የአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ሥልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ

የአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት (ሰክሬት ሰርቪስ) ኃላፊ ሥልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ።

የዴሞክራት እና ሪፐብሊካን የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ክምብርሊ ቻትል ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።

አባላቱ ኃላፊዋ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ የጠየቁት የሪፑብሊካኑ ፕሬዚዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ እንዲፈጸም ምክንያት ለሆነው የጸጥታ ክፍተት ተጠያቂ በማድረግ ነው። ነገር ግን ኃላፊዋ ጥሪውን ውድቅ ከማድረጋቸው ባሻገር ተጨማሪ ማብራሪያም ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።

በብዙ ጉዳዮች የተለያየ አቋም በማንጸባረቅ የሚታወቁት የተወካዮች ምክር ቤት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ የሪፐብሊካን ሊቀመንበር ጄምስ ኮመር እና የዴሞክራቱ ከፍተኛ ፖለቲከኛ ጄሚ ራስኪን ቻትል ከሥልጣን ይነሱ የሚል ተመሳሳይ ድምጽ አሰምተዋል።

“ይህ ኮሚቴ የሚታወቀው የተለያየ አቋም በመያዝ ነው፣ ዛሬ ግን ወደ አንድ መጥተናል” ሲሉ ኮመር ለቻትል ነግረዋቸዋል።

ራስኪን በበኩላቸው ቻትል “በሀገራችን ታሪክ የኮንግረሱን እምነት አጥታለች፤ ስለሆነም በፍጥነት ከዚህ በላይ መሄድ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

ቻትል 4፡30 ሰአት በፈጀው የኮንግረስ ቆይታቸው በፈረንጆቹ ሐምሌ 13 የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በ1981 በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሪገን ላይ ከተፈጸመው ሙከራ ጋር በማወዳደር “በአስር ዓመታት ውስጥ ጉልህ የሚባል የጸጥታ ክፍተት ነው”ሲሉ ገልጸውታል።

ነገር ግን ከኃላፊነት እንዲነሱ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፤ “በዚህ ሰአት ሚስጥራዊ የደህንነት አገልግሎቱን ለመምራት የተሻልኩ ሰው ነኝ ብየ አስባለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ቻትል ትራምፕ በፔንስልቬንያ የምርጫ ቅስቀሳው እያደረጉ በነበረበት ወቅት ስለተደረገባቸው የግድያ መከራ ጋር በተያያዘ በተወካዮች ፊት ቀርበው ሲያስረዱ የትናንትናው የመጀመሪያቸው ነው።

ትራምፕ በጆሯቸው ላይ የመቁሰል አደጋ ሲያጋጥማቸው፣ ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ደግሞ አንድ መገደሉ እና ሌላ አንድ መቁሰሉ ይታወሳል።

ግድያውን በማድረስ የተጠረጠረው የ20 ዓመቱ ቶማስ ክሩክስ በጸጥታ አካላት ተገድሏል። ተኩስ የከተፈው ወጣት ዓላማ ምን እንደሆነ አልታወቀም ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You