የናይል ተፋሰስ ሀገሮች የወንዙን አጠቃቀም በሥርዓት ለመምራት እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 22 ቀን 1999 በታንዛኒያ ዳሬሰላም ተሰብስበው የጋራ ሠነድ ወደ ማውጣት ገቡ፡፡ ከብዙ ሂደት በኋላ አሥራ አንድ ዓመታትም አልፈው በዑጋንዳ ኢንቴቤ የሕግ ሠነዱ ተረቅቆ የመጨረሻውን ቅርፅ እንዲይዝ ተደረገ፡፡
ሠነዱ ላይ የመፈረምና ሀገሮቹ ሰነዱን የሀገራቸው/ የተፋሰሱ ሀገሮች/ ሕግ አካል አድርገው እንዲያጸድቁ የሚደረገው ሥራ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ አስራ አራት ዓመታትን አሳልፎ እነሆ በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛዋ የሕግ ማዕቀፉ ፈራሚና አፅዳቂ ሀገር ሆና ወደ ወሳኝ ምእራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በዚህም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ከሃያ አምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ ወንዙን በተመለከተ በቀጣይ የሚገዙበት እና የሚተዳደሩበት ሠነድ እውን ለመሆን በቅቷል ።
እ.ኤ.አ. በ2010 ዑጋንዳ ኢንቴቤ ላይ የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ያዘጋጁት ይህ የናይል ወንዝ አጠቃቀም የትብብር ማዕቀፍ (CFA) ሠነድ በስድስት ሀገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ዑጋንዳ፣ ቡሩንዲና በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ሱዳን ተፈርሞና ፀድቆ የሀገሮቻቸው የሕግ አካል ለመሆን በቅቷል፡፡ ኬንያ የሰነዱ ፈራሚ ብትሆንም፣ አፅድቃ የሀገሯ የሕግ አካል የማድረግ ሂደት ይቀራታል። ግብፅ ፣ሱዳን ፣ ኤርትራና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ በሠነዱ ላይ ያልፈረሙ ሀገሮች ናቸው ።
በአጠቃላይ በትብብር ማዕቀፉ (CFA) ሠነድ አንቀጽ 42 ላይ “ሠነዱ ከተፋሰሱ ሀገሮች ቢያንስ ስድስት ሀገራት የሀገራቸው የሕግ አካል አድርገው ካፀደቁት የዓለም አቀፍ ሕግ አንዱ አካል ሆኖ እንደሚወጣ” ተደንግጓል ። ይህ ድንጋጌ ሠነዱን ዓለም አቀፍ እውቅና የሚኖረው ሠነድ ስለሚያደርገው ሀገሮች ለሕጉ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያስገድድ ከመሆኑም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በተፋሰሱ ውስጥ የነበሩ የሕግ ድንጋጌዎችን ውድቅ በማድረግ ገዢው ሕግ አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፉ (CFA) እንዲሆን የሕግ መሠረት ይሰጠዋል ።
ይህ ሠነድ በሶስት አበይት መርሆች ላይ የተመሠረተ ነው፤ ከእነዚህም አንደኛው ሀገሮች ወንዙን ሲጠቀሙ የውሃውን አካል ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ጥሎባቸዋል፤ ሁለተኛው ውሃውን በፍትሃዊነት መንገድ መከፋፈል እና ትብብርን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ፤ ሶስተኛው ውሃውን የማስተዳደር ሥራንም ይመለከታል፤ ይህም ሥራ በአንድ ማዕከል ሥር በተቀናጀ መልኩ የሚመራ ይሆናል፤ ዘለቄታዊ ጠቀሜታን በሚሰጥ መልኩ የሚከናወን ይሆናል።
በእነዚህ መርሆች መሠረት የሚፈፀም ተግባር ከሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መካከል ደግሞ ወንዙ ከማናቸውም ጉዳት እንዲጠበቅ እና ለመጪው ትውልድ ቁመናው ተጠብቆ እንዲተላለፍ ማስቻል የሚለው ይጠቀሳል፤ በዚህም ላይ ሀገሮች ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ሰነዱ ያስችላል። ሌላው ፋይዳ አሁን በተግባር ላይ ያለውን ኢ ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም በፍትሐዊ አጠቃቀም እንዲተካ ማድረግ ነው፤ ሁሉም ሀገራት የዚህ የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቃሚነታቸው የተጠበቀ ይሆናል።
በዚህ ፍትሐዊ አጠቃቀም ወንዙ የግጭት መንስኤ ከመሆን ወጥቶ ለሀገሮች ግንኙነት መጠናከር አስተዋጽኦ በማበርከት የትብብርና የአንድነት ተምሳሌት መሆን ይችላል፤ ለጋራ ትብብርና እድገትም መንገድ ይከፍታል። በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ፋይዳው ደግሞ ሁሉም ሀገሮች በዘፈቀደ ውሃውን ለመቀራመት ከሚያደርጉት ሩጫ እንዲታቀቡ ማስቻሉ ነው ፤ በዚህም በአንድ ማዕከላዊ አካል ሥር ተደራጅተው በግልጽ በተቀመጠ ዕቅድ መሠረት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ የውሃውን አጠቃቀም በሚቋቋመው ኮሚሽን አመራር ሥር በማድረግ ቅኝ ገዢዎች ትተውት የሄዱት ኢፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀምን በፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መተካት ያስችላል።
በዓለማችን የድንበር ዘለል ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክቶ ካለው ልምድ የትብብር ማዕቀፍ አዘጋጅተው በጋራ የሚንቀሳቀሱ ሀገሮች የወንዙን ፀጋ በትብብር መንፈስ ጥቅም ላይ በማዋል የሀገራቸውን ብልፅግናና የሕዝባቸውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሲያስጠብቁ ማየት ተችሏል። በአንፃሩ በተናጠል የወንዙን ፀጋ ለመቀራመት የሚደረግ ሩጫ በመካከላቸው የተበላሸ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ጥርጣሬና ግጭት ሲያጭር፣ ራሳቸውን ከልማት በማራቅ የሕዝቦቻቸውን ችግርና መከራ በሚያራዝሙ ተግባሮች ላይ እንዲያተኩሩ ሲያደርግ ተስተውሏል ።
የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ከፉክክርና ውድድር ወደ ትብብር ፊታቸውን አዙረው የጋራ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በጋራ መንቀሳቀስ ለመጀመር ብሎም ይህን የትብብር መንፈስ ወደላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግ የናይል ተፋሰስ ሀገሮች አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍ (CFA) መሣሪያ በመሆን የሚሰጠው አገልግሎት ልማትና ብልፅግናን የማመቻቸት ፋይዳው ከፍተኛ ይሆናል።
በአጠቃላይ የደቡብ ሱዳን በትብብር ማዕቀፉ ላይ መፈረም በናይል ተፋሰስ ሀገሮች መካከል ለሚኖረው ግንኙነት አዎንታዊ ሁኔታን የሚፈጥር ቢሆንም፣ ይህን መልካም ዕድል ተጠቅሞ ውጤታማ ለመሆን በርካታ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድን ይጠይቃል።
በተፋሰሱ ውስጥ ተንሰራፍቶ የቆየው የውሃ ላይ የበላይነት /Hydro hegemony/ እንዲህ በቀላሉ የሚሰበር አይሆንም። ሰሞኑን የአጂፕት ቱዴይ /Egypt Today/ ጋዜጣ ” ግብፅ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር በትብብር ፕሮጀክቶችን ቀርፃ ለመሥራት እቅዶች አሏት” በሚል ርዕሰ ሥር ባቀረበው ዘገባ የግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ የተፋሰሱ ሀገሮች በወንዙ ላይ የሚያካሂዱትን ልማት እንደማትቃወም መጥቀሳቸውን አመልክቶ፣ ይህን መሠሉ የልማት እንቅስቃሴ ግብፅ በናይል ወንዝ ያላትን ታሪካዊ የውሃ ድርሻ መብት በማይነካ መልኩ ብቻ የሚፈጸም እንደሚሆን በመግለጽ የድሮውን የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስነብቧል ።
በመሆኑም ኢትዮጵያም በዲፕሎማሲ አቅጣጫዋ ከላይ በተዘረዘሩት የናይል ተፋሰስ ሀገሮች የትብብር ማዕቀፍ መርሆች ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል። የስምምነቱ በደቡብ ሱዳን መፈረም የአባይ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ከግብጽ ጋር ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮች የመቋጫ ምዕራፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ግድቡን በተመለከተ የሚኖር የድርድር መድረክ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። መጪዎቹ ጊዜያት የናይል ተፋሰስ ሀገሮች /ናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ (NBI) /በመባል የሚታወቀው ተቋም ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን (NBC) በመቀየር ከግብፅ እና ሱዳን ጋር የሚካሄዱ ንግግሮች በዚህ ተቋም አማካኝነት ብቻ የሚፈጸሙ እንዲሆኑ መስራትን ይጠይቃሉ ።
ግርማ ባልቻ፣ ሐምሌ, 2016 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም