በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በሠላም እንዲፈታ ከሕዝብ ተውጣጥቶ የተቋቋመው የሠላም ካውንስል በጋራ ተሸናፊ ከሚያደርገው የእርስ በርስ ጦርነት በመውጣት ወደ የጋራ አሸናፊነት ሊያመጣ የሚችለውን ንግግር መንግሥትና በትጥቅ ትግል ላይ ያለው ቡድን ሊተገብሩት ይገባል በማለት ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ይህን ጥሪ ያቀረበው ካውንስል ከመቋቋሙ በፊት ከሰኔ 12 እስከ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባን ጨምሮ በስምንት መድረኮች ችግሩን በትክክል አንስተው የመፍትሔ ሀሳብ ያመጣሉ የተባሉ ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውይይት አድርገዋል። ከዚያም በስምንቱ መድረክ በተሳታፊዎች ከተመረጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሀገሪቱ የጦር ጄኔራሎችና መኮንኖች እንዲሁም የሲቪል አመራሮች ጋር ምክክር ተደርጓል። በማጠቃለያውም አሸናፊ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ስለሆነ በንግግርና በውይይት እንዲሁም በድርድር ይፈታ የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።
የድምዳሜው መፍትሔ ሀሳብ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ይዤ ነው የምዋጋው ከሚለው ኃይል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ንግግርና ድርድር እንዲደረግ የሚል ነው። በጉባኤው ማጠቃለያ የአማራ ክልል መንግሥት ይህ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት በንግግርና በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛ ነኝ ነገር ግን ፋኖ አደረጃጀቱና መሪው ብዙ ነው በማለቱ ተደራዳሪዎች ተለይተው እንዲቀርቡ ሁለቱን ወገኖች እያነጋገረ ለንግግርና ለድርድር ጥረት የሚያደርግ 15 አባላት ያሉት አመቻች የሠላም ካውንስል ተመርጧል።
የተመረጠውም የሠላም ካውንስል የሠላም ጥሪ አቅርቧል። የሠላም ካውንስሉ ጥሪ ሲያቀርብ ከገለጻቸው ሀሳቦች ውስጥ ልቤን የነካው ‹‹ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው መፍትሔ የማያመጣ የእርስበርስ ጦርነት ማድረጋችን ሳይሆን፤ ከመገዳደል ወጥተን ፖለቲካዊ ልዩነታችን በውይይት፣ በመነጋገር፣ በመደራደርና በሰጥቶ መቀበል በሚፈታ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ስንገባና ባሕል ስናደርግ ያኔ ነው ለኢትዮጵያ ሰበር ዜና መባል ያለበት። ስለሆነም የወገናችሁ ስቃይ ተረድታችሁ መሸናነፍ በማትችሉበት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደምትችሉበት ንግግርና ድርድር እንድትገቡ አመቻች የሠላም ካውንስሉ አበክሮ ይጠይቃል፤ ለማግባባትም ይጥራል። ›› የሚለው አንዱ ነው።
ስለሆነም ሁለቱም ኃይሎች ለዚህ ሠላማዊ ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠታቸው የመሸነፍ ስሜት ውስጥ መግባታቸውን የሚያመላክት ሳይሆን፣ አገለግለዋለሁ ወይም እታገልለታለሁ ለሚሉት ሕዝብ አበክሮ ማሰብን የሚያሳይ ነው። የሠላም ጥሪውን ተቀብያለሁ ማለት ጅምር ሲሆን፣ በውይይቱ አግባባዊ የሆነ ሰጥቶ የመቀበል መርሕን መከተልንም የሚያካትት መሆኑን ሁለቱ ወገኖች አጥብቀው ሊገነዘቡት ይገባል። ይህን የሰጥቶ መቀበል መርሕን ተግባራዊ ማድረግ ሕዝብን ከተጎጂነት፣ ከመፈናቀል እንዲሁም ከሞት በማዳን እፎይታ መስጠት ማለት ነው።
በሠላም ካውንስሉ ጥሪ ላይ ለፌደራል መንግሥትና ለአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ለፋኖ ወንድሞቻችን በሚል በግልጽ እንደቀረበው የሠላም ሀሳቡን በቅንነት ተረድቶ ቀጥታ በንግግርና በድርድር የእርስበርስ ጦርነቱ በሚያበቃበት መንገድ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ከመንግሥት መታመንን እንዲሁም ከፋኖ ወንድሞች ደግሞ እንታገልለታለን ለሚሉት የሕዝብ አጀንዳ በንግግርና በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆንን በማሳሰብ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ይህን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ‹‹ሠላም ለሁሉም ፤ ሁሉም ለሠላም!›› በሚል መሪ መልዕክት፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በቀበሌና በክፍለ ከተማ ደረጃ ሲከናወኑ የቆዩ የሠላም ኮንፍረንሶች የማጠቃለያ መድረኮች ተካሂደዋል። በጎንደር ከተማ በማጠቃለያ መድረክ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ ግጭቱ ወንድም ወንድሙን የሚገልበት መሆኑን አንስተው የጦርነት መጨረሻው ውይይት ስለሆነ አሸናፊነት በሌለው ግጭት ውስጥ ከመቀጠል የሠላም አማራጮችን መጠቀም አለብን ብለዋል።
እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ማጠቃለያዎች ላይ የተገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች የተፈጠረውን የሠላም አማራጭ በመጠቀም ጥያቄ አለን ብላችሁ የወጣችሁ ወንድሞች ክልሉ ወደ ሠላም እንዲመለስ የራሳችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህን አገላለጽ የሠላም ጥረቱ አንድ አካል አድርጎ መመልከት ይቻላል። ምክንያቱም ከመፈራረጅ ወጥቶ ‹‹ጥያቄ አለን ብላችሁ የወጣችሁ ወንድሞች . . . ›› ብሎ ማለት ለካውንስሉ ጥሪ የተሰጠ ጅምር በጎ ምላሽ አድርጌ አየዋለሁ።
ካውንስሉ ከተመሠረተ በኋላ ባደረገው የሠላም እንቅስቃሴ ጅማሮ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አንዳንድ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያነሱት የገለልተኝነት ጥያቄ በሁሉም አካባቢ የሚገኙ የፋኖ አመራሮችን ለማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የካውንስሉ ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ ለሚዲያ ገልጸዋል። ይህን የሚመሳስሉ ሁኔታዎች ሊከሰቱ የሚችሉ መሆናቸውን በመረዳት ካውንስሉ በተግባሩ ገለልተኛ መሆኑን በማሳየት የተነሳበትን ዋና ዓላማ ከግብ ለማድረስ በእጅጉ ልበ ሰፊ በመሆን ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።
አሥራ አምስት አባላት ያሉት የሠላም ካውንስል በክልሉ ሠላም ለማምጣት ሁለቱ አካላት ድርድሩን እንዲቀበሉ፣ አደራዳሪና ተደራዳሪ እንዲመርጡ፣ ቦታና ጊዜ እንዲወስኑ፣ እንዲሁም የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ማግባባት የተሰጠው ኃላፊነት ነው።
ይህንን ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግም እስከ ቀበሌ ድረስ የካውንስሉን ሀሳብ በማውረድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ ልዩ ስሙ ገርጨጭ በሚባል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተለያዩ ሥራዎች ወደ ባሕር ዳር ደርሰው ሲመለሱ የሠላም ኮሚቴ አባላት ለመሆን ነው በሚል ምክንያት የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና እናቶችን በእንብርክክ በማስኬድ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ቅጣት በመቅጣት የደከመ ሰውነታቸውን ማንገላታታቸው ሳይበቃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሠላም የማይፈልጉ አካላት ገለዋቸዋል።
ኢትዮጵያውያን የሕሊና እረፍት እንዲሰማቸው፣ ፀጥታ እንዲያገኙ፣ ከሽብርና ከሰቀቀን እንዲላቀቁ፣ ከሌላው ሰው ጋር በፍቅር፣ በአንድነት፣ በስምምነት እንዲኖሩ የሚሠራ አካል ናችሁ ብሎ መግደል ከጤነኛ አእምሮ የሚፈልቅ ድርጊት አይደለም። ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ስለሆነው ስለሠላም መሥራት ያሸልማል እንጂ አያስገድልም።
ስለ ሠላም ልትሠሩ ነው፣ የሠላም ኮሚቴ ልትሆኑ ብሎ መግደልም ሆነ አሰቃቂ ቅጣት መቅጣት ጤነኝነት አይደለም። ይህን ድርጊት ሊያደርግ የሚችለው ሠላም ሲሰፍን እጎዳለሁ፣ ጥቅሜ ይቀራል ብሎ የሚያስብ ጤነኛ አስተሳሰብ የሌለው አካል ብቻ ነው።
የሠላም ካውንስሉም ቢሆን ኢትዮጵያ የሠላም አየር እንድትተነፍስ የበኩሉን ድርሻ በመወጣቱ የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍል አደጋም ሆነ አሰቃቂ ድርጊቶች ሊደረጉበት አይገባም። ተወያዩ፣ ተመካከሩ፣ መፍትሔ በጋራ ፈልጉ ብሎ ለሠላም የሚሠራን አካል ሕይወት መቅጠፍም ሆነ ማሰቃየት ተቀባይ የሌለው ተግባር ነው።
ይህን ድርጊት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል። እንዲህ ዓይነት ተግባር የሚፈጽሙ የሕዝብን አጀንዳ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው ቢሉም የሚሰማቸው አካል ሊኖር አይገባም። እነዚህ አካላት ጭካኔ የተሞላው ተግባር የፈጸሙት ሠላም ቢፈጠር የእነሱ ጥቅም በዋነኛነት ስለሚነካ ነው። በእርግጠኝነት ሠላሙ ሲሰፍን እነሱም ይከስማሉ።
የሠላም ካውንስሉ በዚህ ድርጊት ሳይደናገጥ የተነሳበትን ዋና ዓላማ ለማሳካት አሁንም ከፍተኛ ጥረቱን መቀጠል ይገባዋል። የተነሳበትን ዋና ዓላማ ለሚያደናቅፉ ሁኔታዎች ከሕዝብ ጋር በመምከር፣ መፍትሔዎችን በማበጀት ሠላም እንዲሰፍ እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ምክንያቱም ዓላማው ቢሳካ በዋናነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ ነፍሰጡሮች፣ ወዘተ. በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ይህን እኩይ ተግባር ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቡና፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና ወግ ካለው ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም። ድርጊቱን የፈፀመው ሠላምን አጥብቆ የሚጠላ፣ ሀገርንና ሕዝብን የማያከብር አካል የፈፀመው መሆኑን በግልፅ ያሳየ ነው። ስለዚህ መላው ሕዝብ ይህን ፅንፈኛ አካሄድ በጥብቅ መቃወም አለበት። ታጣቂ ቡድኑ እነዚህን ወገኖች በአደባባይ የገደለበት ድርጊት አፀያፊም፣ አሳፋሪም በመሆኑ በአንድ ድምፅ ሊወገዝ ይገባል። ስለሠላም መሥራት ያሸልማል እንጂ አያስገድልም!
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም