የደቡብ ኮሪያ ቀዳማዊ እመቤት ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተገለጸ

ቀዳማዊ እመቤት ኪም ኪዮን ሂ በስቶክ ማጭበርበር እና 2,200 ዶላር ዋጋ ባለው የቅንጦት ቦርሳ ጉዳይ በሙስና ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል።

የደቡብ ኮሪያ ቀዳማዊ እመቤት በማጭበርበር ተጠርጥረው እየተመረመሩ መሆኑ ተገለጸ። ይህ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ተቃዋሚዎች የመንግሥት የሥነ ምግባር መመሪያ በመጣስ ቅንጡ የዳዮር ቦርሳ የተቀበሉት እና በስቶክ ማጭበርበር ውስጥ ሚና እንዳላቸው በሚጠረጠሩት ቀዳማዊት እመቤት ላይ ልዩ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

የሴዑል ማዕከላዊ ግዛት የዓቃቤ ሕግ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ዓቃቤ ሕግ ባለፈው ቅዳሜ በኪም ላይ “የፊት ለፊት ጥያቄ” ማድረጉን ገልጿል። ባለፈው ዓመት በድብቅ ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ኪም 2,200 ዶላር ዋጋ ያለው ቅንጡ ቦርሳ ሲቀበሉ ታይተዋል። የሀገሪቱ ጋዜጦች ይህን ክስተት ‘የዳዮር ባግ ስካንዳል’ ወይም የዳዮር ቦርሳ ቅሌት ሲሉ ጠርተውት ነበር።

ቅሌቱ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮኦል ፓርቲያቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር በተካሄደው ምርጫ እንዲሸነፍ አሉታዊ ተፅዕኖ አድርጓል። ይህ ቀዳማዊ እመቤቷ የተቀበሉት ስጦታ፣ ማንኛውም የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ሚስቶቻቸው ከ750 በላይ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ስጦታዎች እንዳይቀበሉ የሚከለክለውን ሕግ የሚጥስ መሆኑ ተመላክቷል።

የኪም ረዳቶች ለመርማሪዎች እንደተናገሩት ቀዳማዊ እመቤቷ ቦርሳውን በገዙበት ቀን እንዲመልሱ ቢነገራቸውም፣ ረስተው አለመመለሳቸውን ሮይተርስ ዮንሀፕ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ዩን የቦርሳውን ቅሌት በተመለከተ በየካቲት ወር ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ጉዳዩ ፖለቲካዊ ወጥመድ ነው ሲሉ አጣጥለውት ነበር። ዩን እንዳሉት ባለቤታቸው ኪም ስጦታውን የተቀበሉት አልቀበልም ለማለት አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ነው ነበር ያሉት። ነገርግን ዩን ዘግየት ብለው በግንቦት በሰጡት መግለጫ የባለቤታቸው ስጦታ መቀበል ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You