የኢትዮጵያ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ይታወቃል:: ከዚህ ውስጥ በበጋ መስኖ ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት አንዱ ነው:: በተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ ላይ እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ መኖሩም ይታወቃል:: ይሁንና መሰል የሆኑ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ዛሬም ድረስ የዕለት ጉርስ ማግኘት ያልቻለ የኅብረተሰብ ክፍል መኖሩ የማይታበል ሐቅ ነው::
በተለያዩ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የየዘርፉን ባለሙያ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን በመጋበዝ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የውይይት መድረኮችን የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፤ ከሰሞኑም ተመሳሳይ መድረክ አዘጋጅቶ የዘርፉን ምሁራን ያከራከረ ሲሆን፣ ክርክሩ ዋና ትኩረት ያደረገውም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ያለመረጋገጡ መንስኤ ምንድን ነው? ለማሻሻልስ መደረግ ያለበት ምን ዓይነት ተግባር ነው? የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥስ የማን ኃላፊነት ነው? በሚል ዙሪያ ነው::
የዕለቱን መድረክ ሲመሩ የቆዩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ፣ እንዳሉትም፤ የውይይቱ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ሳትችል የቆየችበትን መንስዔ አጠቃላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው:: ሀገራዊ የምግብ ዋስትና ማሻሻያ ስልቶችን ለመጠቆምም ጭምር ያለመ ነው::
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ፤ ጽንሰ ሃሳቦቹ ሶስት ጉዳዮች ሲሆኑ፣ እነርሱም በምግብ ራስን መቻል፣ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ናቸው:: በምግብ ራስን መቻል ሲባልም ሀገራት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል በቂ የማምረት አቅምን የሚያሳይ ነው:: ስለዚህ የግብርና ምርትን መጨመር፣ የውጭ ምርቶችን መቀነስ፣ የምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ እና ለውጭ አቅርቦት ተጋላጭነትን መቀነስ ላይ ያጠነጥናል::
የምግብ ዋስትና ሲባል ደግሞ ከዚህ ትንሽ ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ደገፋ፣ በቂ ምግብ የማግኘት ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል:: አቅርቦት ላይ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎቱ ተደራሽነትን የሚያጠቃልል ነውም ብለዋል:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ የምግብ ዋስትና ጉዳይ አራት ምሰሶዎች አሉት:: አንዱ የምግብ በበቂ ሁኔታ መኖር ነው:: ሁለተኛው ተደራሽነት ሲሆን፣ ሶስተኛው ደግሞ አጠቃቀም፣ አራተኛው የሶስቱ ቀጣይነት እና መረጋገጥ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ፕሮፌሰር ደገፋ አስረድተዋል::
የምግብ ሉዓላዊነት ሲባል ደግሞ ሀገሮች የራሳቸውን የግብርና እና የምግብ ፖሊሲ የመወሰን መብቶቻቸውን ማስጠበቅ መቻል ላይ የሚያተኮር ነው:: ስለዚህ ሀገራት በሥነ ምህዳር ጤናማ እና በዘላቂነት የሚያመርቱት ጤናማ ባህላዊ ምግቦችን የማግኘት መብቶቻቸው እና የየራሳቸውን የምግብ እና የግብርና ሥርዓት የመወሰን መብታቸውን የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል::
ፕሮፌሰር ደገፋ፣ እኤአ በ2024 በዓለም ደረጃ ከ700 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ አለመሆኑን ጠቅሰዋል:: እነዚህም ሳይጠግቡ ወደ መኝታቸው የሚሄዱ ሲሆን፣ ከዚህ መካከል ወደ ሃያ በመቶው በአፍሪካ ከሳራ በታች የሚኖሩ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ በ1966 እና በ1977 ዓ.ም በምግብ እጦት የምትታወቅበት ጊዜ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ደገፋ፣ በሰላሙም ጊዜ ቢሆንም በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምግብ እጥረት የተጋለጠ መሆኑን አስታውሰዋል:: በአሁኑ ወቅትም ከአራት ኢትዮጵያውን መካከል አንዱ የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ አለመሆኑን አመልክተዋል:: ከአስር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ኑሮው በልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ገልጸዋል:: ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝብ ደግሞ በከፍተኛ እርዳታ እህል እየተዳደረ ያለ ነው ብለዋል::
ፕሮፌሰር ደገፋ፣ ለዚህ ዋና ዋና መንስዔ ናቸው ያሉት አራት ሲሆኑ፣ እነዚህም ተደጋጋሚ የሆነ ድርቅ፣ የአፈር መሸርሸርና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሠረተ ልማት እና የግብዓት አለመሟላት እና የኢንቨስትመንት እጥረት እንደሆኑ አብራርተዋል::
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ያለመረጋገጡ መንስኤ ምንድን ነው? ለማሻሻልስ መደረግ ያለበት ምንድን ነው? የምግብ ዋስትና መረጋገጥ የማን ኃላፊነት ነው? በሚል ዙሪያ ምሁራዊ እይታቸውን እንዲያካፍሉ ከተጋበዙት መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ኮሌጅ ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ሌላኛው ደግሞ የግብርና ኢኮኖሚስቱ ዳዊት ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ኮሌጅ ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ (ዶ/ር) ያለፉት ዓመታትንና የአሁኑን የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ሁኔታን በተመለከተ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት ግብርናን እና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ብዙ ጥረት ተደርጓል:: ከዚህ የተነሳ ምርትና ምርታማነት በተወሰነ ደረጃ አድጓል:: ለምሳሌ እኤአ በ1990 ወደ አስር ኩንታል የነበረው አማካይ ምርት በ2011 ላይ ወደ ሃያ ኩንታል መድረስ ችሏል:: በቅርቡ ደግሞ በ2022 እስከ 23 ኩንታል ደርሷል:: ስለዚህ ሙከራዎች መኖራቸውን ያመላክታል:: ይሁንና የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በሰፊው አልተረጋገጠም::
በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትና ማጣትም መስፋፋትም ወደ 58 ነጥብ አንድ በመቶ የደረሰ ነው:: ይህ በቁጥር ሲሰላ ከሰብ ሰሃራ አፍሪካ ከአፍሪካም እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረስን ነን:: ሌላው ማሳያ ደግሞ የመቀንጨር ሁኔታ አሁን የሚታየው እስከ 34 ነጥብ አራት በመቶ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል:: ስለዚህ በእርሳቸው እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠም::
የግብርና ኢኮኖሚስቱ ዳዊት ዓለሙ (ዶ/ር)፣ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ሁኔታ ከዓመት ዓመት የተለያየ ነው:: የምግብ ሥርዓቱ የተንጠለጠለው ዝናብ ላይ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የሚወሰነው እንደየዝናቡ ሁኔታ ነው:: ሌላው የምግብ ዋስትና እንዳይረጋገጥ ተግዳሮት የሆነው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ነው:: ምክንያቱም ቀደም ሲል ወደ 20 እና 25 ሚሊዮን አካባቢ የነበረ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት እስከ 130 ሚሊዮን የተጠጋ ነው
እዚህ ላይ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሰፊው ከዘረጋቸው ፕሮግራሞች አንዱ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ነው:: በዚህ ፕሮግራም የሚሳተፈው ቁጥር ደግሞ መቀነስ ሲገባው ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣ ነው:: ለአብነት ያህል የአማራ ክልል ቢወሰድ በፊት ከነበረው ተጨማሪ 17 ወረዳዎች በዚህ ፕሮግራም የታቀፉ ናቸው:: ከዚህ የተነሳ የዕለት ጉርስ ፈላጊው በርክቶ ይታያል ማለት ነው:: ስለሆነም የምግብ ዋስትና ሁኔታው እየባሰ እና ፈታኝ እየሆነ ነው ሲሉ ከፕሮፌሰር በላይ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ::
ታዲያ የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ያለመቻሏ ምክንያት ምን ይሆን ለሚለው ፕሮፌሰር በላይ እንደሚሉት፤ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዳይቻል ያደረገው ምክንያት ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ እርስ በእርሱ እንኳ ለማስታረቅ የቸገረ ጉዳይ ነው:: ይህ ፈተና ኢትዮጵያንንም አፍሪካንንም የነካ ነው:: ከዚህ ውስጥ አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው:: እኤአ ከ1960 ጀምሮ ወደ አንድ ነጥብ አንድ ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት ጨምሯል:: በሚቀጥሉት እስከ 2050 ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ሶስት ዲግሪ ሲልሺየስ ሙቀት እንደሚጨምር ይጠበቃል:: በዚያው ልክ የዝናብ ሥርጭትም፣ የጎርፉና የድርቁም ሁኔታ በጣም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል:: በእያንዳንዱ ዲግሪ ሴልሼየስ ጭማሪ እስከ አስር በመቶ ምርታማነት ይቀንሳል የሚል ጥናት አለ:: ስለሆነም አንዱ ትልቁ ችግር ይህ ነው ይላሉ::
ፕሮፌሰር በላይ አክለው ፣ ሁለተኛው ትልቁ ችግር ልክ እንደ ዳዊት (ዶ/ር)ሁሉ የሕዝብ ብዛት መጨመር ነው ይላሉ:: የሕዝብ ቁጥር መጨመር የተፈጥሮ ሀብት ላይ የማይሆን ጫና እያሳደረ ነው:: ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ባለው የሕዝብ መጨመር ስሌት ሲሰላ በ2050 ደግሞ ወደ 215 ሚሊዮን ሕዝብ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል:: ይህ በግብርና እይታ መብዛቱ ሳይሆን ሕዝቡ ምግብ፣ ማገዶ፣ ቤት ይፈልጋል:: ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ጥግግት በስኩዌር ኪሎ ሜትር 105 ሰው ነው:: በ2050 ደግሞ በስኩዌር ኪሎ ሜትር ወደ 193 ሰው ይደርሳል ይላሉ::
ሶስተኛው ምክንያት ብለው ፕሮፌሰር በላይ የጠቀሱት የማኅበራዊ አለመረጋጋትን ነው:: ግብርናን በአግባቡ ለመሥራትና የተመረተውንም ምርት ከቦታ ቦታ ለመውሰድ ማኅበራዊ አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው:: ከዚህ በተጨማሪ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓት እጥረትም ሆነ የመሬታችን መጎሳቆል ምርት እንዲቀንስብን አድርጓል ሲሉ ያስረዳሉ::
ለምሳሌ አብዛኛው አርሶ አደር ከጤፍ ምርት እየወጣ ወደ ባህርዛፍ ምርት እየገባ መሆኑንም ያስታውሳሉ:: ከዚህ የተነሳ ብዙ የመስኖ ቦታዎች ጨዋማ እየሆኑ ይገኛሉ::
ዳዊት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ያለመቻሏ ምክንያት ያሉት አንደኛው እንደ ፕሮፌሰር በላይ ሁሉ ምርትና ምርታማነት ማነስ ነው ይላሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ መሬትን በአግባቡ አለመያዝና ግብዓትንም ካለመጠቀም ጋር የተያያዘ መሆኑን ያስረዳሉ:: ከዚህ ጋር በተያያዘ የምርጥ ዘር አለመጠቀማችን ነው::
ምርጥ ዘር መጠቀም ከ20 እስከ 40 በመቶ ምርታማነትን እንደሚጨምርም አስታውሰዋል:: ሌላው የመስኖ አቅማችንን ባለመጠቀማችንና የመስኖ ልማቱ መዳከሙ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ::
ፕሮፌሰር በላይ እንደሚሉት፤ የምግብ ዋስትናውን ለማሻሻል መደረግ ያለበት በጥናት በተደገፈ ፖሊስና ተቋማዊ አደረጃጀት ማበረታቻ ቢደረግ ጥሩ ነው:: ለምሳሌ ድሮ የነበረ ዓይነት የግብዓት ድጎማ ወሳኝ ነው:: ይህ ዓይነቱ አሠራር በብዙ የአውሮፓና የኢስያ ሀገራት ያለ ነው:: ሁለተኛው የግብርና መሠረተ ልማትን ማሳደግና ከግብርና ጋር የተያያዙ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት መልካም ነው:: ሶስተኛው ምርምርና ልማትን በእውቀትና በክህሎት እንዲመራ ማድረግ እንዲሁም ኤክስቴንሽኑን ከፖለቲካው መነጠል ያስፈልጋል::
የተፈጥሮ ሀብት መጎሳቆልን ለማስቀረት በእያንዳንዱ አግሮ ኢኮሎጂና ሥርዓተ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ ቢሰራ መልካም ነው ብለዋል:: ኢትዮጵያ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን በተመለከተ ራሷን እንድትችል ቢጣር የተሻለ ነው::
ሀገራችን ወደ 48 አካባቢ አግሮ ኢኮሎጂ አላት ቢባልም የግብርና ሚኒስቴሩ እውቅና የሰጠው ወደ 32 አግሮ ኢኮሎጂ ነው የሚሉት ደግሞ ዳዊት (ዶ/ር) ናቸው:: ከዚህ የተነሳ በየትኛውም አካባቢ ያለ ሁሉ በእኛ ሀገር መብቀል ይችላል ይላሉ:: ይሁንና ለምሳሌ የአትክልት ዘሮችን ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ከውጭ እያስገባን ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ መመረት የሚችሉ በመሆናችው በእዚህ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል:: በተጨማሪም ሀገር በቀል እውቀትንም መቃኘቱ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል:: የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችም ሲቀረጹ ሀገር በቀል እውቀቶችን አካትተው ቢሆን መልካም እንደሆነ አስረድተዋል::
በሀገር አቀፍ ደረጃና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ኃላፊነቱ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ተዋንያኑ ብዙ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር በላይ፣ ዋና ተዋናይ ግን መንግሥት ነው ይላሉ:: አግባብነት ያለውና ሊተገበር የሚችል ፖሊሲ ማውጣት ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው:: ሁለተኛው ከምርምር ተቋማት ብዙ የሚጠበቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም:: ምርምሮችን ማፍለቅና ማሰራጨት ላይ በሰፊው መሳተፍ አለባቸው:: ሶስተኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ ሀገር በቀል እውቀትንም ከግምት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል:: በግብርናው ላይ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ትርፍን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው ልማት ላይ በማተኮር እነርሱም አርሶ አደሩም ተጠቃሚ እንዲሆን ሊሰሩ ይገባል::
ግብርናው ሀገር በቀል በሆነ ቴክኖሎጂና ሀገር በቀል ሳይንቲስቶች የሚመራ ባለመሆኑ ብዙ ነገር የተመሰቃቀለ እንደሚመስላቸው የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶችን መመለስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::
መንግሥትና የግሉ ሴክተር ተናብበው መሥራት አለባቸው የሚሉት ደግሞ ዳዊት (ዶ/ር) ናቸው:: ሌላው የግብይት ሥርዓቱ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ አሁን ድረስ ገበያ አጥቶ የሚሰቃይ አርሶ አደር እንዳለ ሁሉ፤ ምግብ አጥቶ የሚሰቃይ ሕዝብ አሉ በማለት ገልጸዋል:: ከዚህ አንጻር የገበያ ሥርዓቱ መታየት እንዳለበት አስረድተዋል::
የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ አሁን ከምታመርተው ጭማሪ ማምረት እንዳለባት ጠቅሰው፤ ሀገር በቀል እውቀትም ከግምት መግባት እንዳለበት አመልክተዋል:: የምርጥ ዘር የግብይት ሥርዓት ቢጠናከርና የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓትም በጊዜው ቢደርስ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን አብራርተዋል:: ምርምርና ልማትን በእውቀትና በክህሎት እንዲመራ ማድረግም ተገቢነቱ ላይ አ ስምረዋል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም