንዳላቸውም ሮይተርስ ዘግቧል

በአንጻሩ ሩሲያ የዩክሬንን መሬት በሃይል መውረሯ ተገቢ አይደለም ብለው የሚያምኑ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲያበቃ ሩሲያ ሕዝበ ውሳኔ ያደረገችባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን መውጣት አለባት የሚል አመለካከት ያላቸው ዜጎች ቁጥር 55 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ኢንስትቲዩቱ አስታውቋል፡፡

29 ወራትን በተሻገረው ጦርነት እስካሁን ባለው በ2014 በድምጽ ውሳኔ የተጠቃለለችውን ክሪሚያን ጨምሮ ሞስኮ የዩክሬንን 18 በመቶ ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች፡፡

የዩክሬን ጦር ከባላፈው ዓመት ጀምሮ በርካታ ሥፍራዎችን የተቆጣጠረውን የሩሲያ ጦር በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ጥረት ቢያደርግም እምብዛም ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡

በ2022 ሩስያ ዶኔስክ፣ ሉሀንስክ፣ ኬሪሶን እና ዛፖሮዢያ ክልሎችን ወደ ራሷ ማጠቃለሏ ይታወሳል፡፡

ሞስኮ ለኬቭ ባቀረበችው የጦርነት ማቆም ጥሪ ላይ የፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አስተዳደር ለነዚህ ክልሎች የሩስያ አካልነት እውቅና እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡

ኬቭ በበኩሏ ሩሲያ ወደ ቀደመ ስፍራዋ ካልተመለሰች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከሚታወቁ ከዩክሬን ግዛቶች ሙሉ ለሙሉ ካልወጣች የሚደረግ ድርድር እና የጦርነት ማቆም ስምምነት የለም በሚል አቋሟ ጸንታለች፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You