በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ሰው ቀደም ብሎ ድሮን አብርሮ ነበር ተባለ

በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ሰው ቀደም ብሎ ድሮን አብርሮ ነበር ተባለ፡፡

የፊታችን ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ቅዳሜ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለው ወደ ህክምና መግባታቸው ይታወሳል።

ለጥቂት ከሞት የተረፉት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ነበር ማቲው ክሩክስ በተሰኘ የ20 ዓመት ወጣት በጥይት የቆሰሉት።

ማቲው ክሩክስ በ130 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ስናይፐር በተሰኘ የጦር መሳሪያ ዶናልድ ትራምፕን ተኩሶ አቁስሏቸዋል፡፡

የሀገሪቱ ሚስጢራዊ የደህንነት ተቋም ሠራተኞች ወዲያውኑ በወሰዱት የአጸፋ ርምጃ ማቲው የተገደለ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ትኩረት እንደሳበ ይገኛል።

ቢቢሲ የአሜሪካ ብዙሃን መገናኛዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ማቲው ክሩክስ ዶናልድ ትራምፕ ንግግር በሚያደርጉበት ቦታ ለይ አስቀድሞ ድሮን አብርሮ ነበር ተብሏል፡፡

ተጠርጣሪው ድሮን ያበረረው ግድያውን ለማሳካት ስለ ሥፍራው በቂ መረጃ ለማግኘት በሚል ሊሆን እንደሚችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ስለ ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን ከቀናት በፊት የማቲው አባት ልጃቸው የተለየ ባህሪ ማሳየቱን ተከትሎ ፖሊስ ክትትል እንዲያደርግ ከክስተቱ በፊት ሪፖርት አድርገው እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ ለማድረግ ወደ መድረኩ የመጡ ሰዎች ወጣቱ የጦር መሣሪያ ይዞ ማየታቸውን እና ሁኔታውን ወዲያውኑ ለፖሊስ አሳውቀው እንደነበር ተገልጿል።

ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ሚስጢራዊ ደህንነት ጥበቃ ክፍል ሃላፊ እና የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሃላፊ ሃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል ተብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You