ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ በአፍሪካ ቀዳሚዋ በዓለም ደረጃ ከፊተኞቹ መካከል ብትጠቀስም፣ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነችም ይታወቃል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች በምክንያት ይነሳሉ። የእንስሳት ሃብቱን ምርታማነት ለማሳደግ ከቁጥር ባሻገር ጤናማና ዘመናዊ የሆነ የእንስሳት እርባታ ሥርዓት ያለመዘርጋቱ በዋነኝነት ይገለጻል። ሥርዓቱ አሁንም ድረስ ኋላቀር በመሆኑ በእንስሳቱ ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳይጎለብት ሆኖ ቆይቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሃገሪቱ ለእንስሳት ሕክምና እና መድኃኒት በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች። የዚህ እንስሳት መድኃኒት ዋጋም ውድና ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት አሁንም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶና አርብቶ አደር ባሕላዊ የእንስሳት መድኃኒቶችን እንደሚጠቀም መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ባሕላዊ መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸውና ፍቱንነታቸው ምንም እንኳ በሳይንሳዊ መንገድ ባይረጋገጥም አርሶ አደሮቹም ሆነ አርብቶ አደሮች ዛሬም ድረስ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባሕላዊ መድኃኒቶችን ለእንስሳት ሕክምና በመጠቀም ሕንድና ቻይና የተሻለ ተሞክሮ አላቸው። እነዚህ ሃገራት ከውጭ የሚያስገቡትን የእንስሳት መድኃኒት በሃገራቸው ምርት ከመተካት አልፈው ለሌሎች ሃገራት በመሸጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ማግኘት እየቻሉም ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በርካታ መድኃኒታማ ዕፅዋቶች እንዲሁም ሃገር በቀል እውቀቶች ቢኖራትም፣ በዘመናዊ መንገድ በመፈተሽና እሴት በመጨመር ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሏ ከውጭ በሚገቡት ምርቶች ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል።
ሃገሪቱ በየጊዜው ለእንስሳት መድኃኒት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ መታደግ ያስችል ዘንድ በምርምር ዘርፍ ምን እየተሠራ ነው? ስንል በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑትን ቢክሲሳ ኡርጌን (ዶ/ር) ጠይቀናል። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ የሃገሪቱን የእንስሳት ሃብት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፤ ሃገራዊ የልማት ግቦችን መሠረት ያደረጉ ሰፋፊ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ለዚህም ይረዳው ዘንድ በዘርፉ በብሔራዊ ደረጃ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት፤ የምርት ጥራትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎችን በማዕከል፣ በአርሶ አደርና አርብቶ አደር ደረጃም እየተሠራ ነው።
በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሃገር በቀል እውቀቶችን መሠረት በማድረግ መድኃኒታማ ዕፅዋቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች መሠራታቸውን አስተባባሪው ይጠቅሳሉ። በማዕከሉ የሚከናወነው ምርምርም ሆነ የሚገኘው ውጤት ሃገሪቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት እያደረገች ላለችው ሁለንተናዊ ጥረት አስተዋፅዖ ማበርከት በሚያስችል መልኩ ታስበው የተቀረፁ ስለመሆናቸውም ያስረዳሉ።
ሃገር በቀል እውቀቶችና ዕፅዋቶች ላይ ምርምር በማድረግና ሥራ ላይ በማዋል በርካታ የዓለም ሃገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ቢክሲሳ (ዶ/ር) ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ግን በተሻለ መልኩ ሃገር በቀል እውቀትም ሆነ የዕፅዋት ሃብት ቢኖራትም በዘመናዊና ሳይንሳዊ መንገድ ባለመቀመሯ የእንስሳት ሃብቷን ከበሽታ ለመታደግ ያለመቻሏን ቁጭት ሊፈጥር ይገባል ይላሉ። ይህንን ታሪክ ለመቀየር በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት እነዚህን ሃገር በቀል እውቀቶች በመጠቀም ሃገሪቱ እያወጣች ያለችውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ኢንስቲትዩቱ በብሔራዊ ደረጃ ፕሮጀክት ቀርፆ ሰፊ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹እነዚህን ሃገር በቀል እውቀቶችንና፤ በተፈጥሮ ያገኘናቸውን መድኃኒታማ ዕፅዋቶችን የልማት ሥራዎች በቤተ-ሙከራ እንዲታገዙ በማድረግና፤ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሠራሮችን ማውጣት ችለናል›› ሲሉም ይገልጻሉ። በዋናነትም በተደጋጋሚ በሚከሰቱና አዲስ ሊከሰቱ በሚችሉ የእንስሳት በሽታዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ያብራራሉ። በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት በሽታችን በመለየት፣ ለመከላከልና ምላሽ በመስጠት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣትም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ።
አስተባባሪው እንዳስታወቁት፤ በጣም በስፋት ስንሠራበት የነበረው የኢትኖ ቨተርነሪ ምርምር ዘርፍ ነው፤ ይህም ባሕላዊ የእንስሳት መድኃኒቶች ላይ ያተኩራል፤ በተለይም በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የሚገኙ በማኅበረሰቡ በፈዋሽነታቸው የሚታወቁ መድኃኒታማ እፅዋቶችን በመሰብሰብ፤ በማባዛት፣ በቤተ ሙከራ ሳይንሳዊ ምርምር በማካሄድና እሴት በመጨመር ስድስት የተለያዩ መድኃኒቶችና ኬሚካሎችን ማውጣት ተችሏል።
ባሕላዊውን ከዘመናዊ ምርምር በማጣመር የተገኙት መድኃኒቶች በዋናነት ከዚህ ቀደም እንደሃገር በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎችን መከላከል የሚያስችሉ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል። ለአብነትም እንደ ፈንግል ያሉ የዶሮ በሽታዎችን፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የወተት ላሞች በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ። ‹‹በተለይ የእንስሳት የጡት፣ የቆዳ፣ የሳልና ጥጆችን የሚገድሉ በሽታዎችን የሚከላከሉ ናቸው›› ሲሉም ያስረዳሉ።
ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡት መድኃኒቶች በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ ባለመሆናቸው ምክንያት በተለያየ ጊዜ የእንስሳት መሞት በስፋት እንደሚያጋጥም የሚጠቅሱት ቢክሲሳ (ዶ/ር)፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ እነዚህ ከውጭ የሚገቡት መድኃኒቶችን የማግኘት ዕድሉ ቢኖረውም እንኳን ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትሉ በመሆናቸው ተመራጭ አይደሉም ሲሉም ያስገነዝባሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች የመድኃኒት መላመድ ችግሮችን የሚያስከትሉ ናቸው፤ በተጨማሪም በተለያዩ የእንስሳት ተዋፅዖ ውጤቶች ላይም የመድኃኒት ቅሪት እንዲኖርና በተጠቃሚዎች ጤና ላይ አሉታዊ ችግር ሊያመጡ ይችላሉ። እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመፍታት ረገድ ከሃገር በቀል ዕፅዋቶች የተገኙት መድኃኒቶችና እና ቴክኖሎጂዎች ውጤቶች ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው።
አስተባባሪው እነዚህ በምርምር መድኃኒቶች ከውጭ ይገቡ የነበሩትን ከመተካት ባለፈ፤ የውጭ ምንዛሪ በመታደግ ያላቸውን አበርክቶ ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹በብሔራዊ ደረጃ ከተሠሩት የምርምር ሥራዎች መካከል ለምሳሌ ብንጠቅስ ‹አፕሮሊየም› የሚባል የዶሮ መድኃኒት ኢትዮጵያ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ነው የምታስገባው፤ ሆኖም አሁን በተሠራው የምርምር ሥራ በሃገር በቀል ዕፅዋት መተካት ተችሏል። ይህም በመሆኑ ሃገሪቱ ለመድኃኒት ግዢ የምታወጣው ወጪ ይቀንሳል›› በማለት ይገልፃሉ። የእንስሳት ጡት በሽታን ለማከም ለሚያገለግለው አንድ መድኃኒት 30 ሺ ብር ወጪ እንደምታደርግ ጠቅሰው፤ ከአሉቬራ (ሬት) በሚሠራው መድኃኒት መጠቀም ቢቻል ግን ይህንን ወጪ ማስቀረት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
ኢንስቲትዩቱ ያወጣቸውን ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶች የማስፋፋት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመድኃኒት ፋብሪካዎች በተጨማሪ ለኬሚካል ኢንዱስትሪዎችም ዋነኛ ግብዓት በመሆናቸው በሃገር ደረጃ የማስፋፋት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት መድኃኒቶቹን ከውጭ የሚያስመጡ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ቢክሲሳ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት በርካታ የምርምር ሥራዎች እየሠራን ብንገኝም እነዚህን ቴክኖሎጂዎች አባዝቶ ለተጠቃሚዎች በአግባቡ ማድረስ ላይ ክፍተት አለ›› የሚሉት አስተባባሪው፤ በተለይም በአርብቶአደር አካባቢ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የሁሉም ርብርብ ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል። ‹‹ለምሳሌ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የገንዲ በሽታ በስፋት ያጋጥማል፤ ይህንን በሽታ በመከላከል ረገድ ሰፊ ምርምር እናደርጋለን። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ አርብቶ አደሮች የተለያዩ የእንስሳት ጤና ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ሆነዋል›› ይላሉ። ይሁንና ከዚህም በላቀ ቁጥር ተጠቃሚ ለማድረግ የሌሎች አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
በሌላ በኩልም ከሁለት ዓመታት በፊት በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሆነ የዶሮ ወረርሽኝ በሽታ ይከሰት እንደነበር ቢክሲሳ (ዶ/ር) አንስተው፤ እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቱትዩቱ በእነዚህ የዶሮ በሽታዎች መድኃኒቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ ሠርቷል። በተለይ በክትባት ላይ የማሻሻያ ሥራ በመሥራት አበረታች ውጤት ማግኘትም ተችሏል። በተጨማሪም ለኅብረተሰቡ ስለ ዶሮ በሽታና የክትባት አጠቃቀም በቂ እውቀት እንዲኖረው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተከናውኗል። ይህም በመሆኑ በሌማት ትሩፋቱም ሆነ በሌሎች የልማት መርሐ ግብሮች አማካኝነት የሚከናወኑ የዶሮ እርባታ ምርታማነት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማድረጉን፤ የእንቁላል ገበያም እንዲረጋጋም የዶሮ በሽታ መጠን እንዲቀንስ መደረጉ አስተዋፅዖው የላቀ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ኢንስቲትዩቱ ነባርና ባሕላዊው እውቀቶችን ከዘመናዊ የምርምር ሥራዎች ጋር በማጣመር፤ በመቀመር ያወጣቸው ስድስቱም አዳዲስ የእንስሳት መድኃኒቶች የተለያዩ የምርምር ሂደቶችን እንዲያልፉ ተደርገዋል። መድኃኒቶቹ ፈዋሽነታቸው በሳይንሳዊ መንገድ ተረጋግጦ የወጡ ሲሆን በተጨማሪም በእንስሳት ላይ ተሞክረው ተረጋግጧል። በተጨማሪም በሃገሪቱ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ምክረሃሳብ የተደገፉ ናቸው።
ከውጭ ከሚገቡት ጋር የንፅፅር ሥራም መሠራቱን ቢክሲሳ (ዶ/ር) አመልክተው፤ ‹‹እነዚህ መድኃኒቶች ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት ከኢንስቲትዩቱ ባሻገር በሚመለከታቸው ተቋማት በፍተሻ ተረጋግጠው የእውቅና ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ተደርጓል›› በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም መድኃኒቶችን የማባዛቱ ሥራ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
‹‹በተለይም እነዚህ የእኛ ግኝቶች ሃገሪቱ ለእንስሳት ሕክምና አሁን እያወጣች ያለችውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚታደግ በመሆኑ ወደ ፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ መሄድ አለባቸው። የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ይህንን ግብዓት ቢጠቀሙ ከውጭ የሚገባውን መተካት ይቻላል›› ሲሉም ያስገነዝባሉ። በሌላ በኩል መድኃኒታማ እፅዋቶችን የማባዛት ሥራም ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፍጠር ጠቅሰው፣ ወጣቶች እንዲደራጁና ከምርምር ማዕከሉ ጋር ትስስር በመፍጠር እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ ቢክሲሳ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ በተለይ የግሉ ዘርፍ በተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችን በመደገፍ የእንስሳት ሃብቱን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ሃገሪቱ ካላት ሰፊ የእንስሳት ሃብት በተጨባጭ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል። በተለይም ከውጭ የሚገባውን መድኃኒት በሃገር ውስጥ በመተካት በአሁኑ ወቅት ለእንስሳት መድኃኒት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳንም ይገባል። ይህ ሲሆን ደግሞ እንደሃገር ለተጀመረው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሁለንተናዊ ጥረት ስኬታማ ይሆናል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም