በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ የሆነው 2016 በጀት ዓመት

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከሚባሉና ዘመን የተሻገረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ጥቂት ሀገራት አንዷናት። ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ባሳለፈቻቸው የ3ሺህ ዘመናት ታሪኳ ውስጥ በየዘመናቱ የዲፕላሚሲ ግንኙት በመፍጠርና ዐሻራ በማስቀመጥ ዛሬ ላይ የደረሰች ጥንታዊት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪካ ያላትና በየዘመናቱም የሀገሪቱን ጥቅም በዲፕሎማሲው መስክ ለማስከበር በርካታ ተጋድሎ ያደረጉ መሪዎችን ያፈራች ሀገር ነች።

ይኸው አኩሪ የዲፕሎማሲ ታሪክ ቀጥሎ በ2016 በጀት ዓመትም አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። በተለይም ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ አካሄድና ጎረቤት ሀገራትን ማዕከል ያደረገው ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘላት ነው። በ2016 በጀት ዓመት ከጎረቤትና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በማሻሻል፣ በማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር በኩል በርካታ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ጋር ያላትን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ በከፍተኛ አመራሮችና በሚኒስትሮች እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ የመረጃ ልውውጦችና የጋራ ኮሚሽን ስብሰባዎችን አከናውናለች። 12 የሚደርሱ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተፈራርማለች። ስምምነቶቹ በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ነው።

በሌላም በኩል አንዱ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ የሆነውን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን ከመተግበር አንጻር ፍርድ የተሰጣቸውና በእስር የሚገኙ ዜጎችን መቀያየር በሚቻልባቸውና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሀገራት ጋር መፈራረም ተችሏል። በዚህም በተለያዩ ሀገራት በስቃይና በእንግልት ውስጥ የቆዩ ዜጎች እፎይታ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ሌላው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚወሰደው ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነትን ማጽደቋ ነው። አዲሷ የተፋሰሱ ሀገር የወሰደችውን ርምጃ “ታሪካዊ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አድንቀዋል። ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን መጽደቁን፣ “ዲፕሎማሲያዊ እመርታ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፣ ይህም “በናይል ተፋሰስ ቀጣናዊ ትብብር ለማድረግ ባለን የጋራ ምኞት ጉልህ ርምጃ ነው፤” ብለዋል።

በሌላ መጠሪያው “የኢንቴቤ ስምምነት” እየተባለ የሚታወቀው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት፣ በደቡብ ሱዳን መጽደቁ፣ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን በቂ ድጋፍ የሚያስገኝ ነው።

ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ሆና የትብብር ማእቀፍ ስምምነቱን መፈረሟ፣ ስምምነቱ “ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችል ነው። ይህም ለዘመናት በጉዳዩ ላይ ስትደክም ለቆየችው ኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው።

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነትን አሥራ አንዱም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጋሩትን የናይል ወንዝ፣ “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለግብጽ እና ለሱዳን ብቻ ያከፋፍላሉ፤” በሚል የሚተቹትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሻር በአዲስ ለመተካት የሚያስችል ነው።

ስምምነቱ ለ11 ዓመታት ከዘለቀ ውይይት በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም. (በአውሮፓውያኑ 2010) ግንቦት ወር ላይ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ሲፈረም፣ ብሩንዲ በቀጣዩ ዓመት ስድስተኛ ሀገር ሆና ፈርማለች። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ከኬንያ በቀር አምስቱ ስምምነቱን በየሀገሮቻቸው ሲያጸድቁ፣ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛዋ የስምምነቱ አጽዳቂ ሀገር ሆናለች።

ይህንኑ አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) እንደዘገበው የናይል ተፋሰስ የውሃ ምንጭ የሆኑት የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት፣ የትብብር ማእቀፍ ስምምነቱ፥ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም” የሚለውን መርሕ የሚያሟላ መሆን እንዳለበት እንደሚገልጹና ስምምነቱ፥ “የውሃ ደህንነታችንንና ታሪካዊ ድርሻችንን ማረጋገጥ አለበት፤” የሚል አቋም ያላቸው ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው፣ እስከ አሁን ስምምነቱን አለመፈረማቸውን ዘግቧል።

የደቡብ ሱዳን ውሳኔ፣ ከ11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ የስምምነቱን አጽዳቂዎች ቁጥር ወደ ስድስት በማድረስ ወደ ተፈጻሚነት እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል። ይህም፣ ግብጽ እና ሱዳን፣ በቅኝ ግዛት ስምምነቶች መሠረት አለን የሚሉትን ታሪካዊ የውሃ መብት ጥያቄ የሚያስቀር ነው።

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ካገኘቻቸው ድሎች አንዱ ብሪክስን የሚመለከት ነው። ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነትን ማግኘቱን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከመሥራቾቹ ቀጥሎ በሁለተኛ ረድፍ ላይ የቡድኑ ባለድርሻ ሆናለች። ይህም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማሲና የምጣኔ ሀብታዊ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ኢትዮጵያ የዚህ ብሎክ አባል መሆኗ በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኙላት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚው የኢኮኖሚ ትብብር ነው። በዚህ የኢኮኖሚ ትብብር ኢንቨስትመንትን እና ንግድን ከማበረታት ጋር ተያይዞ በተለይ በአባል ሀገራት ዙሪያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ሪሶርስ እና ገበያ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ ብሪክስ አባል ሀገራት እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ እና የኢንቨስትመንት ሥራ ኢትዮጵያ ትልቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ትሆናለች ተብሎ ይታሰባል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ እንደመሆኗ መጠን የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ድጋፍ ይሆናታል። በተለይም ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ለሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብድርና እና ርዳታ ከማግኘት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው። የብሪክስ ማህበር የፈጠረው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሀብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለው ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል የሰፋ ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን፤ ሰፋፊ የግብርና ሥራዎችን፤ የመንገድ መሠረተ ልማቶችንና ኢንዱስትሪዎችን የምትገነባ ሀገር በመሆኗ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልጋታል። ለዚህ ግብዓት የሚሆን ድጋፍ እና ብድር ከእነዚህ ሀገራት ይገኛል ተብሎ ይታሰባል። እንደ ቻይና እና ሩስያ ከመሳሰሉ ሀገራትም የብድር ተቀናሽና ስረዛ ለማግኘትም ዕድል ይሰጣል።

ከምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ጎን ለጎንም ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲዊ ተሰሚነቷን የሚጨምረው ነው። በተለይም ኢትዮጵያ የምትከተለውን ከሁሉም ወገን ጋር አብሮ የመሥራት አካሄድ ለመተግበርና ከምዕራቡም ከምስራቁም ዓለም ጋር በወዳጅነት ለመዝለቅ የምትከተለውን ሚዛን የጠበቀ ግንኙነት ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችላት ነው።

ለኢትዮጵያም ሆነ ለአባል ሀገራቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የብሪክስ ስብስብ በ2016 በሩሲያ ሞስኮ ስበሰባውን አካሂዷል። ኢትዮጵያም በዚህ ከፍተኛ ጉባዔ ላይ የተሳተፈች ሲሆን ስብሰባውም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ኢኮኖሚ ትብብሯን ለማጠናከር የረዳት ነበር።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ እያስመዘገበችው ያለው ውጤት የሀገሪቱን ተሰሚነት ያሳደገና በርካታ ጥቅሞችንም ይዞ የመጣ ነው። በአራቱም አቅጣጫ ያለምንም አድሎና ወገናዊነት እያሳካችው ያለው የዲፕሎማሲ ድል ሀገሪቱ በርካታ ወዳጆችን እንድታፈራና በሪዮታለም የታጠረውን የዓለም አካሄድ ተሻግራ ጥቅሟን እንድታረጋግጥ አድርጓታል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You