በኢትዮጵያ የሰፈነው ሠላምና መረጋጋት፣ የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት (በተለይም በመሠረት ልማት ዝርጋታ ዘርፍ) እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና ሰፊ የገበያ እድሎች መኖራቸው ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል። ይህም ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።
የኢንቨስትመንት ዘርፉ በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠሩት የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተደምረው በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል። በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች (የፀጥታ መደፍረስ፣ የኢትዮጵያ ከአጎዋ (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና) ለኢንቨስትመቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረም በኋላ ሠላም በመስፈኑ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው የፀጥታ ችግር እልባት አግኝቷል። የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ስጋትነቱ በመቀነሱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መነቃቃት ማሳየቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ያሏቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለመጨመር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጫና አሳድረው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እያገኙ በመምጣታቸው በዘርፉ መነቃቃት እየታየ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ገልጿል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ በ2016 በጀት ዓመት በብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተስፋ ሰጭ ውጤት እንደተመዘገበ።
እሳቸው እንደሚሉት፣ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ የሀገሪቱን እምቅ ሀብት አሟጥጦ በመጠቀም ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመጨመር፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የሚስችሉ ተግባራትን አከናውኗል። ኮሚሽኑ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን የማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማሳለጥ፣ የድኅረ ኢንቨስትመንት ድጋፍ፣ የኢንቨስትመንት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አመራርና አስተዳደር ተግባራትን ያከናውናል። ኮሚሽኑ በእነዚህ ተግባራት አማካኝነትም የሚያሳካቸው ዋና ዋና ግቦችም የወጪ ንግድንና ተኪ ምርትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የዘርፎችንና የባለሃብቶችን ትስስር እና የክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳደግ ናቸው።
በዚህ ረገድ በበጀት ዓመቱ የኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል ረገድ ሁለት ዐበይት ተግባራት ተከናውነዋል። አንደኛው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁና ወደ ሥራ መግባቱ ነው። አዋጁ አዳዲስ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ተሠማርታ ቆይታለች። በፓርኮቹ ልማት ላይ በተገኙት ውጤቶችና ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ላይ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ከፓርኮቹ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ታቅዶም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ፀድቋል። አዋጁ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን፣ የሎጂስቲክስ እና ከማምረት ውጭ ያሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ የሚያስችል ማዕቀፍ ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላሉ።
ሌላው ዐቢይ ተግባር የጅምላና ችርቻሮን ጨምሮ ለብዙ ዓመታት ዝግ የነበሩ የንግድ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መፈቀዱ ነው። መመሪያው ከወጣ በኋላ ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅቶችን (መመሪያው ወደ ሥራ የሚገባባቸውን ማዕቀፎች ማዘጋጀት፣ ለሠራተኞች ሥልጠና መስጠት…) ሲያደርግ ቆይቷል። ባለሃብቶች ፍላጎቶችን በማሳየታቸው መስፈርቶቹን ማሟላታቸውን በማረጋጋጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል። ይህ መመሪያ ለዋጋ መረጋጋት በጎ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም ከልዩ ኢኮኖሚ አዋጁ መፅደቅ እና ከንግድ ዘርፎች መከፈት ጋር ተያይዞ በ2017 በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ይጠበቃሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታን ለማሻሻል ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመጀመር ያሉ እንቅፋቶች ምንድን ናቸው?›› በሚል መነሻ ጥናቶች ተደርገዋል። ኮሚሽኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚያስተባብረው የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ማሻሻያ አዲስ ማዕቀፍ ውስጥ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል። ማዕቀፉ ቢዝነስ ለመጀመር ያሉትን ችግሮች ለይቶ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ፋይዳ ይኖረዋል።
የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ማጠናቀቅም ሌላው በበጀት ዓመቱ የተከናወነ ተግባር ነው። ሀገራት እነዚህን ስምምነቶች ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ ይጠቀሙባቸዋል። ላለፉት ጥቂት ዓመታት እነዚህ ስምምነቶች ሳይፈረሙ ቆይተዋል። ቀድመው የተፈረሙት ስምምነቶችንም አሁን ካለው ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ባስገባና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መከለስ በማስፈለጉም የክለሳ ሂደቱ ተጠናቆ ከአዳዲስ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ድርድሮች እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህ ሲጠናቀቅ ከአዳዲስ ሀገራት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ቀጣናዊና ክልላዊ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች በመፈጠራቸው ከእነዚህ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ‹ብሪክስ›ን (BRICS) መቀላቀሏን ተከትሎ ከ‹ብሪክስ› አባል ሀገራት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የተጀመሩ ሥራዎችም እንዳሉ ዋና ኮሚሽነሯ ጠቅሰዋል። እነዚህን ሀገራት ታሳቢ ያደረጉ የፕሮሞሽን ሥራዎችም ሲሠሩ መቆየታቸውንም አመልክተው፣ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተጠቃሚ ለመሆን የሚያግዙ ሥራዎችም መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማሻሻል ረገድ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል፣ ከክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽኖች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ከሁሉም ክልሎች ጋር ውይይቶች መካሄዳቸው እና በኢንቨስተሮች ላይ ብዥታ የፈጠሩ አሠራሮች እንዲስተካከሉ መደረጋቸው ተጠቃሽ ተግባራት እንደሆኑ ወይዘሮ ሐና ይናገራሉ። ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመተግበር የመሬት እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ብዙ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የኢንቨስትመንት አቅሞችንና ዕድሎችን በማስተዋወቅ ረገድ ደግሞ፣ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ በ10 ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፏል። በሲንጋፖር፣ በጀርመን፣ በሕንድ፣ በጣሊያን፣ በሩስያ፣ በኔዘርላንድስ እና በቻይና በተካሄዱ የኢንቨስትመንት ፎረሞች ላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅሞችና መልካም እድሎችን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል። የሀገራትንና የዘርፎችን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሁም ዕድሎችንና ማበረታቻዎችን በተመለከተ መረጃ የሚያሰጥ አዲስ የኢንቨስትመንት ጠቋሚ ሰነድም (Investment Guide) ተዘጋጅቷል።
‹‹አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶችን እያየን ነው። ከጃፓን፣ ከሕንድ፣ ከሩስያ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከማልታ፣ ከቱርክና ከፓኪስታን ከመጡ ባለሃብቶች ጋር ውይይቶች ተደርገዋል። የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራ ውጤቱ ወዲያው የሚታይ ባይሆንም ፎረሞቹንና ውይይቶቹን ተከትለው የተገኙ ለውጦች አሉ። ለአብነት ያህል በሚያዝያ ወር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከነበሩ የማልታ ቢዝነስ ልዑካን አራቱ ተመልሰው መጥተው በጥልቀት ዕድሎችን እያዩ ነው። ከባለሃብቶች ጋር ውይይቶችን ካደረግን በኋላ ክትትል እናደርጋለን›› በማለት ይገልፃሉ።
ዋና ኮሚሽነሯ እንዳሉት፣ በ2016 በጀት ዓመት ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል። ይህም የእቅዱን 80 በመቶ ያህል ነው፤ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ11 ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ አለው። ይህ አፈጻጸም ከ2014 ወዲህ የተመዘገበው ትልቁ ውጤት ነው። ላለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና ዘልቃለች። ከአዳዲስ ሀገራት ፍላጎቶች እየታዩ በመሆናቸውን በቀጣይ ጊዜያት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበቱ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ።
በበጀት ዓመቱ 329 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ተሰጥተዋል። ከእነዚህ መካከል 227 የውጭ፣ 40 የሀገር ውስጥ እና 62 ደግሞ በሽርክና (Joint-Venture) የሚሠሩ ባለሃብቶች ናቸው። ፈቃድ ከወሰዱት የውጭ ባለሃብቶች መካከል የቻይና፣ የሕንድና የጅቡቲ ባለሃብቶች ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል።
ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት በማምረቻ ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው። በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል። በቤት ግንባታ እና በግብርና ዘርፎችም ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች አሉ። ይህም ከማምረቻው ዘርፍ ውጭ ያሉ ሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው አመላካች ነው።
በሀገሪቱ 13 የመንግሥትና አምስት የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሐና፣ ከሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች 115 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል ሲሉም ጠቅሰዋል። ማሳካት የተቻለው ግን የእቅዱን 46 በመቶ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። ከዚህ ገቢ ውስጥ 80 በመቶው የተገኘው ከቦሌ ለሚ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሆኑም ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ53ሺ590 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ይሁን እንጂ ከዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በለቀቁ ሠራተኞች የተተኩ ናቸው። አዳዲስ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው 2 ሺ 208 ዜጎች ናቸው። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በመንግሥትና በግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ75ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት ፍላጎት ካሳዩ 70 ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል። ከእነዚህም መካከል 44 የሀገር ውስጥ፣ 24 የውጭ እና 2 በሽርክና የሚሠሩ ባለሃብቶች ናቸው። አብዛኞቹ ባለሃብቶች የገቡት ወደ ቦሌ ለሚ እና ‹‹ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ›› ነው።
በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ 205 ፕሮጀክቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ተከናውነዋል። ፕሮጀክቶቹ የተሰጣቸው ማበረታቻ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን እና በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት መሥራታቸውን ለማረጋገጥ በተሠሩ ሥራዎች ክፍተት የተገኘባቸው ድርጅቶች እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም