«በፍራንኮ ቫሉታ ለኢንቨስትመንት ተብሎ የሚገባው ገንዘብ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ትልቅ ተጽእኖ አለው ብለን አናምንም»– ወይዘሮ ሃና አርአያሥላሴ፣ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር

የዓለም ሀገራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በውድድርና በእሽቅድድም ውስጥ ናቸው፡፡ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እና ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዓይነት ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንደመሆኗ፤ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንጻር በ2016 በጀት ዓመት ምን አከናወነች? ስትራቴጂክ እቅዶቿስ ምን ይመስላሉ? እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሃና አርአያሥላሴ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፤

አዲስ ዘመን፡- እንደተቋም በ2016 በጀት ዓመት ከእቅድ አንጻር ምን ምን ተግባራትን አከናወናችሁ?

ወይዘሮ ሃና፡– የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሀገራችን ዋና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ተቋም እንደመሆኑ ባለፉት ዓመታት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታና ከባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን፣ የውጭ ባለሀብቶች የመመልመልና የመሳብ፣ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱባቸውን ፕሮጀክቶች በመከታተል፣ በመደገፍና በማበረታታት እንዲሁም በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የለሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋትና ተገቢውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማከናወን ዋና የኢንቨስትመንት ግቦች የሆኑትን የወጪ ንግድና ተኪ ምርቶችን የማስፋፋት ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡

ከዚህ አኳያም በ2016 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን በማሻሻል ረገድ የልዩ ኢኮኖሚክ ዞን አዋጅ ጸድቆ ወደሥራ ተገብቷል፡፡ ለውጭ ኢንቨስትመንት ተከልለው የቆዩ የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ የንግድ ዘርፎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ክፍት ተደርገዋል። የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታን ለማሻሻል አዲስ ምዕራፍ ተጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ሁለትዮሽ ስምምነት አዲስ ረቂቅ ሰነድ ተጠናቋል፡፡

እነዚህን ማሻሻያዎች ተከትሎ በልዩ ኢኮኖሚክ ዞን ልማትና በውስጡ በሚገቡ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቁጥር እንዲሁም በንግድ ዘርፍ የሚሰማሩ የውጭ ኢንቨስተሮች በቀጣይ ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጡ ይጠበቃል።

በዚህ ዓመት በተደረጉ የፕሮሞሽን ሥራዎችም የሀገራችንን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ኮሚሽኑ 10 ዓለም አቀፍ ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፏል። በሀገር ውስጥም ዘጠኝ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ፎረሞችን አዘጋጅቷል። ከዚህ አንጻር ዋና የትኩረት ሀገራት የነበሩት ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ጃፓን፣ ማልታ፣ ቱርክ፣ ፓኪስታንና ሳውዲ አረቢያ ናቸው። እነዚህን ፎረሞች ተከትሎ ባለሀብቶች ድህረ ጉብኝት በማድረግና በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ በዓመቱ 378 ፕሮጀክቶች የኢንቨስት መንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ ለ329 ፕሮጀክቶች አዲስ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ትልቁን ድርሻ የሚሸፍነው እና 246 ፕሮጀክቶች የሚይዘው የማምረቻ ዘርፉ ሲሆን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኮንስትራክሽን ዘርፎች ቀጣዩን ቦታ ይይዛሉ።

በመንግሥትና በግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመሰማራት ጥያቄ ካቀረቡ ድርጅቶች መካከል ኮሚሽኑ በ2016 በጀት ዓመት ከ70 ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ከእነዚህ መካከል 44 የሀገር ውስጥ ፤ 24 የውጭ ድርጅቶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የጥምርታ ፕሮጀክቶች ናቸው። ኮሚሽኑ የሚሰጣቸው የፍቃድ፣ ዕድሳትና ተያያዥ አገልግሎቶች፣ የማበረታቻና የቪዛ ድጋፍ አገልግሎቶች ሁሉ ከዕቅድ በላይ ተፈጽመዋል። 169 ፕሮጀክቶችም ወደማምረት ተሸጋግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ያከናወናቸው የፕሮሞሽንና የኢንቨስትመንት ድጋፍ አገልግሎቶችን ተከትሎ በ2016 በጀት ዓመት ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ ከዕቅዱ 80 በመቶ ያሳካ ሲሆን፤ ይሄም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የንግድና ልማት ተቋም (UNCTAD) የ2023 ሪፖርት መሠረት በአፍሪካ ከሚገኙ አምስት ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተቀባዮች አንዷ ሆና ቀጥላለች።

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገኘ ኤክስፖርት 115 ነጥብ ሁለት ሚሊየን ዶላር ሲሆን፤ ይሄ ደግሞ ከዕቅዱና ከባለፈው ዓመት የቀነሰ አፈጻጸም ነው። በቀጣይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለአዳዲስ ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች እንዲያቀርቡ በመደገፍ ኤክስፖርት አፈጻጸሙን ለማሳደግ ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- ካለፈው ዓመት አፈጻጸማችሁ በመማር በ2017 በጀት ዓመት ምን አቅዳችሁ ምን ለማሳካት አስባችኋል?

ወይዘሮ ሃና፡– የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት በአምስት ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ለመሥራት ዕቅድ ይዟል። የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን በማሻሻል በ2016 በጀት ዓመት የወጡ አዲስ ሕጎችን ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ የማስገባት፣ የሎጂስቲክስና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻያዎችን ለማድረግ እና የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራን ለማጠናከር አዲስ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ቀርጾ ለመተግበር አቅዷል፡፡

በተጨማሪም የድህረ ኢንቨስትመንት አገልግሎትን ከክልሎች ጋር በተሻለ ቅንጅት ለመሥራት፤ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ሥርዓት ለመተግበር እና የኮሚሽኑን መዋቅር በመከለስና ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ አቅደናል።

ከዚህ ባሻገር በ2017 በጀት ዓመት ሌሎች የኢንቨስትመንት ግቦችን ለማሳካት እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከእነዚህ የኢንቨስትመንት ግቦች መካከል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ወደ አራት ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር ማሳደግ፤ 386 የሚሆኑ አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች መስጠት (341 ከፓርኮች የውጪ፤ 45 ፓርኮች ውስጥ)፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርትን ወደ 153 ሚሊየን ዶላር ማሳደግ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አዲስ ሥራ ፈጠራን ወደ ሁለት ሺህ 352 ማሳደግ፤ የፓርኮች ተኪ ምርቶች አስተዋጽኦን ማሳደግ የሚሉት ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ የዓለም ሀገራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በእጅጉ ፉክክራቸውን እያዘመኑ ይገኛሉ፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምን እያደረገ ይገኛል?

ወይዘሮ ሃና፡- ለእኛ ሀገር ቅድሚያ በምንሰጣቸው ዘርፎች ላይ አቅሙና ብቃቱ ያላቸውን ሀገራት ለመሳብ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፈናል፡፡ በበጀት ዓመቱም 10 ዓለም አቀፍ ፎረሞች ላይ ተሳትፎ አድርገናል፡፡ በሀገር ውስጥ ደግሞ ዘጠኝ ስምምነቶችን ተቀብለናል፡፡

ሁሉም ሀገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥረት ያደርጋል፡፡ ይህን ለማድረግ እንደ ሀገር ያሉንን ሀብቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ኢንቨስትመንት ላይ ለመወዳደር እንደ ሀገር ምን አለኝ? የሚለውን ማወቅ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር በግብርና፤ በማምረቻ ዋና ዋና ዘርፎች (ሴክተሮች) ላይ ኢትዮጵያ ያሏትን ዋና ዋና ነገሮች አስተዋውቀናል፡፡

መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሪፎርሞችን አድርጓል፡፡ በዚህም ለግል ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰቷል፡፡ ከዚያ ውስጥ ደግሞ ለውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የሕግ ማዕቀፍ እና የፖሊሲ ማሻሻያ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይሄንን ለኢንቨስተሮች በማስረዳት በቀጥታ ኢትዮጵያ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሰላምና የጸጥታው ጉዳይ ምን ያህል ኢንቨስትመት ዘርፉ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል?

ወይዘሮ ሃና፡– በባለፉት ዓመታት የኢንቨስትመንት ምህዳሩን በጣም ፈታኝ ካደረጉት ነገሮች መካከል የሰላምና የጸጥታው ጉዳይ አንደኛው ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ስለ ኢንቨስትመንት እድል ማውራት አይቻልም፡፡ በዘንድሮው ዓመት ግን የሰላምና ጸጥታው ሁኔታ በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ በዚህም ሀገር ውስጥ ያሉ ኢንቨስተሮች የሰላምና የጸጥታው ጉዳይ ቶሎ ወደ መስመር ገብቶ ወደ መደበኛው ሥራቸው ለመግባት ትልቅ ተስፋ አሳድረዋል፡፡

ከፀጥታው ጋር በተገናኘ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ያልጀመሩ፤ ማምረት ከሚችሉት በታች እያመረቱ ያሉ፤ ሥራ ላይ ሆነው ምርቶቻቸውንና ሥራቸውን ለማስወጣት እየተቸገሩ ያሉ አሉ፡፡ ይህንንም ለመፍታት ከኦሮሚያና ከአማራ ከክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ጋር ጥቃቅን ጉዳዮችን ሳይቀር በማንሳት ለዚህኛው ኢንቨስተር ይሄ ቢደረግ፤ ለዚህኛው ይሄ ቢደረግ በማለት ተጨባጭ መፍትሔዎችን መስጠት ችለናል፡፡ ለአንዳንዶቹ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ጥበቃ ከለላ እንዲሰጣቸው በማድረግ፤ የፌዴራሉም ሆነ ክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው፤ ስጋት ሲያጋጥማቸውም ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው በማድረግ ብዙ ችግሮችን መፍታት ችለናል።

በአጠቃላይ አሁን ላይ እንደ መንግሥት ለኢንቨስተሮች ማድረግ ያለብንን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም አጠቃላይ በሀገሪቱ ከተጀመሩ የሰላም ግንባታ ጥረቶች የተነሳ በጣም የተሻለ የሰላም ሁኔታ ውስጥ እንገባለን በሚል አሁን ያሉት እንዲቀጥሉ አዳዲሶች ደግሞ እንዲመጡ እየሰራን እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች እስከ መዘጋት ስለመድረሳቸው ይነገራል፤ በእርስዎ ምልከታ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በምን ደረጃ ፈትኖታል?

ወይዘሮ ሃና፡- ከኢንቨስተሮች ጋር ባሉን ውይይቶች ዋና ዋና የኢንቨስትመት ችግሮች መካከል የመጀመሪያው የጸጥታ ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሁላችንም እንደምናውቀው በሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ አውድ ውስጥ አንዱና ትልቁ ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የወጪ ንግዱ (ኤክስፖርት) ከገቢ ንግዱ (ኢምፖርት) ጋር አለመመጣጠኑ ሲሆን፤ ይሄም የንግድ አለመመጣጠንን ስለሚያስከትል የውጭ ምንዛሬ ለረጅም ዓመታት ለሀገራችን ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይሄን ሲባል ግን ምንም ዓይነት የውጭ ምንዛሬ ለድርጅቶች እየተሰጠ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ዘንድ ከችግሩ በጣም የገዘፈ እይታ እንዳለ ይታያል፡፡ የብሔራዊ ባንክ እና ንግድ ባንክ በአንድ ጊዜ ለሁሉም ድርጅቶች ማዳረስ ስለማይችሉ ቅድሚያ ለሚሰጠው ዘርፎች የተሻለ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ካሉን በርካታ ሴክተሮች መካከል የማምረቻ ሴክተሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ከሁሉም በተሻለ እሴት የሚጨምር ዘርፍ ስለሆነ አንድ አምራች ግብዓቱን ለማግኘት በተሻለ ፍጥነት የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኝ ጥረት ይደረጋል፡፡

በነገራችን ላይ እንደ መንግሥት ሴክተር ተኮር የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም አለ። ለምሳሌ፣ ጤና ዘርፉ ላይ ብንመለከት የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን ለማበረታታት ከሁለት ሶስት ዓመት በፊት በተወሰነ ውሳኔ የመንግሥት የመድኃኒት አቅርቦትና ግዥ ኤጀንሲ ከሀገር ውስጥ መድኃኒት ሲገዛ 55በመቶ የሚሆነውን በዶላር እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን በቀላሉ ከውጭ ግብዓቶቻቸውን እንዲያስገቡ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም ለብዙ ዓመታት ቆመው የነበሩና ለመዘጋት ቀርበው የነበሩ የመድኃኒት አምራቾች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት በጣም አበረታች ለውጦች አሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሌላ ድጋፍ የምናደርገው “ፍራንኮ ቫሉታ” የምንለውን ነው። ይሄም ድርጅቶች ከሀገር ውጭ ባላቸው የውጭ ምንዛሬ ወደሀገር ውስጥ ግብዓት እንዲያስገቡ ድጋፍ ማድረግ ማለት ነው፡፡ የመጨረሻውን ፈቃድ የሚያገኙት ከጉምሩክ ቢሆንም በኛ በኩል ግን የጠየቁት እቃዎች የእውነት ለሥራው አስፈላጊ ናቸው የሚለውን ዓይተን ገምግመን ሲታመንበት እንዲፈቀድላቸው ድጋፍ እናደርጋለን፡፡

በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች የዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ ስለሆኑ አብዛኞቹን ግብዓቶቻቸውን በዚህ ሥርዓት ስለሚያስገቡ ጊዜያዊም ቢሆን መፍትሔ አገኝተዋል። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ሥራ ማቆም ላይ የደረሰ ኢንቨስተር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ አሁን ላይ በብሔራዊ ባንክ በኩል የተጀመሩ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ እየተወሰዱ ያሉ ለውጦች (ሪፎርሞች) የምንጠብቀው የውጭ ምንዛሬውን የሚፈታ መፍትሔ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፍራንኮ ቫሉታ ሥርዓት ሰዎች በሕገ ወጥ መልኩ ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊ እንዲያደርጉት መንገድ ይከፍታል ተብሎ እንደስጋት ይነሳል፡፡ እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ችግር እንዳይሆንስ በእናንተ በኩል ምን ዓይነት ጥንቃቄ እየተወሰደ ነው?

ወይዘሮ ሃና፡- አጠቃላይ በሀገር ውስጥ በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ እቃዎች በኢንቨስትመንት ከሚገቡት በቁጥር በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ገንዘብ ሚኒስቴር የፈቀዳቸው በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ መሠረታዊ እቃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ዘይት እና ዱቄትን የመሳሰሉትን በኢንቨስትመንት ከሚገቡት ብናወዳደር በቁጥር በጣም ትንሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

በዚህም ለኢንቨስትመንት ተብሎ በፍራንኮ ቫሉታ የሚገባው ገንዘብ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ትልቅ ተጽእኖ አለው ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም ንጽጽሮሹ ትንሽ ነው፡፡ ችግር እንዳይሆን ለማስቻልም የኢንቨስተሮቹ ከውጭ የሚመጡ ስለሆኑ ገንዘቡን ከእናት ድርጅቶቻቸው ያመጡት መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ይሄም በኢንቨስተሮች በኩል ሊፈጠር የሚችለውን ስጋት ይቀንሳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስተሮችን ከመሳብ ጎን ለጎን በተቋማችሁ ያለውን የደንበኛ አያያዝ ከማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጣችሁን ከማዘመን አኳያ ምን ዓይነት ሥራ ሰርታችኋል?

ወይዘሮ ሃና፡– አገልግሎት አሰጣጣችንን ከማዘመንና ከማቀላጠፍ አኳያ እንደ ተቋም በተቻለ መጠን የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ቶሎ ቶሎ መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለረጅም ጊዜ ውሳኔ ሳያገኙ የቆዩ ጉዳዩችን ውሳኔ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ አሁንም በጉዳዮች ላይ ፈጣን ውሳኔዎችን ለመስጠት ሳምንታዊ የማኔጅመንት ስብሰባዎችን ያለምንም ማቋረጥ እያደረግን ነው፡፡ ኢንቨስተሩ ዴስክ ላይ መጥቶ በተለያየ ምክንያት መስተናገድ ካልቻለ ወዲያው ጉዳዩ ተለይቶ መፍትሔ ማግኘት የሚችልበትን ሥርዓት ዘርግተናል፡፡

ለኢንቨስተሮች በጣም ግልጽ የሆነ እና ወደ ላይኛው አመራር መምጣት የሚችሉበትን እድልም እንሰጣለን፡፡ በዚህም ችግሮች ሲከሰቱ ቶሎ እንፈታለን። ለሠራተኞቻችንም በደንብ ተጠንቅቀው እንዲሰሩ ያስችላቸዋል፡፡ ችግሮች እንዲቀረፉ ከታች ጀምሮ እስከ ላይኛው አመራር ድረስ ሥርዓትን ዘርግተናል፡፡ ሆኖም ግን በጣም ጥሩ አገልግሎት እየሰጠን ነው ማለት አንችልም ፤ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡

ከዚህ አኳያ እንደ ተቋም በ2017 በጀት ዓመት ልንፈታው ይገባል ብለን የያዝነው የዲጂታል አገልግሎት መስጠትን ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ላይ አንድ ኢንቨስተር ጥያቄ አቅርቦ ካልደወለ ወይም ኢሜል ካላደረገ ማወቅ አንችልም፡፡ ስለዚህ በ2017 በጀት ዓመት ቁልፍ የሆኑ አራት አገልግሎታችንን “አውቶሜት” ለማድረግ እቅድ ይዘናል። “አውቶሜት” ማድረጋችንም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ርግጠኛ እንድንሆን ያስችለናል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከውጭ መጥተው ሀገር ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ ለሚገኙ ኢንቨስተሮች ምን ዓይነት ጥበቃ ታደርጋላችሁ? በሰላም እና አለመረጋጋት ንብረቶቻቸው ቢጠፋ ወይም ቢወድም በምን መልኩ ድጋፍ ታደርጉላቸዋላችሁ?

ወይዘሮ ሃና፡- እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ የመንግሥት ምላሽ ምንድነው? የሚለውን የሚመራው ገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡ እንደ መንግሥት ካሳ ክፍያ ውስጥ አይገባም፤ ሆኖም ግን በዓይነት የሚደረጉ ድጋፎች አሉ፡፡

ከዚህ ቀደምም ባጋጠሙ ሀገራዊ ችግሮች የተጎዱ ፕሮጀክቶችን ድጋፍ ለማድረግ የገቢ ግብር እፎይታቸውን ማራዘም፤ አዳዲስ እቃዎችን እንዲገቡ መፍቀድ የመሳሰሉ ድጋፎች ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ምን ዓይነት መፍትሔ እንስጥ በሚለው ላይ ውይይት እያደረግን ነው፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢሆንም በኛ በኩል ምክረ ሃሳቦችን እያቀረብን እንገኛለን፡፡

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ስለሆነ ችግሩ ያጋጠማቸውን ድርጅቶች በሀገሪቱ ውስጥ እምነት ኖሯቸው የማልማት ሥራቸውን ማስቀጠል እንዲችሉ እንደ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረግን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያሏት መሠረተ ልማቶች፤ የፋይናንስ አቅርቦት፤ የሕግ ማዕቀፎች በአጠቃላይ ለኢንቨስትመንት እድገት ግብዓት ናቸው የሚባሉ ጉዳዮች በምን ደረጃ ላይ ናቸው ማለት እንችላለን?

ወይዘሮ ሃና፡- የሕግ ሥርዓቱ በጣም ጥሩ የሚባል ነው።የኢንቨስትመንት ሕጎቻችን እና ፖሊሲዎቻችን ላይ ደግሞ ብዙ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ ለኢንቨስተሮች ግልጽ የሆነና ቀጥተኛ የሆነ የሕግ ሥርዓት ለመዘርጋት ተሞክሯል፡፡ አሁንም የተወሰኑ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እንዴት ነው ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የምችለው? የሚለው በጣም ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ሥራውንም ደግሞ ያቀለለው ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ትግበራ መጀመር ድረስ በአንድ ተቋም (በኮሚሽኑ) በመሰጠቱ ነው፡፡

የፋይናንሱን ጉዳይ ስናይ በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮችን አብዛኞቹ ከውጭ ገንዘብ ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን በሀገር የብድር መጠኑ ውስን ስለሆነ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች የሚሰጥ ነው። የውጭ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ግን የምናየው የፋይናንስ አቅማቸውን እና እቅዳቸውን ነው፡፡

ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት ስንል የኢንቨስትመንት ዋናው አላማ ተጨማሪ ካፒታል ለሀገሪቱ ማስገኘት ስለሆነ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ውስን ብድር በማጣበብ ፋንታ የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው እንዲመጡ ማድረግ አንዱ መስፈርታችን ነው፡፡ በተለይም በቅርብ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ በሀገሪቱ ብድር ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡፡

በርግጥ በሀገር ውስጥ ሲሰሩ በሀገር ውስጥ ባንኮች ነው የሚጠቀሙት፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ሥርዓቱ መከፈት ተጨማሪ የሆኑ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሰጭዎች ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሄ ለኢንቨስትመንት ምህዳሩ መስፋት ትልቅ እንደምታ ይኖረዋል፡፡ የተሻለ አቅርቦትና አገልግሎት ይቀርባል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ ይሄም ወደፊት እየተሻሻለ ይሄዳል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የንግድ ሥርዓቱን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ከማድረግ ጎን ለጎን የቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ ምን ዓይነት ሥራዎች እየሰራችሁ ነው?

ወይዘሮ ሃና፡– የቁጥጥር ሥራ ላይ ሁለት ዓይነት ነገር አለ፡፡ እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፈቃድ ለሰጠናቸው ባለሀብቶች የመቆጣጠር ኃላፊነት አለብን። በ2016 እንደምናደርገው 2017 የፕሮጀክት ቁጥሮችን ፕላን አድርገን ከማበረታቻ አኳያ እና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማምረቻዎች ላይ ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ እንደዚሁም ክልሎችና ከተሞች ቁጥጥር የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሁሉም ፈቃድ ለሰጣቸው ኢንቨስተሮች በሀገሪቷ ሕግና ደንብ መሠረት እየሰሩ መሆናቸውን ቁጥጥር እያደረግን እንገኛለን፡፡ በየዓመቱም የተሻለ ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ኢንዱስትሪል ፓርክ ላይ ያሉት ላይ ብቻ ሳይሆን ከዛ ውጭ ያሉትም ላይ ተመሳሳይ ቁጥጥር ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርብ ጊዜ አዲስ በወጣው የንግድ መመሪያ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ ኢንቨስተሮች በገቢ ንግድ፣ የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ይህ ምን ዓይነት ስጋቶችና እድሎች አሉት? ስጋቶቹንስ ለመቀነስ እንዴት ለመቆጣጠር አቅዳችኋል?

ወይዘሮ ሃና፡- ከዚህ ቀደም የገቢ ንግዱ ለውጭ ባለሀብቶች የተፈቀደ አልነበረም፡፡ የወጪ ንግዱ ላይ ግን ከተወሰኑት ምርቶች ውጭ ክፍት ነበር፡፡ ክፍት የተደረጉት ዘርፎች ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ የተከፈቱ ሳይሆን መመሪያውን ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ መመሪያውም ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፡፡ ሀገራዊ ጥቅምን በሚያረጋግጥ መልኩ የሚከወን ነው፡፡ ይሄንንም ለማረጋገጥ መመሪያው ከጸደቀ ጀምሮ ምዝገባ ተካሂዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ቅድመ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡

በአራቱም ንኡስ ዘርፎች ላይ ያሉት ስጋቶች ምንድናቸው? የቱ ጋር ነው ቁጥጥሩ መጥበቅ ያለበት? የሚለውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጓል። በኮሚሽኑም በኩል መመሪያው ለታለመለት አላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የተለያዩ መመሪያዎችን አዘጋጅተናል፡፡ በዚያ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶች በሙሉ መሟላታቸውን እንዴት ነው የምናረጋግጠው? ምን ዓይነት ሰነድ ነው የምንጠይቀው? የሚለውን አዘጋጅተን ለኢንቨስተሮቹም አሳውቀናል። ቁጥጥሩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለሚያካሂድ እኛ የምንጠነቀቀው ለማን ፈቃዱን እንስጥ የሚለው ላይ ነው፡፡ ፈቃድ የሚሰጣቸው ጥራት ያላቸውና እንደ ሀገር የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን ነው፡፡

የገቢ ንግዱ ፈቃድ ሲሰጥም እንደ ሀገር የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣሉ የሚለውን ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የዋጋ ግሽበትን ከማረጋጋት አንጻር የሚኖራቸው ሚና አንዱ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ክፍት የተደረገው የገቢ ንግድና የጅምላና ችርቻሮ ንግድ መመሪያ እንዲሻርና አዲስ እንዲወጣ የተደረገው ምን ዓይነት ለውጥ ስላላመጣ ነው? መመሪያውስ እንደ መመሪያ ችግር የነበረበት መመሪያ ነው ማለት እንችላለን?

ወይዘሮ ሃና፡- ክልከላው ለዚህ ሁሉ ዓመታት እንዲቀመጥ የተደረገው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከዘርፉ በሚያገኙት ትርፍ ወደ ማምረት ይሸጋገራሉ በሚል ነበር። ንግድ ከማምረት አንጻር ዝቅተኛ ኪሳራና ወጪ ያለው ነው። ትርፉም ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ማምረት ይገባሉ ተብሎ ለ50 ዓመታት ተጠብቋል፤ ነገር ግን ከንግድ የሚገኘው ትርፍ ከፍተኛ ስለሆነ ነጋዴዎች ወደ ማምረት አልገቡም፡፡ ሕጉ ከለላ መስጠቱ ነጋዴዎችን ወደ ማምረት ሊያመጣ አልቻለም፡፡

ለዚህ ሁሉ ዓመታት ከዓለም አቀፍ ውድድር ውጭ ሆነው መቆየታቸው ወደ ማምረት አለማስገባቱ ብቻ ሳይሆን የንግድ ዘርፉ ላይና ተገልጋዩ ላይ ያደረሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ለአቅራቢዎችም የገበያ ሰንሰለቱ ብዙ ችግር ያለበት ነበር፡፡ አሁን ላይ የሚመጡት ባለሀብቶች የተለያዩ ልምዶችን ያካበቱ በመሆናቸው እንደ ሀገር የተሻለ የኢኮኖሚ ትስስር ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ይነገራል። አንዳንዶች እንዲሁም በኢንቨስትመንት ስም የጉልበት ብዝበዛ እየተካሄደ እንዳለ ይናገራሉ፤ እዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድነው?

ወ/ሮ ሃና፡- በየፓርኮቹ ያለው የደመወዝ አከፋፈል የተለያየ ነው፡፡ ብዙዎቹ ፓርኮች ላይ ጥሩ የሚባል ደመወዝ ይከፈላል፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ግን ዝቅተኛ የሚባል ደመወዝ ይከፈላል፡፡ ነገር ግን ከማን ጋር ነው ማነጻጸር ያለብን? አንዳንድ ሪፖርቶች ላይ ቻይና ሀገር ይሄንን ያህል ይከፈላል ኢትዮጵያ ላይ ግን ዝቅተኛ ነው ይባላል፡፡

ማነጻጸር ያለብን ከሀገራዊ አውዱ ጋር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ስናይ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ላይ ከሚሰራው ሠራተኛ ደመወዝ ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው፡፡ በፓርክ ውስጥ ያሉት ግን የስምንተኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከሌሎች አማራጮቻቸው አንጻር የተሻለ ነው፡፡ ከአውዱ ውጭ መመልከት የለብንም፡፡ ሀገሪቱ ላይ ያለው የደመወዝ እስኬል ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በጣም አስከፊ ነው የምንለው አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኢንቨስትመንት መሳብ ባሻገር የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ምን እየሰራችሁ ነው?

ወይዘሮ ሃና፡- እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለዜጎች የሥራ እድልን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሚባል የሥራ እድል መፍጠርን ለማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ የሥራ መብዛት እንዳይኖርና ኢንቨስተሮች በየጊዜው የሠራተኞችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲጨምሩ ግፊት እናደርጋለን።

ዝቅተኛ ደመወዝ ይከፍላሉ የሚባሉ ድርጅቶች ስንመለከት በጣም ብዙ ጥቅማ ጥቅሞችን ለሠራተኞቻቸው ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ የመኖሪያ ቤት እና የትምህርት እድል ለሠራተኞቻቸው ያቀርባሉ፡፡ ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ደግሞ ምግብ ለሠራተኞች ያቀርባሉ፡፡ እነዚህን ታሳቢ ስናደርግ መጥፎ የሚባል ክፍያ እየከፈሉ ነው ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን እንደ ተቋም ጥሩ የሚባል ክፍያ እንዲኖር እናበረታታለን፡፡

እንደ ሀገርም ራሳችንን ስናስተዋውቅ ዝቅተኛ ተከፋይ የሆነ ሰው ኃይል አለ በሚል ሳይሆን የሰለጠነና አቅም ያለው የሰው ኃይል አለን በሚል ነው፡፡ ባለሀብቱ እዚህ መጥቶ በዝቅተኛ ደመወዝ እንዲያሰራ ሳይሆን ጥሩ ክፍያ ከፍሎ ጥሩ ሥራ እንዲሰራ ነው የምንፈልገው፡፡ ከቁጥጥሩ ባሻገር የምናመጣቸው ኢንቨስተሮች ጥሩ ኢንቨስትመንት ያላቸው ከሆኑ ጥሩ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡

በሠራተኛና ክህሎት ሚኒስቴር በኩልም ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ለማስቀመጥ ከረጅም ዓመት በፊት ጀምሮ የቆየ ሂደት አለ፡፡ እሱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ለኢንቨስትመንት ፓርኮች ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ቢቀመጥ ቢያንስ ለኢንቨስተሮች መመሪያ ይሰጣል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን በኛ በኩል ለኢንቨስተሮቹ የሚከፍሉት ደመወዝ ለመኖር በቂ እንዲሆን እንናገራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡

ወይዘሮ ሃና፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You