አሜሪካ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ለንግግር ጋበዘች

 

አሜሪካ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ለንግግር መጋበዟን ወጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናገሩ።

አሜሪካ የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በፈረንጆቹ ነሐሴ 14 በስዊዘርላንድ በሚካሄደው እና ራሷ በምትመራው የተኩስ አቁም ንግግር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ በትናንትናው ዕለት ጠዋት “በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሠብዓዊ ርዳታ ለተቸገሩ ሁሉ እንዲደርስ” ለማድረግ በንግግሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ጽኑ አቋማችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን… ተጨማሪ ሰው እንዳይሞት፣ ተኩሱ እንዲቆም እና ሀገሪቱ በሲቪል አስተዳደር እንድትመራ የሚያስችል ሰላማዊ እና በድርድር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በንግግሩ የአፍሪካ ህብረት፣ አረብ ኢምሬትስ እና ተመድ በታዛቢነት እንደሚሳተፉ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። ሳኡዲ አረቢያን ከአሜሪካ ጋር በጋራ በመሆን ንግግሩን እንደምትመራ ብሊንከን አክለው ገልጸዋል።

“በሱዳን የደረሰው የሞት መጠን፣ ስቃይ እና ውድመት አስከፊ ነው። ይህ ትርጉም የለሽ ግጭት መቆም አለበት” ያሉት ብሊንከን የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በንግግሩ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል።

በፈረንጆቹ ሚያዝያ አጋማሽ 2023 የተጀመረው የሱዳን ጦርነት 10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዲፈናቁሉ እና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኗል።

በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በምዕራብ ዳርፉር የብሔር ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ ይቀርብበታል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ይህን ክስ አይቀበሉትም።

አሜሪካ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድሜዳሜ ላይ መድረሷን ማሳወቋ ይታወሳል።

የሱዳኑን ግጭት በሰላማዊ መንገድ የማስቆም፣ አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በጂዳ ሁለቱንም ኃይሎች አገናኝተው የነበረ ቢሆንም ያለውጤት ተቋርጧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You