ከተረጂነት መላቀቅ ከተናጠል ዜጋ እስከ ሕዝብ ድረስ የሚተመን ጥቅም የሚኖረው የምትታፈር ሀገርን አንግቦ ነው፡፡ ምክንያቱም በተረጂነት ቋጠሮ ውስጥ መኖር አለመኖር የሀገርን የውጭ ግንኙነት አቅም የሚተነብይ ነውና፡፡ በዓለም ኃያላን ሀገራት ርዳታን የውጭ ጉዳይ ማስፈፀሚያ ባደረጉበት በዚህ ጊዜ ደግሞ ከተረጂነት መላቀቅ ለሉዓላዊነት መከበር አብይ ጉዳይ ይሆናል፡፡
የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ምልዑ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል ሀገራቱ የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ሁለንተናዊ አቅም የመገንባታቸው እውነታ ነው፡፡ የኔ የሚሉትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶች የማፅናትና የማስቀጠል ጉልበትን ሲፈጥሩ በተጨባጭ ተግባራዊ በማድረግ ማህበረሰባዊ ማንነታቸውን አጠናክረው መቀጠል ሲችሉ ነው፡፡
ይህንን መሰል ጉልበት ለመገንባት ደግሞ ሀገርን ከጥገኝነት ማላቀቅ የግድ ይላል፡፡ ተረጂነት ከአመለካከት ጀምሮ እስከ ተግባሩ ሌላው ላይ ተጣብቆ መኖር ነው፡፡ ራስን ባዶ የሚያደርግ በሽታም ነው፡፡ ተረጂ የሆነ ሀገር ሀገራዊ ክብሩና ሉዓላዊነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ከተረጂነት የሚተረፍ ነገር የለም፡፡ ምናልባት አፋጣኝ ሕይወትን በማትረፍ ረገድ የሚገኝ ነገር ቢኖረውም በዘላቂነት በተረጂነት ሊተረፍ አይቻልም፡፡
ከዚህ አንፃር መንግሥት ከተረጂነት ወጥተን በራሳችን አቅም ከድህነት እንውጣ የሚለውን መንገድ መከተሉ ተገቢ ነው፡፡ የተያዘው አቅጣጫ ሀገርንም ሆን ሕዝብን የሚጠቅም ነው፡፡ የተረጂነትን ስሜት በመቀልበስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ሀገራዊ ክብርንና ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
አልፎ አልፎ ተረጂነትን ከመረዳዳት ጋር በማመሳሰል መስጠትን እንደ በጎ ማድረግ የሚቆጥሩም አሉ፡፡ መረዳዳት በማህበራዊ ፋይዳዎቻችን ውስጥ ማህበራዊ ተቋማትን የፈጠረ የጋብቻ፣ የዝምድና፣ የዕቁብና የደቦ ሥርዓት ውጤት ነው፡፡ የተበታተነ ሀብትን፣ የተበታተነ ጉልበትን ወደ አንድ አምጥቶ አንድ ሥራ ለመሥራት በራሱ መንገድ የሚፈጥራቸው መዋቅሮች መረዳዳትን ያመጣሉ፡፡ በዚህም ማህበረሰቡ ይተጋገዛል፤ ይረዳዳል፡፡
ይህ ግን ከጥገኝነትና ከተረጂነት ነፃ የሆነ ነው። መረዳዳት እና ተረጂነትን ነጥለን ማየት አለብን። መረዳዳት ማህበራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ሲሆን ተረጂነት ግን ሥነ ልቡናዊ ቀውስ የሚያስከትል፣ በራስ የመተማመን አቅም የሚያሳጣ ነው፡፡ በእውቀት፣ በመልካም ሃሳብ፣ በገንዘብ መረዳዳትና መደጋገፍ የሰው ልጅ በአወንታዊ እሳቤ የሚከውነው እውነት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በአሉታዊ አመለካከት ምክንያት በብዙዎች ዘንድ የሚስተዋለው የጠባቂነት አመለካከት እንደ ሀገር ሊወገድ የሚገባው ነው፡፡
ይህ የጠባቂነት አስተሳሰብ ሁልጊዜ እርዱኝ የሚል እሳቤን ይዞ ይመጣል፡፡ “እኔ ምንም አልተሰጠኝም፣ እኔ ምንም ማድረግ አልችልም በሚል ከጥገኝነት መውጣት አዳጋች እንዲሆን ሲያደርግም እንመለከታለን፡፡ የተሰጠንን ነገር ባለማወቅም የሌሎች ሰዎች ሀብት፣ እውቀት፣ ቁሳቁስ በማየት እንድንረዳ፣ እንዲደረግልን አጥብቀን እንሻለን፡፡ ይህ እሳቤ እያደገ ሄዶ ሰርተን ከመለወጥ ይልቅ የጠባቂነት መንፈስ በውስጣችን እንዲያድግም ያደርጋል፡፡
ይህንን አመለካከት የማናጠፋው ከሆነ ደግሞ ስር የሰደደ ሥነ ልቡናዊ ቀውስ ይዞብን እንደሚመጣ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የተረጂነት አስተሳሰብ ግለሰብን፣ ቤተሰብን፤ ማህበረሰብን የሚመጣውን ትውልድ የሚጎዳና ከወዲሁ የማናስቆመው ከሆነ ዘርፈ ብዙ ሥነ ልቡናዊ ቀውሶችን ያስከትልብናል፡፡
ሰዎች ሌሎችን ጠባቂዎች የሚሆኑበት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች በስንፍና ምክንያት ከሌሎች ርዳታ ሲጠብቁ ሌሎች ደግሞ ከአቅም ማጣት መረዳት ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ማህበረሰብም ቢሆን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ወደ ተረጂነት የሚመጡም አሉ፡፡ ይህን ምክንያት ጠንቅቆ ማወቅ ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣትም ዋና መንገድ ነው፡፡
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አንዳንዶች ተረጂነትን ልማድ አድርገውት ሲኖሩ እንመለከታለን። ከተረጂነት ለመውጣት ምንም ዓይነት ጥረትም አያሳዩም፡፡ በሌላው ላይ ጥገኛ ሆነው በመኖራቸውና በመረዳታቸው የማይፀፀቱ ሰዎች፣ ከተረጂነት ለመውጣት ጥረት የማያደርጉ ሰዎች ለከፋ ሥነ ልቡናዊ ቀውስ ከመዳረጋቸው በፊት ቆም ብለው ሊያስቡ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
የተረጂነት አስተሳሰብ ግለሰብና ማህበረሰብ ላይ የሚቆምም አይደለም፡፡ ከዚህ አልፎ እንደ ሀገር ሲፈታተን እንመለከተዋለን፡፡ ሀገር ከተረጂነት እንዳትወጣ ደግሞ ዘላቂ ትርፍን በማሰብ ርዳታ እና ድጋፍን ጠባቂ እንድትሆን የሚያደርጉ አንዳንድ ተቋማትና ሀገራትም ይኖራሉ፡፡
የተረጂነት አስተሳሰብ ከግለሰብ ጀምሮ በቤተሰብም፣ በሀገርም ደረጃ ያለ ነገር ነው፡፡ አስተሳሰቡ ሰዎች ‹‹መቼም ቢሆን አንሰለጥንም፣ መቼም ቢሆን አሸናፊ አንሆንም፣ መቼም ቢሆን ራሳችንን አንችልም›› እንዲሉና ሁልጊዜ የተገዢነት ስሜት፣ የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ሊያደርግ የሚችል መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ጥናቶችም ተመሳሳይ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡
የተረጂነት አስተሳሰብ በውስጡ የዳበረ ማህበረሰብ መቼም ቢሆን ሰልጥኖ ራሱን አይችልም። በተለይ ደግሞ ምዕራባዊያን እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በአፍሪካና በሌሎች እያደጉ ባሉ ሀገራት ላይ እንዲሰፍን ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ የእነሱ እቃ ማከማቻ፣ ማራገፊያ እንዲሁም ገዢ ሆነው እንዲቀጥሉ በመፈለጋቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አስተዋፅኦ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የቀኝ ግዛት ዘመን ነው፡፡
የቀጥታው የቀኝ ግዛት ዘመን ካበቃ በኋላ የእጅ አዙር የቀኝ አገዛዝ ሰፍኗል፡፡ በተለይ ወቅቱ የኢኮኖሚ አገዛዝ ነውና አፍሪካዊያንና ሌሎችን ጥሬ እቃቸውንና ሌሎች ሀብታቸውን ለመበዝበዝ እንዲመቻቸው የቀየሱት መላ ነው፡፡ በብድርና በሌሎች መሰል ነገሮች በማጥመድ ሀገራት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲገቡና ሁሌም ተረጂ ሆነው እንዲቀሩ ለማድረግ ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡
በርግጥ አፍሪካን ብቻ አይደለም ሌሎች ሀገራትንም መሰል ድርጊት ፈፅመውባቸዋል፡፡ ይህንን ወጥመድ አምልጠው ከድህነት የወጡና ምሳሌ የሆኑ ሀገራትም አሉ፡፡ ከድህነት፣ ከተረጂነት መውጣት ይቻላል የሚለውን ነገር ማስተማሪያ ወይም ምሳሌ የሚሆኑ ሀገራት አሉ፡፡
ለዚህም እንደ ጥሩ ምሳሌ የምትነሳው ቻይና ነች፡፡ ቻይና ከአርባና ሀምሳ ዓመታት በፊት እጅግ ኋላቀርና ድሃ ሕዝብ ነበራት፡፡ የዓለም ቁጥር አንድ ድሃ ያለባት ሀገር ነበረች፡፡ ትልቅ የቆዳ ስፋትና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም እንደነጃፓን ባሉ ትንንሽ ሀገራት ስትገዛ፣ ስትደፈርና ስትወጋ ኖራለች፡፡
እናም ሊቀመንበር ማኦ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቻይና እንድትለወጥ በሩን ከፍተዋል፣ መንገዱን ዘርግተዋል ተብለው ይሞካሻሉ። ላለፉት አርባ ዓመታት ቻይና ተአምራዊ የሚባል እድገትን አሳይታለች፡፡
እኤአ የካቲት 25 ቀን 2021 የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺጂፒንግ ወጥተው አንድ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ በቻይና ከዚህ በኋላ አንድም ድሃ የለም፤ የደሃ ደሃ የሚባለውን ሙሉ በሙሉ ቀልብሰነዋል፣ አጥፍተነዋል ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያሉትን ነገር የዓለም ባንክም፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅትም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም አምነውበታል፡፡
የዓለም ባንክ በሚያስቀምጠው መስፈርት መሠረት አንድ ሰው በቀን ከሁለት ዶላር በታች የሚያገኝ ከሆነ የድሃ ድሃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ቻይና እኤአ 1981 ላይ 878 ሚሊዮን የድሃድሃ ተብለው የሚጠሩ ዜጎች እንደነበሯት የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ከ88 በመቶ በላይ መሆኑን መረጃው ያትታል፡፡ 2015 ላይ ግን ይህ የድሆቿ ቁጥር ወደ ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ወርዷል፡፡ ከዛ በኋላ 2021 ላይ ደግሞ ድህነት የሚባል ከቻይና ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፡፡
ሌላዋ ተምሳሌት የምትሆነው ሀገር ጃፓን ነች። አሰፋ ማመጫ አርጋው የተባሉ ፀሐፊ ‹‹የጃፓን መንገድ ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለም›› በሚለው መጽሐፋቸው ጃፓን እንዴት ከውድቀት ተነስታ አሁን ወዳለችበት የእድገት ደረጃ ላይ እንደደረሰች በስፋት አቅርበዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጦርነት የፈራረሰችውን ጃፓንን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት ትከሻቸው ላይ የወደቀባቸው የጃፓን መሪዎች የጦርነት አስከፊነት በተግባር አይተዋል፡፡ በስልጣኔ ማማ ላይ ደርሳ የነበረችውን ሀገራቸውን በአቶሚክ ቦምብ ወድማ ወደ አመድነት ስትቀየር በዓይናቸው ተመልክተዋል፡፡
እናም እኤአ ከ1945 በኋላ የመጡት መሪዎች የአባቶቻቸውን መንገድ እርግፍ አድርገው በመተው የጦርነት ተሸናፊ የሆነችውን ሀገራቸውን የሰላም አሸናፊ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ በዚህም ተአምራዊ የሚባል ነገር ሰርተው ጃፓንን አመድ ከነበረችበት አውጥተው በዓለማችን ላይ ሁለተኛና ሶስተኛ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት እንድትሆን አድርገዋል፡፡
ይህ የቻይና እና የጃፓን ልምድ ለሌሎች ሀገራትም የሚሰራ ነው፡፡ ይህንን ወደ እኛ ሀገር ብናመጣው የሚቻል አካሄድ ወይም ጥሩ ተምሳሌት ይሆናል። በሀገራችንም ብዙ ምሳሌ የሚሆኑ ጉዳዮችን መጠቃቀስ እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ካለባት ስር የሰደደ የተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነት በሀገረ መንግስቷ በኩል አስታውቃለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የሆኑ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ ልመና ይብቃን በምግብ ራሳችንን መቻል አለብን ብለው በግብርና ዘርፍ አመርቂና ዓለምም የተደነቀበት ሥራ መሥራት ጀምረዋል፡፡
ርግጥ ነው ከተረጂነት ለመውጣት የለውጥ እሳቤ ከተስፋ ውስጥ የሚወለድ በብዙ ውጣ ውረዶች የሚፈተን ስለነገ ዛሬ ላይ በፍቃደኝነትና በቁርጠኝነት ብዙ ዋጋ በመክፈል ዝግጁነትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው፡፡ ስኬታማነቱ የሚሰላውም ይህንኑ መሠረታዊ እውነታ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መታተር ያስፈልጋል፡፡
የተረጂነትን አስተሳሰብም ሆነ ተግባር ማሸነፍ የሚቻለው ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ብቻ ነው። ለዚህም ስኬት በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍም እንደ ኢትዮጵያ ታምርት ያሉ ንቅናቄዎችን በስፋት ማስኬድ፣ በራሳችን ምርት መኖርና በምግብ ራስን የመቻል ተግባራትን በተሻለ መልኩ መተግበር የውዴታ ግዴታ ማድረግ አለብን፡፡
በርግጥ በተሰሩ ሥራዎች ከተረጂነት ስሜት መውጣት እንደምንችል እየተረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የስንዴ ምርትን ማየት ይቻላል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጦችም እየታዩ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ የብዙ ገፊ ምክንያቶች ውጤት ነው፡፡
ፍላጎቶችን አቻችሎና አጣጥሞ በፈተናዎች ውስጥ ያሉ እድሎችን ፈልቅቆ በማውጣት ውስጥ ደግሞ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ሆኖ ይቀመጣል። ስለዚህ በተለወጠ ማንነትና የሥራ ባህል ሀገርን ከተረጂነት ሕዝብንም ከእርጥባን ጠባቂነት ለማላቀቅ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡም ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥቶ ከመንግሥት ጋር በጣምራ መሥራት የግድ ይለዋል፡፡
ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት እሳቤ ለመውጣት ከዘመቻ ባለፈ መውጫ መንገድ (ስልት) መቀየስ ያስፈልጋታል፡፡ የመንግሥት ስትራቴጂዎች ከዘመቻ ያለፉ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው። በጀታችንና ብራችን ሰዎችን ወደ ሥራ በሚያስገቡ ሥራዎች ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውጥኖች ሕዝብ የመከረባቸው፣ በፖለቲካ አዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ዘርፉን ጠንቅቀው በሚያውቁ ምሁራን እና ባለሙያዎች ሃሳብ የተሰጡባቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከተለመደው አካሄድም ወጣ ማለትን ይጠይቃል፡፡
የተለመዱ የተረጂነት አስተሳሰቦች በየትኛውም መመዘኛ የማህበረሰብን ለውጥ መሻት ተጨባጭ ማድረግ አይችሉም፡፡ ስለዚህ እንደ ሀገር ከዚህ ችግር በዘለቄታው ለመውጣት ብዙ ዋጋ የተከፈለበትን ሀገራዊ ክብራችንና ነፃነታችንን አስጠብቀን ለመጓዝ ከተረጂነትና ከተረጂነት አስተሳሰብ ራሳችንን ነፃ ማውጣት ይጠበቅብናል፡፡
ከተረጂነት መውጣት የራስን እድል በራስ መወሰን፣ የሀገርን ቀጣይ የታሪክ ምዕራፍ ብሩህ አድርጎ የመቀለም፣ ብሔራዊ ማንነትን የማፅናት ራዕይ ነው፡፡ ይህ ትልም ወደ ተግባር እንዲቀየር ግን የሁሉንም ዜጋ ቁርጠኝነት ይጠይቃልና እንደ ሀገር ልንተባበር ይገባል፡፡
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም