የደን ሀብት መረጃን በቴክኖሎጂ መምራት

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በደን ሀብት የተሸፈነች እንደነበረች መረጃዎች ይጠቁማሉ:: የደን ሽፋኗ 40 በመቶ ከነበረበት ሁኔታ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው:: ሀገሪቱ ይህ ሀብቷ ባለፉት ዘመናት ሲጨፈጨፍና ሲራቆት ቆይቷል:: በዓመት እስከ 100 ሺ ሄክታር የተፈጥሮ ደን ሲመነጠር፣ በሰደድ እሳት ሲወድም መቆየቱን ጥናቶች ያሳያሉ:: በዚህም የተነሳ ይህን ሀብቷን ከማጣቷ ባሻገር ለድርቅ ለአካባቢ መራቆት ለበረሃማነት ለምግብ እጥረት እና ለደህነት ስትጋለጥ ኖራለች::

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንን ለመቀልበስና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የአካባቢ ጥበቃ እና የደን ልማት ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛሉ:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) አነሳሽነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተጀመረው ‹‹የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር››ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች እየተተከሉ ነው::

በደን ልማት ሥራ ውስጥ እነዚህን ችግኞች መትከል ብቻ በቂ አይደለም፤ የደን ሀብቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዝ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል:: እንደ ሀገርም የደን ሀብቱን ለማወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው::

በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ የሀገሪቱ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በጥናት ተረጋግጧል:: ጥናቱ የደን ልማት ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን መስፈርት መሠረት የተሰራና ተቀባይነት ያገኘ ነው:: የደን ሽፋኑ ሲሰላ ዘመኑ የደረሰበት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋሉ መሆኑም ተመላክቷል::

ወርቁ ዘውዴ (ዶክተር) የደን ዘርፍ ተመራማሪና አስተማሪ እንዲሁም የደንና የሳተላይት መረጃ አማካሪ ናቸው:: እሳቸው እንደሚሉት፤ ቴክኖሎጂ ለሁሉም ሥራ ያስፈልጋል:: ዛሬ ላይ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር የሚጠቀሙበት የሳተላይት መረጃ አየር ላይ ባሉ ሳተላይቶች ተሰብስቦ ለመረጃነት የሚያገለግል ነው:: የደን ሀብቱም እንዲሁ በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ ያስፈልገዋል::

ሦስት ዓይነት የደን ሀብት መረጃዎች አሉ:: የመጀመሪያው ከመሬት የሚሰበሰበ መረጃ ነው:: ሁለተኛው በአውሮፕላን ወይም በዌብ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ ሦስተኛው ከሳተላይቶች የሚገኝ መረጃ ነው::

እነዚህም መረጃዎች የሚገኙበት በሦስት ዓይነት ዘዴዎች ነው፤ አንደኛው ኦፕቲካ (በፀሐይ ብርሃን ተጠቅሞ) መረጃ የሚሰበሰብ ነው:: ሁለተኛው ደግሞ የራዲዮ ሞገድ( ዌብ) ተጠቅሞ መረጃ የሚሰበሰብ ነው:: ሦስተኛው የራሱን ብርሃን ለቆ ከሚመለሰው ብርሃን ከሚያገኘው መረጃ የሚሰብሰብ ነው::

እነዚህ ሦስት የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶች ደኑን ለማወቅ የሚያስችሉ ናቸው የሚሉት ተመራማሪው፣ መረጃ መሰብሰቢያዎቹ ደኑ የት ቦታ ይገኛል? በዚያ ቦታ ላይ ምን ያህል መጠን ያለው ደን አለ? ያለውስ ደን ምን ይመስላል? የሚሉትን ለማወቅ የሚረዱ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ::

ደኑን ምን ይመስላል? በሚለው የዛፉን ቁመት፣ ቅርንጫፍና ስብጥር ማወቅ እንደሚቻል ገልጸው፤ ይህም የራሱን ብርሃን በመልቀቅ ከሚሰበሰበው መረጃ እንደሚገኝ ያመላክታሉ:: ‹‹ይህም ቴክኖሎጂ የዛፉን ቁመት፣ ቅርንጫፎች፣ ስብጥርና አጠቃላይ ደኑ ክፍተት አለው ወይስ ደፍን ነው ? የሚለውን ለመለየት ይረዳል:: መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ስለደን ማወቅ ያለብንን እንዲናውቅ ሊረዱንና በጣም ሊያግዙን ይችላሉ›› ብለዋል::

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ይተከላሉ:: እነዚህ ችግኞች በተባለው በቦታ ላይ ስለመተከላቸው በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማወቅ ይቻላል የሚሉት ተመራማሪው ፤ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ችግኞቹ የተተከሉባቸው ቦታዎች የት ነው? የሚለውን ለማወቅ እና ተከታታይነት ያለው ክትትል እንዲደረግ ያስችላል ይላሉ::

ለአብነት የአረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተተከሉ ችግኞች በአሁኑ ወቅት የደረሱበት ደረጃ ለመመልከት ያስችላል:: ሌላው ቀርቶ የዛፎቹ የካርበን፣ የናይትኖጂን እና ክሎሮፊን መጠን ወይም በቅጠላቸው ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች መጠን መለካትም ይቻላል:: በእነዚህ ነጥረ ነገሮች የተነሳ ይዘቱ እያደገ እያደገ ይሄዳል ይላሉ::

ዛፎች በጣም እያደጉ ሲሄዱ አረንጓዴነታቸው እየበዛ መሬት ላይ የሚታየው ክፍተት እየጠፋ ስለሚመጣ ይህ አረንጓዴነት የሚለካበት ቴክኒክም አለ:: ‹‹ችግኙ ሲተከል መጀመሪያ ክፍት ነበር፤ ከዓመት በኋላ የሆነ ደረጃ ላይ ደረሰ እያለን በዓመታት መለካት ይቻላል:: ትንሽ እየቆየ ከሄደ ደግሞ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዛፎቹን ቁመት መለካት ይችላል:: ከዚህ አንጻር አረንጓዴ ዐሻራን ልንከታተልባቸው የምችላቸው እድሎች ሰፊ ናቸው›› ሲሉ ያስረዳሉ::

ኢትዮጵያ የደን ሀብትን በቴክኖሎጂ ከመምራት አንጻር በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በምርምር ቦታዎች ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሂደት ጥሩ ተሞክሮዎች አሉ የሚሉት ወርቁ (ዶክተር) ፤ ቀደም ብለው የሚታዩት ክፍተቶች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተሻሉ ሥራዎች እየታዩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ:: ይህም ቢሆን ግን ክልሎችም እየሄዱበት ካለበት ሁኔታ አንጻር ይህንን ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመው የደኖችን መረጃዎች እየተከታተሉ እየሰሩ ናቸው ለማለት ግን እንደማያስደፍር ይናገራሉ::

በጅምር ደረጃ አበረታች ነገሮች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ውሏል ለማለት እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ:: እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ደን ልማት ክልሎችን ለማገዝ የሚሰራቸው ሥራዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ:: ‹‹እዚህ ውስጥ እኛም እንደ ባለሙያ አብረን እየሰራን እንገኛለን፤ ጅምሮቹ ጥሩ ናቸው፤ ግን ሌላው ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት አንጻር ስንመለከት ብዙ ይቀረናል›› ብለዋል::

ቴክኖሎጂን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ያሉት ተግዳሮቶች ውስን ናቸው የሚሉት ዶክተር ወርቁ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የባለሙያ እጥረት መሆኑን አንስተዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ የደን መረጃ ለመሰብሰብ መሬት፣ ድሮን እና አውሮፕላን እንዲሁም ሳተላይት መጠቀም የግድ ይላል፤ አብዛኞቹ ባለሙያዎች የሳተላይት መረጃ ትንተና ልምዶች አላቸው:: ነገር ግን መሬት ለመለካት የራሱን ብርሃን ለቆ የሚለካውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ከማወቅ አንጻር መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ:: እነዚህ ነገሮች ቢጨመሩ በአቅም ደረጃ በባለሙያ በኩል ብዙ ችግር አይኖርም:: ይህ ሥራ የተወሰኑ ባለሙያዎች ብቻ የሚችሉት ይሆንና ዋናው ቦታ ላይ ብዙም ጠንካራ እንዳልሆነ ያመላክታሉ::

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ በኢትዮጵያ የደን ልማት ባለሙያዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል:: የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሌሎች ባለሙያዎችን በማፍራት ሥራው የበለጠ ተጠናክሮ ወደፊት ሊሰራበት እንደሚገባ ያመላክታሉ::

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ካርበን ልቀት ጋር ተያይዞ ደን ያለበት ሁኔታ እንደሚለይ ይታወቃል:: እንደ ሀገር እኛ ደኖች አሉን ብለን ስንናገር ደኖቹ የት ቦታ ነው ያሉት የሚለውን ለመለየትና ለማወቅ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመው የራሳቸውን ባለሙያ ልከው ነው የሚያረጋግጡት:: እኛም ቀደመን ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን የሰራነው ሥራ መረጃ ከነማስረጃው ይዘን አብረን በመሥራት ማሳየት አለብን:: እስካሁን ግን እዚህ ላይ እምብዛም ሥራ አልተሰራም››ይላሉ::

መረጃዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ የመያዙ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሎ አድጎ አብሮ መሥራት ካልተቻለ ወደኋላ መቅረት እንደሚመጣ አመልክተው፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያሉትን ጅምሮች ይበልጥ በማሳደግ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ አለብን ሲሉ ያላቸው እምነት ገልጸዋል::

ይህ ዘመን የቴክኖሎጂ ዘመን እንደ መሆኑ ነፃ ዳታ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል የሚሉት ተመራማሪና አማካሪው፣ የባለሙያዎችን አቅም መፍጠርና ዳታው የሚተነተንባቸውን እንደ ኮምፒውተር፣ ሶፍትዌር እና የመሳሰሉት ቁሳቁስ በማሟላት ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል::

ቀደም ሲል እ.ኤ.አ 2008 የናሳ የሳተላይት ዳታ በነፃ ይሁን የሚለው የመጀመሪያ አዋጅ እስከሚታወጅ ድረስ ዳታ የሚገኘው በግዢ ነበር ሲሉም አስታውሰው፣ ምክንያቱም ዋጋው ውድ ስለነበር እንደ ሀገር ገንዘብ ማውጣትና የሳተላይት ዳታ መግዛት ከባድ እንደነበር ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት ይህ ሁሉ ችግር ተቀርፎ የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ዳታ በነፃ እንዲገኝ የሚያደርግ እድል ተፈጥሯል ሲሉም አስገንዘበዋል::

በተለይ ዳታ ማግኘት ላይ የነበረው ተግዳሮት መቅረፉ ትልቅ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የባለሙያውን አቅም መፍጠር ይቀራል ይላሉ:: ‹‹ሥራውን መሬት ላይ በማውረድ መጠቀም ከቻልን ያንን ያህል የሚያስቸግር ነገር ይኖራል ብዬ አላሰብም›› ሲሉ ወርቁ (ዶክተር) ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞቱማ ቶሌራ (ዶክተር) በበኩላቸው እንደ ሀገር የደን ሀብት መረጃን በቴክኖሎጂ በመታገዝ መሥራት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን ይናገራሉ:: በደን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቶታል:: የዘንድሮ የ2024 ዓለም አቀፍ የደን ቀን መሪ ቃል ከፈጠራና ኢኖቬሽን ጋር መሆኑን ለቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ያሳያል ሲሉም ጠቅሰው፣ እንደ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ያለው የቴክኖሎጂ ምን ይመስላል:: በደን ዘርፉስ ላይ ምን ዓይነት ለውጦች እያመጡ ነው:: ዛሬ ላይ የት ነን የሚሉት በደንብ እየተፈተሹ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ::

እሳቸው እንደሚሉት፤ የደን መመንጠርም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያለው የተራቆተ ደንን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ የሚረዱ ብዙ ቴክኖሎጂዎች እየመጡ ናቸው:: በዘርፉ በየሰዓቱ ያለውን ለውጥ ጭምር ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግኝቶች እየታዩ ናቸው:: ለምሳሌ በደን ላይ የተከሰተ እሳትም ሆነ ወደፊት ሊከሰት የሚችል እሳትን መቆጣጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩ መጥተዋል:: እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በሚቀጥሉት ጊዜ እሳት ሊከሰት የሚችልበት ቦታዎች መለየት ያስችላል::

እዚህ ቦታ ላይ እሳት ተከስቷል እና ገና ሊከሰት ከሆነ በዚህ ጊዜ ውስጥ እሳት ሊከሰት ይችላል ብለው የእሳቱን መከሰት የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል የሚያሳውቅ ይሆናል:: አሁን ላይ ቴክኖሎጂውን ከመጠቀሙ አንጸር ጥሩ መሻሻሎች እየታዩ ለውጦች እየመጡ ስለመሆኑ ማሳያ ነው::

በሳተላይት መረጃ በኩልም የአንድ አካባቢን መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ማዕከል የሚላክበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፤ በዚህም ለውሳኔ የሚመቹ መረጃዎች እየመጡ ውሳኔዎች እየተሰጡ መሻሻሎች ከፍ እያሉ የሄደበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል::

ደኖች ለተለያዩ አላማዎች ከቦታቸው ላይ እንዲነሱ ቢደረግ እንኳ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ መልሶ የመተካት ሰፊ ሥራን መሥራት ይቻላል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ አንድን አካባቢ መልሶ ምቹ አካባቢ ለማድረግ ያሉ ደኖች ቢቆረጡ የተቆረጡት ዛፎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መልሶ መትከል እንደሚቻልም ይገልጻሉ:: ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማን ያነሳሉ:: በከተማዋ ምንም ዛፍ ባልነበረባቸው ቦታዎች ሳይቀር በቴክኖሎጂ በመደገፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ደን የሚመስል ነገር ለመፍጠር የተቻለበትን ሁኔታ መመልከት እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You