“አረንጓዴ ዐሻራ ‐ ነገን ዛሬ መሥራት”

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከሚከውኑት ሀገራዊ ትላልቅ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አንዱ ነው:: በየዓመቱ የክረምት መግቢያ ሰሞን ላይ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ብዙሃንን ባነቃነቀ የተሳትፎ ንቅናቄ ችግኝ እንተክላለን:: ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ለአንድ አላማ፣ በአንድ የመከርንበት የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር ተጀምሯል::

‹የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ› በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የዘንድሮው የግሪን ሌጋሲ ንቅናቄ እንዳለፈው ጊዜ ዓለም አቀፋዊነትን በተላበሰ መልኩ ርምጃ የጀመረ ነው:: የመሪ ሃሳቡ ዋና ዓላማ ኃላፊነትን ከሀገር ፍቅር ጋር ማስቀጠል የሚል አንድምታ ያለው ሲሆን በተለይ ደግሞ ወጣቱ አውቆና ተረድቶ ከአባቶቹ እዳን ሳይሆን ምንዳን፣ ጥላቻን ሳይሆን አንድነትን፣ ድህነትን ሳይሆን ልማትን የሚወርስበትን መድረክ ለማመቻቸት ጭምር ነው::

ሀገርና ትውልድ ተነጣጥለው የማይታዩበት አረንጓዴ ዐሻራ በመሪ ሃሳቡ በኩል መጪውን ከአሁኑ ጋር አስተሳስሮ በማስቀጠል ረገድ ሚናው ላቅ ያለ ነው:: ከዛሬ ወደ ነገ የሚሸጋገርን ትውፊት በቅብብሎሽ ለማስቀጠል እንደምቹ አጋጣሚ የተፈጠረ ከሕዝብ ለሕዝብ የሆነ እሳቤ ነው:: ትውልዱን ከኃላፊነት ጋር ለሀገር የሚታትርበትን ሞራል ለመፍጠር አቅም የሚሆን፣ በድርቅና በበረሃማነት በድህነት የምትታወቅን ሀገራችንን በልምላሜ ለመግለጥ ቆርጦ የተነሳ ንቅናቄ ነው::

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው “እኛ ላይ እዳ ወድቋል ይሄን እዳ ለልጆቻችን ማውረስ የለብንም” ብለዋል:: በንግግራቸው ላይ እዳ ተብሎ የተገለጸው ከመትከልና ከማጽደቅ ጋር ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣውን ትውልድ ነው:: ሀገር በኃላፊነት እዳን በሚቀይር አእምሮና ልብ የተማገረች ናት:: በሥራችን ኃላፊነታችንን መወጣት ካልቻልን ከጥቅማችን ጉዳታችን ያመዝናል:: ያለፈውን ትተን ስለመጪው ብናወራ ዛሬ ላይ እየተከልናት ያለችው አንድ ችግኝ መጪውን ትውልድ ነፃ ከማውጣትና እኛንም በታሪክ ከማስመስገን አኳያ አስተዋጽኦዋ የላቀ ነው::

ሰው የልማዱ ባሪያ ነው፣ ልምምድ በቀላሉ የምንገላገለው አይደለም:: ዛፍ እየቆረጥን በመጥፎ ልማድ መጥተናል:: ይሄ ልምምድ በጎ በሆነ በህብረት ልምምድ የሚጠፋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ አክለውም ከ40 በመቶ ወደ ሶስት በመቶ የደን ሽፋን መውረዳችንን ከአጉል ልምምዳችን ጋር አያይዘው ተናግረዋል:: በእውነቱ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነው:: ዓለም ቀስ በቀስ እየጠፋች ነው ያልኩትና ብሔራዊ ሙዚየም ያስተዋልኩት የድሮና የዘንድሮ የተፈጥሮ ምስል ይሄን እውነታ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ::

ወደ መፍትሔው መማተር ከዚህ ዓይነቱ አደጋ ለመውጣት ብቸኛ መንገዳችን ነው:: ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት “እኚህ መጥፎ ልምምዶች የሚሻሩት እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ባሉ ማህበራዊ ልምምዶች ነው:: የአየር ንብረት ለውጥ በስብሰባ አይቀየርም:: በወሬ፣ በሱፍ ለባሾች አይቀየርም:: እጃቸውን ጠቅለው በሚተክሉ የሚቀየር ነው:: መትከል ምግብም ነው፣ ውበትም ነው:: የምንተክለው ምግባችንን ነው:: የምንተክለው ውበታችንን ነው:: ባለፉት ጊዜ በመትከላችን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ እስከ ውጭ ኤክስፖርት ድረስ ተጠቃሚዎች ነበርን” ሲሉ ተናግረዋል::

በዚህ ዓመት ካለፈው ልቀንና ገዝፈን ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ተበስሯል:: ዛሬን ነገ መሥራት ማለት በዚህ ዓይነቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚገለጽ ነው:: ሰዎች ወደ ጫካ መሄዳቸው ቀርቶ ጫካን ወደ ሰዎች ማምጣት የዚህ ትውልድ ሚና እንዲሆን ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ተግባር መሆኑ ሌላው በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተበሰረ ጉዳይ ነው:: ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናት የራሳቸውን ዐሻራ በማሳረፍ የአረንጓዴ ዐሻራ የሚናው ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሌላው የአደራ መልዕክት ነው::

ዛፍ ከመቁረጥ መጥፎ ልማድ ዛፍ ወደመትከል የብዙሃን ልምምድ መሸጋገር የትውልዱ ኃላፊነት እንዲሆን የሁላችንም ምኞት ነው:: በዚህ አቅጣጫ ካልሆነ ዋጋ እያስከፈሉን ካሉ ልምምዶቻችን መራቅ አንችልም:: የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ችግር ነው:: ራሳችንን የምንታደገው ሌሎችን በመጠበቅ ሳይሆን የድርሻችንን በመወጣት ነው:: ተክለን ስናጸድቅ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው:: በኩራትና በመንደላቀቅ የምንኖርባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ እየፈጠርን ነው:: ይሄ እውነታ በአንድ ቃል ቢገለጽ ነገን ዛሬ መሥራት የሚለውን ይሆናል:: አረንጓዴ ዐሻራ ነገን ዛሬ ከመሥራት ሌላ በምንም አይገለጽም:: የዛሬ ኃላፊነቶቻችን ነገን ነፃ የምንወጣባቸው፣ እንደ ሥጋት ከፊታችን የተጋረጡን የአየር ንብረት ለውጦችን የምናልፍባቸው፣ በርሃማነትንና የአየር መዛባትን የምናስተካክልበት ከምንም በላይ ደግሞ ራሳችንን ከተፈጥሮ አደጋ ስጋት ጠብቀን ምቹ ከባቢን የምንፈጥርበት ነው::

አንዳንድ አጋጣሚዎች ዋጋቸው በተመን አይለካም:: የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄም ከተመን በላይ የሆነ በሕይወት የሚሰላ አላማ ያለው ዓለም አቀፍ እውነታ ነው:: የምንተክለው ላለመሞት ነው:: የምናጸድቀው በአረንጓዴ ዐሻራ ቀጣይነት ያለው የመኖር ዋስትናን ለማረጋገጥ ነው:: ለተፈጥሮ ሞልታና ተትረፍርፋ የተሰጠችን ቢሆንም በእኛ እንዝህላልነት ኦናዋን አስቀርተናታል:: ምድር አረንጓዴ ሰማይ ደግሞ በሰማያዊ ቀለም አጊጠው በፈጣሪያቸው በኩል የተቸሩን ስጦታዎቻችን ናቸው:: ሆኖም ግን እነዛ ጥንተ መልኮች አሁን ላይ የሉም::

ዓለም መልስ ካጣችለት አሁናዊ ጉዳይ አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው:: መነሻው ብዙ ቢሆንም ማዳረሻው ግን የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ነው:: ዛፍ ስንተክል ደልቶን አይደለም እንደ ሀገር መጪ ጫናዎቻችንን ለማስቀረት እንደ ዓለም ደግሞ ለሌሎች የመኖር ዋስትና ለመሆን ነው:: ያለፈውን ትተን ሰሞነኛውን የአየር ንብረት ሁኔታ ብንመለከተ በዓለም ላይ በዚህ ሳምንት ብቻ በድንገተኛ ሙቀት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ይሄ ችግር እኛ ሀገር ያለመግባቱ ዋስትና ከዚህ ቀደም የተከልናቸው ዛፎች አስተዋጽኦ ነው::

በመንግሥት በኩል ወደ ትውልዱ የወረደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አላማው ለመጪው ትውልድ እዳን ያለማውረስ ግብግብ ነው:: ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ሥነ ምህዳርን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የአየር ንብረት ስጋትን የመከትንበት ሁኔታ አለ:: ብዙ ሀገራት የምንሰማቸው የተፈጥሮ አደጋዎች እኛ ጋ ያልቀረቡት ትላንትና በወሰድነው የአረንጓዴ ዐሻራ ርምጃ መሆኑ ማረጋገጫ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹አሁን ዛሬ የማንተክል፣ የማንከባከብ ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አፈር እየተሸረሸረ፣ እየተወሰደ ከሆነ ጊዜ በኋላ እንትከል ብንል እንኳን ለመትከያ የሚሆን አፈር አናገኝም:: የተቆረጠ ዛፍ በአጭር ዓመት ውስጥ ራሱን ይተካል የተወሰደ አፈር ግን በአንድ ሺ ዘመናት ውስጥም ራሱን ማደስ አይችልም› ሲሉ ዛፍ የመትከላችንን አንገብጋቢ ምክንያት አስረግጠው ተናግረዋል::

ዛሬ ላይ ካልተከልን ነገ ላይ እንደ ሰው የመኖራችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ይሄ ምርምር የማያስፈልገው ግልጽ እውነታ ሆኖ በሁላችንም የሚታመን ነው:: ዓለም በተፈጥሮ ስጋት በኩል ቀስ በቀስ እየጠፋች ነው:: ይሄ ጥፋት የሚያገግመው ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል ነው:: ልክ አንድን ቀዳዳ ጥብቆ በመርፌ ጥፎ የማሳመር ያክል የተፈጥሮ ሽንቁርም በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል የሚታከም ነው:: ካልሆነ ሽንቁሩ ሰፍቶ መጣፍ ወደማይችልበት ደረጃ ይደርስና ህልውናችንን ተረት ያደርገዋል:: ሳይቀጠል በቅጠል እንዲሉ የዛሬ ትጋቶቻችን ለነገ መልስ እየሰጡ ያሉ ተግባሮች እንደሆኑ መታወቃቸው ወደፊት እንድንገፋ የሚያደርገን ነው::

ዛፍን በኃላፊነት መትከልና ማጽደቅ ከመንግሥት ዓመታዊ እቅዶች መካከል አንዱ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል:: በቀጣይም በጀት ተመድቦለት በስፋትና በጥራት እንቅስቃሴው እንደሚቀጥል እየተነገረ ይገኛል:: ከዓመት ዓመት በኃይልና በብርታት መልኩን እየቀየረ የመጣው ይሄ ንቅናቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ አፍርቶ ግቡን እንደሚመታ እሙን ነው:: ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር የተገናኙ ማህበራዊ ልምምዶች በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ዓይነት ጥቅም ያላቸው ናቸው:: የመጀመሪያው ትውልዱን ከእዳ ማላቀቅ ነው:: በዚህ ውስጥ አብረው የሚነሱ ለውጥና እድገትን መሠረት ያደረጉ ሀገራዊ ትሩፋቶችም አብረው ይነሳሉ:: ትውልዱ በኃላፊነት ዛፍ ሲተክል መጪውን ጊዜ በተስፋ ከመቃኘት ጎን ለጎን ለሕይወት ዋስትና የሚሆኑ ዐሻራዎችን እያስቀመጠ ይሄዳል::

ሁለተኛው ከምንተክላቸው ዛፎች የምናገኘው በረከት ነው:: በረከቱ ብዙ ዓይነት ነው:: አካባቢን ከመጠበቅ፣ አፈር እንዳይሸረሸር ከማድረግ፣ የዝናብ ወቅትን ከመቆጣጠር፣ በርሀማነትን ከመከላከል፣ ክረምትና በጋ ወቅቱን ጠብቆ እንዲመጣ በማድረግ፣ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ፤ ንጹህ አየርን ለመተንፈስ… በረከቱ ብዙ ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ፋይዳ ምቹና ለጤና ተስማሚ የሆነ አካባቢን መፍጠር ነው:: በዚህ እንቅስቃሴ ላይ እንደ መንግሥት ትልቁ ኃላፊነት በተፈጥሮ አደጋ በኩል ከስጋት ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው:: በዚህም እየተሳካልን ይገኛል::

እንደ ሀገር የምንተክለው እዳን ለትውልዱ ላለማውረስ ብቻ አይደለም በድህነት ላይ እንደቁምጥና ከሚነሳው የአየር ንብረት ስጋት ለመዳን ነው:: ተፈጥሮ ዛፍ ሰጥቶናል የእኛ ኃላፊነት የተሰጠንን መንከባከብ ነበር ፤ ሆኖም ያንን ባለማድረጋችን ካለፈው እዳ ተቀብለን ለመጪው እዳን እያስተላለፍን ነው:: አሁናዊ ትግላችን ይሄንን የውርስ እዳ ለማስቀረት ነው:: በገዛ ጥፋታችን መንከባከብ ብቻ የሆነውን ተግባራችንን ወደመትከል አሸጋግረነዋል:: አሁን ላይ ካልተከልንና ካልተንከባከብን ለም አፈሮቻችን በመሸርሸራቸው እህል ማብቀል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ:: ይሄ መሆኑ ርሀብና ድህነት ስር እንዲሰድ መንገድ የሚጠርግ ነው::

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚተረጎም አይደለም:: ሁሉም ቦታ ያለ ሁሉንም የሚነካ የህልውና ጉዳይ ነው:: ለዛም ነው መንግሥት ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ባልተቋረጠ መልኩ እያስኬደው ያለው:: የዛሬ ትጋቶቻችን የመጪው ዘመን ፍሬዎቻችን ናቸው:: ኃላፊነትን ከሀገር ፍቅር ጋራ ባጣመረ መልኩ እየተከልን መንከባከብ ነገም የሚቀጥል የቤት ሥራችን ነው:: ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ ትውልድ በትችትና በወቀሳ የሰላ ከመሆኑ በላይ በስንፍና የታወቀ ነው:: እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች ደግሞ በኃላፊነት ተጀምረው የሚያበቁ ናቸው:: የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድን ነው የምትፈጥረው:: የሚያጸድቅ ትውልድ ደግሞ በእዳ ሳይሆን በምንዳ የሚያምን ነው::

የዘንድሮው ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዳለፈው ጊዜ ከሀገር አልፎ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽፋን ያለው ሆኖ ለብዙዎች የመነቃቃት መንፈስን የሚፈጥር እንደሚሆን ይታመናል:: ያለፉት የተሳትፎ ዓመታቶች ከሀገር ልቀው መላውን ዓለም ያነጋገሩ እንደነበሩና በርካቶችን ለትጋት የቀሰቀሱ እንደሆኑ ይታወሳሉ:: ዘንድሮም ካለፈው በተሻለ ሕዝባዊ ተሳትፎና እንቅስቃሴ መሰል ድሎችን ለመጎናጸፍ ዝግጅቱ በሁሉም ዘንድ ይሁንታን አግኝቷል::

አረንጓዴ ዐሻራ የሕይወት ደም ስር ነው:: ዛፍ ከሕይወት ጋር የተሰላ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው:: የምንተነፍሰው አየር ከአረንጓዴ ቀለም መንጭቶ ወደሳንባችን የሚገባ ከዛም ተመልሶ የሚወጣ ዓይነት ተፈጥሮ ያለው ነው:: ስንተክል ሕይወት እየተከልን ነው፣ እድሜ እየቀጠልን ነው:: ስናጸድቅ ህልሞቻችንን እውን እያደረግን ነው:: ከዚህ ወዲያ ያለው ድርጊት ለሕይወት እምብዛም ዋጋ የሌለው ነው::

ዛፍና ሕይወትን በአንድ ተፈጥሮ መስለን ብንናገር አካልና ነፍስ ይሆናሉ:: አካል ያለ ነፍስ ነፍስም ያለ አካል ማደሪያ የለውም:: ይሄ እንደ ግለሰብና እንደ ማህበረሰብ የሰፋ አድማስ ያለው እሳቤ ነው:: እንደ ሀገር ሲሆን ደግሞ የት ድረስ እንደሆነ መረዳቱ ቀላል ነው:: አረንጓዴ ዐሻር መነሻው ሀገር እና ትውልድ መፍጠር መሆኑ እምብዛም የሚያጠያይቅ ባይሆንም ከሞራልና ከያገባኛል ጋር ሲሆን ደግሞ ዋጋው የዛኑ ያክል የላቀ ነው::

ሀገር ከዛ ወደዚህና ከዚህ ወደዛ ቅብብሎሽ ናት:: ቅብብሎሹን የተሳለጠ የሚያደርገው ደግሞ የትውልዱ ኃላፊነትን የመሸከም አቅም ነው:: በበሳል ምሬትና ሁሉን ባቀፈ የጋራ ተልዕኮ ሀገር የትውልድ ቅብብሎሽ ናት ስንል እንዲህ ባለው እሴት በኩል መሆኑ አይጠፋንም:: ችግኝ ስንተክል ትውልድ እየተከልንና መጪውን ጊዜ ብሩህ እያደረግን እንደሆነ ለሁሉም የሚታመን እውነታ ነው:: ዓለም በግሎባል ዋርሚንግ እና በተያያዥ ችግሮች በምትሰቃይበት በዚህ ጊዜ መጪውን ቃኝቶ ቀድመን መዘጋጀታችን አርቆ አሳቢነታችንን የሚያሳይ ነው:: ለዚህ ደግሞ መንግሥት በኩር ተወዳሽ ሲሆን ሕዝብ ተከታዩ ተመስጋኝ ይሆናል::

በተያያዙና በተባበሩ እጆች በተከልናቸውና ባጸደቅናቸው ችግኞች አዲስ ክስተት ፈጥረን ከዓመት ዓመት መነጋገሪያ ሆነናል:: ኢትዮጵያውያን በአንድ ስንነሳ ዓለምን ማስደነቅ እንደምንችል በተለያዩ አጋጣሚዎች አስመስክረናል:: ጊዜው በአረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሁልጊዜያችን ታሪክ የምንሰራበት ነው:: የታሪካችን መነሻ አሁን ቢሆንም መድረሻው ነገ ሆኖ ለእያንዳንዳችን እንደ አደራ ተሰጥቷል:: ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ› እንደመሪ ሃሳብ ብዙሃነትን ያቀፈ፣ ከዛሬ ወደነገ የሚሻገር አንቂና አሳታፊ መሆኑ እሙን ቢሆንም ከዚህ በላይ ጎልቶ የሚነሳው ደግሞ አላማ መር በሆነ ንቅናቄ ከእዳ ወደምንዳ፣ ከነውጥ ወደለውጥ፣ ከንቅቅፍ ወደትቅቅፍ አሻጋሪ መሆኑ ነው:: ቸር ሰንብቱ!

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You