ዛምቢያ የፀረ ሙስና ተቋሟ በሙስና ተዘፍቋል በሚል አመራሮቹን ከሥራ አገደች

ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዛምቢያ ሙስና ከተንሰራፋባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በሥልጣን ላይ ያሉት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሀኪንዴ ሂቺለማ በሙስና ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙስናን እንዲከላከሉ የተሾሙ የፀረ ሙስና ቦርድ አባላትን ከሥራ አግደዋል:: የፀረ ሙስና ቦርድ አባላቱ በሙሰኞች ላይ የተጀመሩ ምርመራዎችን ጉቦ እየተቀበሉ አቋርጠዋል ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን እንደመጡም በቀድሞው የሀገሪቱ መንግሥት አስተዳደር ወቅት በሙስና ተግባር የተሳተፉ አመራሮች ላይ ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚል አዲስ የፀረ ሙስና ቦርድ አቋቁመው ነበር፡፡

ይሁንና ሙስናን እንዲታገል የተቋቋመው ይህ ተቋም ራሱ በሙስና ተዘፍቆ ተገኝቷል በሚል የፀረ ሙስና ቦርዱ እንዲፈርስ ተደርጓል።

የዛምቢያ ፀረ ሙስና ቦርድ አራት ከፍተኛ አመራሮች ያሉት ሲሆን ቦርዱ በሙስና ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው የነበሩ ሰዎችን ሙስና እየተቀበሉ ምርመራውን እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡

በተለይም በቦርዱ ውስጥ ይሠራ የነበረ አንድ ባለሙያ በሙስና ተጠርጥረው ምርምራ ሲደረግባቸው የነበሩ የቀድሞ ፖለቲከኞች እጅ መንሻ እየሰጡ ምርመራቸው እንደተቋረጠላቸው ይፋ አድርጓል፡፡

ይህን ተከትሎ ጉዳዩ በመላው ዛምቢያ ዋነኛ የወቅቱ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን የፀረ ሙስና ቦርድ አመራሮች አስቀድመው ራሳቸውን ከኃላፊነት በማግለል ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ዘግይቶ ባወጣው መግለጫ የፀረ ሙስና ቦርድ አመራሮች ራሳቸው በሙስና በመዘፈቃቸው ምክንያት ቦርዱ እንዲፈርስ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You