የችግኝ ተከላው ባሕል ለእንክብካቤውም ይዋል!

የሀገራችን የክረምት ወራት ከሌሎች ወራት የተለየ ገጽታ አላቸው:: የዝናብ ወቅት እንደመሆኑ ጭጋጉ፣ ዝናቡ፣ ጭቃው፣ ብርዱ፣ ወዘተ አስፈሪ ወቅት ቢያደርጋቸውም፣ ከሀገራችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ የማምረት ሥራዎች ከሚካሄድባቸው ወቅቶች መካከል ዋናው የሆነው የመኸር እርሻ ሥራ የሚካሄድባቸው ናቸው::

የግብርና ሥራው ደግሞ በሰብል ልማት ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም፤ የደን ልማት ሥራዎችም በስፋት ይካሄዳሉ:: እንደ ክረምት ከችግኝ ጋር የሚስማማና የሚግባባ ወቅት ባለመኖሩ ችግኞችን ለመትከልም ለመንከባከብም ይህ በእጅጉ ይመረጣል:: በዚህ ወቅት በተለይ አርሶ አደሮች በችግኝ ተከላው በስፋት ሲሠሩ ኖረዋል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ታላቅ ሥራ ለአርሶ አደሩ ብቻ የተተወ አይደለም:: ከተሜውም በከተሞች አካባቢ፣ ለአረንጓዴ ስፍራ በተተዉ ክፍት ቦታዎች እንዲሁም ወደ ገጠር ጭምር በስፋት በመግባት የችግኝ ተከላውን በከፍተኛ ርብርብ በስፋት እያካሄደ ይገኛል::

የችግኝ ተከላ ሥራን ፊትም ኅብረተሰቡ ክረምቱን ተከትሎ በተበታተነ መልኩ በየፊናው ሲያከናውነው የኖረ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተቀናጀ መንገድ የሚከናወን ሀገራዊ ተግባር ተደርጓል:: ክረምትና የችግኝ መትከል ሥራ የማይነጣጠሉ ሆነው በአንድነት እየታዩ ናቸው፤ ይህም የችግኝ ተከላውን ባሕል ማድረግ አስችሏል:: የችግኝ ተከላው በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመንግሥት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ‹‹የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር›› የሚል መጠሪያም ተሰጥቶት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለአምስት ዓመታት የተካሄደበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል::

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) አነሳሽነት በሃገር አቀፍ ደረጃ በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር በማንቀሳቀስ እያሳተፈ በመሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል አስችሏል::

በዚህ የችግኝ ተከላ በአንድ ጀንበር በተተከሉ የችግኞች መጠን በሀገሮች የተያዙ ክብረ ወሰኖችን ለመስበር በማቀድ ጭምር በተከናወነ የችግኝ ተከላ ከአቅድም በላይ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል የተቻለበት ሁኔታም እንደነበር ይታወቃል:: በዚህም ምንም እንኳ በተለያዩ ምክንያቶች ሪኮርዱ ባይመዘገብም፣ በአንድ ጀምበር የ66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ተይዞ የነበረውን የዓለም የክብረ ወሰን ለመስበር መሠራቱ ይታወሳል::

መላ ዓለም በአየር ንብረት መዛባት በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በአውሎ ነፍስ፣ በሰደድ እሳት እና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ለመሆኑ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የተፈጥሮ ሀብት መራቆትና የደን መጨፍጨፍ ነው:: ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ዋናዋ ገፈት ቀማሽ መሆኗ ይታወቃል::

ይህን ዓለምን ስጋት ላይ እየጣለ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም አይነተኛ መፍትሔ ተብለው ከተቀመጡ ተግባሮች አንዱ ችግኝ በመትከል የደን ሀብትን ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለስ ነው:: ኢትዮጵያም አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት ያለች ሀገር እንደመሆኗ ለደን ልማት ትኩረት በመስጠት ‹‹አረንጓዴ ዐሻራ›› በሚል የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በየዓመቱ በቁርጠኝነት እየተገበረች ትገኛለች::

በ2011 ዓ.ም በተጀመረውና ላለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብርም 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል:: ዘንድሮም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ትግበራ ገብታለች::

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር:: ይህን የደን መመናመን ለማስቆምና ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ በተከናወነ ተግባር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣትም ተችሏል:: በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ቅድመ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም. ከነበረበት 17ነጥብ2 በመቶ ወደ 23ነጥብ6 በመቶ ከፍ ብሏል በሚል ከተገለጸው መረዳት እንደሚቻለውም በልማቱ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየት እየተቻለ መሆኑን ነው::

በ2013 ዓ.ም ‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ ››በሚል መርሐ ግብርም በሃገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ከመተከላቸው በተጨማሪ የችግኝ ተከላው ክፍለ አሕጉራዊ እንዲሆን ለማድረግ ጭምር ተሠርቶበታል:: በዚህም አንድ ቢሊዮን ችግኞች ለጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ መሰጠቱም ይታወሳል:: ሀገሪቱ ችግኝ በመትከል ለዓለም ጭምር እያበረከተች ያለችው አስተዋፅዖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ እየታየ ከመሆኑም በተጨማሪ በችግኝ ተከላው ለሌሎች ሀገሮች ተምሳሌት እንድትሆን እያደረጋትም ይገኛል::

ዘንድሮም 7ነጥብ5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም የችግኝ ተከላው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: እስከ አለፈው ሳምንትም ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል::

የሚተከሉ ችግኞች ብዛት ብቻ ሳይሆን እየጨመረ ያለው የችግኞች የፅድቀት ምጣኔ እየጨመረ ነው:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የችግኞች የፅድቀት ምጣኔ በአማካኝ 80 በመቶ ያህል ደርሷል:: ለእዚህ ደግሞ የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል::

አንዳንድ ወገኖች ግን ይህ የፅድቀት ምጣኔ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ይገልጸሉ:: እርግጥ ነው በተከላው እየታየ ያለው ርብርብ በእንክብካቤው ብዙም አይታይም:: ለእዚህ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ ለችግኞች ሊደረግ የሚገባው እንክብካቤና ክትትል በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ነው:: ይህም ችግኞቹ በእንክብካቤ ማግኘት ያለባቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ብዙ አልተሠራም በሚል ይገለጻል::

አንዳንድ ተቋማት ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ የተከሏቸውን ችግኞች መለስ ብለው እያዩ አለመሆናቸው፣ የተከላውን ያህል በእንክብካቤው የሚደረግ ርብርብ ብዙም አለመታየቱ ሲታሰብም ለእንክብካቤው የተከላውን ያህል ትኩረት አልተሰጠም ማለት ይቻላል::

አስተያየቱ ሊወሰድ ይገባዋል:: ለችግኞች የሚደረገው አንክብካቤ በሚፈለገው ልክ መሆን ከቻለ ችግኝ ከመትከል ባልተናነሰ በችግኝ እንክብካቤም ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ አስተዋፅዖ ማድረግ እንደሚቻል ይታመናል::

‹‹ችግኝና ሕጻን ልጅ አንድ ናቸው›› እንደሚባለው ሁለቱም በጥሩ ሁኔታ እንክብካቤ ከተደረገላቸው ለቁም ነገር እንደሚደርሱ ሁሉ ለችግኝ ተከላው የሚደረገው እንክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል::

በችግኝ እንክብካቤው ላይ ለመሥራት ከሚያስፈልጉት መካከል አንዱ ችግኞችን በመንከባከብ ላይ ያሉ ተቋማትን ተሞክሮ አውጥቶ ማሳየት ይጠቅማል:: ጥቂትም ቢሆኑ በእዚህ በኩል ጥሩ እየሠሩ ያሉ ተቋማት አሉ:: ይህን ተሞክሮ ማስፋት ይገባል::

ችግኞች ከተኮተኮቱ፣ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ከተጠበቁ፣ በበጋ ወቅት ደግሞ ውሃ የሚያገኙበት ሁኔታ ከተፈጠረ የፅድቀት መጠናቸው ብቻ አይደለም የሚጨምረው፤ እድገታቸውም የተፋጠነ ይሆንና ለተፈለገው ዓላማም ቶሎ መድረስ ይችላሉ::

ባለፉት ዓመታት የተተከሉና በአሁኑ ወቅት እየተተከሉ የሚገኙ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሙሉ ለመንከባከብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል:: የእንክብካቤ ሥራው በዘመቻ ሊፈጸም አይችልም:: በባለሙያ፣ በሠለጠኑ አካላት መፈጸም ይኖርበታል:: ይህን ማድረግ ይገባል::

ችግኞቹን በሙሉ ውሃ ማጠጣትና መኮትኮት ሊያስቸግር ይችላል:: በአቅራቢያችን ያሉትን ችግኞች ግን ውሃ በማጠጣት ጭምር መንከባከብ ይኖርብናል:: ሌሎች በሰፊና በሩቅ ቦታዎች ላይ የተተከሉትንና የሚተከሉትን ውሃ ማጠጣትና መኮትኮት ይቸገራል:: እነሱን ደግሞ ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመጠበቅ ብቻ የፅድቀት መጠናቸውን ማሳደግ እንዲሁም ለተፈለገው ዓላማም ቶሎ እንዲደርሱ ማድረግ ይቻላል::

አንዳንድ ተቋማት እንደሚያደርጉት ሥራ አጥ ወጣቶችን አደራጅቶም ይሁን በሌላ መልኩ ችግኞችን መንከባከብ ሁኔታም ይኖራል:: በእዚህም ወጣቶቹንም ሃገርንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል:: ወጣቶች በወል ቦታዎች የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ፣ በስፋራው የሚገኙ እንደ ሣር ያሉትን ደግሞ እንዲጠቀሙ ማድረግም ሌላው ለችግኝ እንክብካቤው የሚጠቅም ተግባር ነው::

እያንዳንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ ተሳታፊ እንዲሁም መርሐ ግብሩን የሚመሩ ከላይ እስከታች ያሉ አካላት ሕዝቡ ዐሻራውን ያሳረፈባቸው ችግኞች የት ደረሱ? ለችግኞቹስ ምን አይነት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው? በማለት በየጊዜው መጠየቅና እንክብካቤው በአግባቡ እንዲከናወን ማድረግም ይገባል::

ዘንድሮ 7ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኖችን ለመትከል የተያዘው መርሐ ግብር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል፤ ይህ ተሳትፎ ችግኞችን ከመትከልም እንዲሻገር በማድረግ ለእንክብካቤ ትኩረት ሰጥቶ መሠራትም ይኖርበታል:: ይህ ከሆነ እስከ አሁን የተከልናቸውም ሆኑ አሁን የምንተክላቸው ችግኞች አድገውና ለተፈለገው ዓላማ ደርሰው የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም:: ቸር እንሰንብት::

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You