ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት፣ አርሶ አደሮች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች የልማት ኃይሎች ባካሄዷቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በቱሪዝሙ፣ በኃይል ልማትና በሌሎች ዘርፎች ተጠቃሽ ውጤቶች ታይተዋል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በተኪ ምርቶች፣ በቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ በዓባይ ግድብ ግንባታ የተከናወኑ ተግባሮችና የተገኙ ውጤቶች ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ስኬቶች የተመዘገቡት ደግሞ ልማቶቹ እንዲስተጓጎሉ የሚያደርጉ የውስጥና የውጭ ጫናዎች በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ሆነውም ነው፤ አንዳንዶቹ ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የደረሱ አይደሉም፤ በሌሎች ሀገሮች ላይም ጫና ያሳደሩት እንደ ኮቪድ 19 ያሉት ፈተናዎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሀገሮች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል።
ወረርሽኙን ተከትሎ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሥራ ላይ በዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ በሌሎች የበሽታው ስርጭት ባስከተላቸው ጫናዎች ሳቢያ ዜጎች ከሥራ ውጪ የሆኑበት፣ ተቋማት ሥራ ያቆሙበት ሁኔታ ወዘተ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሌላው ሀገሪቱን ለብዙ ቀውስ (ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) የዳረጋት ትልቅ ችግር መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና መንግሥት ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ብሎ አልነበረም›› ጦርነቱን ያካሂድ የነበረው። ጦርነቱን በድል ለመወጣት ይደረግ ከነበረው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ለልማቱ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ በማድረግም ጭምር እንደነበር ይታወሳል። በዚህም በኢኮኖሚውም ውጤታማ ለመሆን ብዙ ጥረት ተደርጓል።
ሀገሪቱ ለኢኮኖሚዋም ይህን ያህል ጥንቃቄ አርጋ ብትሠራም፣ ከዚያ ወሳኝ የጦርነት ወቅት እንዲሁም ከዓባይ ግድብ ግንባታ ጋር ተይይዞ የተደረጉባት ጫናዎች በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እንዲሁም የዓባይ ግድብ ግንባታዋን ለመቀጠል የምታደርጋቸውን ጥረቶች ለማሰናከል የተደረጉት ጫናዎች ለሀገሪቱ ልማት ከባድ ፈተናዎች ነበሩ።
የመንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ በጫና ለማንበርከክ የተደረገው ጥረት ብዙ ርቀት የተጓዘም ነበር። እንደ አሜሪካ ያሉት ሀገሮች አምባሳደሮቻቸውን ከኢትዮጵያ እስከ ማስወጣት ደርሰዋል፤ ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች ከቀረጥ ነፃ ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ገበያ ከሚያቀርቡበት /አጎአ/ ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንዳትሆን ተደርጓል። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና እርዳታ መስጠት ካቆሙ የቆዩ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ /እስከ አሁንም ድረስ/ በዚሁ አቋማቸው ጸንተዋል።
ጦርነቱ ያወደማቸው፣ ከሥራ ያስተጓጎላቸው ኢንዱስትሪዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፤ በግብርናው መስክም ቢሆን በማዳበሪያ ግዥ የተፈጠረው ጫናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የውጭ ምንዛሪው እያለም ማዳበሪያ መግዛት ፈታኝ እንደነበር ይታወሳል። ከኢትዮጵያ አትግዙ፤ ለኢትዮጵያ አትሽጡ የሚሉም ጫናዎች ብዙ ነበር።
ልማት በራስ አቅም ሊካሄድ ቢችልም ልማቱን ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ሊገኝባቸው የሚችልባቸው እንደ ብድርና ርዳታ ያሉት የፋይናንስ አማራጮች ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ ብድርን እንኳን ኢትዮጵያ ያደጉት ሀገሮች ጭምር በእጅጉ ይፈልጉታል፤ ብድር ለኢትዮጵያ የልማት ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
ይህ ብድርና ርዳታ የሚገኝባቸው አጋር ሀገሮችና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና እርዳታ ላለመስጠት መወሰናቸው ልማቱን በሆነ መልኩም ቢሆን አያንገራግጨውም ተብሎ አይታሰብም፤ አልተንገራገጨም ማለትም አይቻልም። የልማት አጋሮችን፣ ሠላምን፣ የውጭ ገበያ ማጣት፣ ወዘተ በልማት ላይ ችግር እንደሚፈጥር ይታወቃል።
እርምጃዎቹን መሠረት በማድረግ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ እንዳያገኙ፣ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ለመዱት መዳረሻቸው እንዳይሄዱ በማዕቀብ ጣዮች ወይም ጫና ፈጣሪዎች በኩል ብዙ ጥረት ተደርጓል። ይህቺ ሀገር የኢንዱስትሪ ግብዓት ብቻ ሳይሆን፤ ለሰው ልጅ በእጅጉ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ጭምር እንዳታገኝም ተደርጋም እንደነበር የሚታወስ ሀቅ ነው።
በሀገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገራቸው የሄዱበት፣ ሌሎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይመጡ የሆነበት ሁኔታም ነበር። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም እንዲሁ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ያቆሙበት ሁኔታ መታየቱ ይታወቃል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ያጠፉት የሰው ሕይወት፣ ያጎደሉት አካል፣ የፈጠሩት የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ያወደሙት ሀብት፣ ለድንጉጡ ኢንቨስትመንት /በተለይ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት/ ከፍተኛ ፈተናዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ማንም አይስተውም። በጦርነቱ ከወደሙ፣ ከተዘረፉ ኢንዱስትሪዎች፣ ሥራቸው ከተስተጓጎለ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱም ሆነ ሌሎች ኢንቨስተሮች ምን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም።
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ የቆየች ሀገር ልማቷን ለማስቀጠል የምትጠይቀውን ብድርና ርዳታ የሚከለክሉ የፋይናንስ ተቋማትና እነሱን የሚዘውሩ ያደጉ ሀገሮች ብድርና ርዳታ ማስከልከላቸው አንሶ ሀገሪቱ ቀደም ሲል የተበደረችውን ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በዚያ ክፉ ቀን እንድትከፍል ጫና ተደርጎባታል። ጫና ብቻም ሳይሆን እንድትከፍል ተደርጋለች።
የውጭ ኃይሎች ይህን ሁሉ ያደረጉት የኢትዮጵያ መንግሥት ጫና ሲበዛበት በቀደድንለት ቦይ ይፈሳል ብለው በማሰብ ነው። መንግሥትን በጫና ብዛት በማንበርከክ የፈለጉትን ሊፈጸሙ አስበው ነበር። ይህ ግን ሊሆን አይችልም ! ነበርና አልሆነም።
ሀገሪቱና ልጆቿ ፈተና አጠንክሯቸው እንጂ አላንበረከካቸውም፡፣ መለኛ አርጓቸው፤ ነገሮችም ጫና ፈጣሪዎች እንዳሰቡትና እንዳቀዱት ሳይሆኑ ሀገሪቱና ልጆቿ እንዳሰቡትና እንዳቀዱት ቀጠሉ። ሀገሪቱም በብዙ ፈተና ሠርታ ካገኘችው ሀብት ትርጉም ያለው የብድር መጠን ስትከፍል ቆይታለች፤ እየከፈለችም ትገኛለች።
የለውጡ መንግሥት ባጋጠሙት ብዙ ፈተናዎች ሳይፈታና ሳይረታ፣ ይልቁኑም ችግርን እንደ መውጫ በማድረግ ያሉትን የሀገር ውስጥ ሀብቶች አሟጦ በመጠቀም ጫና ፈጣሪዎቹ እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዳሰቡት፣ እንደተገበሩትም ሆኖ በፈተና ውስጥ አያሌ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።
በሀገራችን አንድ አባባል አለ፤ ‹‹ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል›› የሚል። ምንም እንኳን መንግሥትን ለማንበርከክ በሚል በሀገሪቱ ላይ በርካታ ጫናዎችን ያሳደሩት ሀገሮች /በጥሬው ትርጉሙ/ ለእኛ ጎረቤት ሀገሮች ባይሆኑም፣ ቅርበታቸው፣ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው፣ ቀደም ሲል ከሀገሪቱ ጋር የነበራቸው እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ሲታሰብ የጎረቤት ያህል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሀገሮች ናቸው ሊባሉ ይችላሉ። እነዚህ ሀገሮች/በአብዛኛው ምዕራባውያን ናቸው፤ ለነገሩ በዚያ ክፉ ቀን ዜጎቻቸውን ያስወጡ የአፍሪካ ሀገሮችም ነበሩ/የጎረቤት ያህል ለኢትዮጵያ ቅርብ ናቸው።
ቴክኖሎጂ ዓለምን አንድ መንደር ባደረገበት ዘመን ጎረቤት የማይሆን ሀገር የለም። እናም እነዚያ ሀገሮች በድንበር ባይዋሰኗትም ጎረቤት ሀገሮች ናቸው።
ከለውጡ በፊት አንድ ወቅት ላይ ኩዌቶች ላንጋኖ አካባቢ አንድ የቱሪስት ከተማ /12 ሺ ሕዝብ ሊያኖር የሚችል/ ሊገነቡ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ነበር፤ በሥነሥርዓቱ ላይም የወቅቱን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ተገኝተዋል። /ዜናውን በወቅቱ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው የተከታተልኩት/ ንግግር ካደረጉት መካከል አንድ የኩዌቱ ሰው ኢትዮጵያና ኩዌት ጎረቤት ሀገሮች ናቸው ሲሉ መናገራቸውን አስታውሳለሁ፤ እኔም እንዴት ሆኖ እያልኩ ሳሰላስል ለእዚህ አባባላቸው ማብራሪያ ሲሰጡ ከአዲስ አበባ ኩዌት ያለውን የአራት ሰዓት የበራራ ርቀት የጉርብትና ያህል ወስደው ነው። ትክክል ነው፤ ያስኬዳል። እኔም ያኔ ያንን ሁሉ ጫና ያሳደሩብን ሀገሮችን እንደ ጎረቤት መውሰዴ አንድም ለእዚህ ነው።
እናም ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል እንደተባለው፤ እነዚህ ሀገሮችና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሀገሪቱ ላይ የፈጠሩት ጫና ሀገሪቱ ችግርን እንደ ልማት መሣሪያ፣ የዜጎችን አቅም እንደ ዋነኛ የልማት መሣሪያ አድርጋ እንድትጠቀም አድርጓል። ያንን ሁሉ ተጠቅማም ነው ባለፉት ዓመታት ተጠቃሽ የልማት ስኬቶችን ማጣጣም ውስጥ የገባችው። ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድልን ተጠቃሚ እንዳትሆን መከልከሏን ተከትሎ የኢንዱስትሪ ውጤት የሆኑ ምርቶችን ሊቀበሉ የሚችሉ ሌሎች ሀገሮችን ማማተር ውስጥ ተገብቷል፤ ቻይና የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ውጤቶች ለመቀበል ፍላጎት ያሳየችውም ይህንኑ ተከትሎ ነበር፤፤
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ሀገሪቱ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በብዙ ፈተና ውስጥ ሆናም አያሌ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሏን ማስታወቃቸው ይታወሳል። እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያውያን ችግርን እንደ መውጫ ተጠቅመው፣ የዜጎችን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በተከናወኑ ተግባሮች የተመዘገቡ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ዕዳ ያጎበጠው ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት ኮሜርሻል ብድር አልወሰደችም፤ አንድ ዶላር ኮሜርሻል ብድር ላለፉት ስድስት ዓመታት አልወሰደችም። በአንጻሩ ግን የአበዳሪ ተቋማት ዕዳ ወደ ልጆቿ መሸጋገር የለበትም በሚል ጽኑ እምነት ብድሯን ስትከፍል ቆይታለች፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ እዳ ወደ 17 ነጥብ አምስት በመቶ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ /ከጂዲፒዋ/ ዝቅ ብሏል። ይሄ ትልቅ ድልና ትልቅ ዜና ነው ሲሉ መግለጻቸው ይታወቃል።
ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች በአማካይ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታቸው /ጂዲፒ/ ስልሳ በመቶ ዕዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዛም በላይ ዕዳ ያለባቸው ሀገራት እንዳሉም አስታውቀዋል። ዕዳን ወደ 17 በመቶ ማውረድ መቻል እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አመልክተው፣ በሚቀጥሉት ዓመታት በሚደረጉ ርብርቦች ደግሞ ዕዳው ከ10 በመቶ በታች መውረድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ከፍላለች፤ የከፈለችው ዕዳ ደግሞ በቀደመው መንግሥት ወቅት የተወሰደ ብድር ነው፤ ‹‹ወደ ልጆቻችን ዕዳ እንዳይሻገር አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ ችለናል። ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ግን ይጠበቅብናል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከተከማቸ ብድር ውስጥ ትርጉም ያለውን ያህል ዕዳ መክፈል መቻል አንድ ትልቅ ስኬት ነው፤ ምንም ሳይበደሩ ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር መክፈል መቻል ደግሞ በራሱ ሌላ ትልቅ ስኬት ነው። የለውጡ መንግሥትም ያደረገው ይህንኑ ነው።
ጫና ሊያሳድሩብን የፈለጉና በብዙ መልኩም ጫና ያደረጉብን ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳያውቁት ጠንካራ ሀገር ሆነን እንድንወጣ አድርገውናል፤ በተኪ ምርት ላይ በተከናወነው ተግባር የተገኘው ውጤትም ሌላ ጫና የወለደው ስኬት ነው።
እንደሚታወቀው የሀገራችን የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ሲታይ ቀደም ሲልም አንስቶ ከፍተኛ ክፍተት ይስተዋልበታል፤ የገቢ ንግዱ ሚዛን ከወጪ ንግዱ በእጅጉ ይሰፋል። ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚጠይቁ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ስናስገባ፣ ወደ ውጪ ከምንልካቸው ምርቶች የምናገኘው የውጪ ምንዛሪ ግን ከዚህ በእጅጉ ያነሰ ነው።
ሀገራችን በርካታ ምርቶችን ለውጪ ገበያ ብታቀርብም የግብርና ምርቶችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ግን በእጅጉ ትታወቃለች። የግብርና ምርቶቹም ብዙ ዓይነት ናቸው። ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት፣ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ ጫት፣ ወዘተ በስፋት ትልካለች። እንደ ወርቅ፣ ኦፓል ያሉ ማዕድናትን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ አንዳንድ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ደግሞ ለጎረቤት ሀገሮች ትልካለች። በዚህ ሁሉ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።
ለውጭ ገበያ የምትልካቸውን ምርቶች መጠንና ጥራት ለማሳደግ፣ የምርቶቹ መዳረሻ ሀገሮችን ለማስፋት፣ የምርቶቹን አይነትም ለማብዛት እንዲሁም ጥራታቸውን ለማስጠበቅም እንዲሁ በትኩረት ሠርታለች።
ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረትም ብዙ ርቀት ተጉዛ ውጤቶችን ማየት ጀምራለች። ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ማምረት ጀምራለች ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሠራች ናት። የቢራ ገብስ ከውጪ ማስመጣት ትታለች። ስንዴ በሀገር በስፋት በማምረትም ስንዴ ከውጪ ከመግዛት ወጥታለች። በነዳጅ ጥገኛ ሆኖ የኖረው የትራንስፖርት ዘርፏ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ መጠቀምም ገብቷል። ይህም ነዳጅ ከውጪ ለማምጣት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለመቀነስ የበኩሉን ሚና ይወጣል።
በአጠቃላይ ግብርናን ጨምሮ በኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች አንዳንድ ምርቶች በተደረገ የገቢ ምርት መተካት /ኢምፖርት ሰብስቲትውሽን/ ሥራ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል።
በተኪ ምርቶች ላይ የተከናወነውን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ ስንዴ አንዱ ተኪ ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹በስንዴ ላይ በተከናወነው ተግባር ብዙ ብር አስቀርተናል›› ብለዋል። ‹‹የፋብሪካ ምርቶች 40 በመቶ ደርሰናል። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን መጠቀም ጀምረናል። ይሄ እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ ነገር ነው።›› ሲሉም ተደምጠዋል።
በተኪ ምርት ላይ እየተከናወነ ያለው ተግባር በንግድ ሚዛኑ ያለውን ክፍተት ለማጠበብ አስተዋፅዖ እንዳለው በእጅጉ ይታመናል። በተኪ ምርት ላይ የታየው አፈጻጸም ወደ 50፣ 60፣ 70 እያደገ ከሄደ፣ ገቢ ምርትን ከተካን፣ የወጪ ምርትን /ኤክስፖርት/ ካሳደግን በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ክፍተት /ትሬድ ዴፊሴት/ እየቀነሰ ከሄደ ጤናማ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት በእጅጉ ያግዛል ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት ።
የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሲቆም ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የርዳታ አቅርቦት ማቆማቸው ይታወሳል፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት በሀገር ውስጥ አቅም የርዳታ አቅርቦት ለመሙላት ርብርብ አድርጎ የተሳካ ሥራ የሠራበት ሁኔታም ሌላው የውጪ ኃይሎች ጫና የወለዳቸው መፍትሔዎቻችንና ስኬቶቻችን ናቸው።
ለዚህ ሁሉ ስኬት ለመድረስ በየዘርፉ ብዙ ተሠርቷል፤ ለልማት አንድ አቅም ተደርጎ የሚታበው የውጭ ብድርና እርዳታ በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ እንዲፋታ ቢደረግም፣ መንግሥት የሀገር ውስጥ አቅምን አሟጦ በመጠቀም ለውጥ አምጥቷል። ጫና ሊያሳደሩብን የሞከሩ ኃይሎች ቢበረቱብንም፣ የልማት አቅማችንን አይተን በራሳችን አቅም እንድንሠራ አማራጭ መንገድ እንድንፈልግ አበርትተውናል። ለእዚህም ነው ‹‹ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል›› ያልነው።
ኃይሉ ሣሕለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም