የዛምቢያ ፀረ ሙስና ባለሥልጣናት በሙስና ተጠርጥረው ከኃላፊነታቸው ተባረሩ

ሙስናን እንዲከላከሉ የተሾሙት የዛምቢያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የቦርድ አባላት ራሳቸው ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል በሚል በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ተባረሩ። የመንግሥታዊው የፀረ ሙስና ተቋም የቦርድ አባላት ቢያስተባብሉም የሙስና ክስ መቀረቡን ተከትሎ ነው የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቺሌማ ለየት ያለ ውሳኔ በማሳለፍ ሁሉንም ከሥልጣን ያሰናበቱት።

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ይፋ የሆነው የሀገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዋና ኃላፊ ቶማስ ሻማካምባ በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላ ነው። ባለሥልጣኑ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ይልቀቁ ወይም በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ከኃላፊነታቸው ይባረሩ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

ከሥልጣን የለቀቁት ኮሚሽነሩ እና የተቋሙ ዋና ዐቃቤ ሕግ ማርሻል ሙቼንዴ ጉቦ በመቀበል የተከሰሱ ሲሆን፤ ሁሉቱም ግን የቀረበባቸውን ክስ ሐሰት ሲሉ አስተባብለዋል።የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሂቺሌማ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ባለሥልጣናት በሙስና በተከሰሱ የቀድሞው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

አሁን በፀረ ሙስና ኃላፊዎች ላይ የቀረበው ክስም ከዛምቢያ የቀድሞ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል። በዚህም ምርመራ እየተደረገባቸው ላሉት የቀድሞ ፖለቲከኞች ምርመራቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲያገኙ ለማስቻል ገንዘብ ተቀብለዋል ተብሏል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጥቆማ የሰጠው ቀድሞ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ የቦርድ አባል የነበረው ኦብሪን ካባ የተባለ ግለሰብ እንደሆነ ተገልጿል።ግለሰቡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጽሁፍ ይፋ እንዳደረገው “በወጡ ዘገባዎች መሠረት የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ በሙስና ከተዘፈቁ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከፍትህ እና ከተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ የሚያስችል በሕግ ትርጉም አልባ የሆነ ስምምነት አድርጓል” በማለት ገልጾ ነበር።

ግለሰቡ ጨምሮም በቀደመው የሀገሪቱ አስተዳደር ወቅት የነበረው “ከመከሰስ ነጻ የሚያደርገው ስምምነት” የአሁኑ አስተዳደር “ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት የሌለው በሚያስመስል ሁኔታ” ጥቅም ላይ እየዋለ ነው በሚልም ተችቷል። ኦብሪን ካባ ተበላሽቷል የሚለውን የሀገሪቱን የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለማስተካከል አራት የቦርድ አባላትን ማባረር ብቻ “በቂ አይደለም” በማለት ሙሉ ተቋሙ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።

የግለሰቡን ክስ ተከትሎ የተቋሙ ዋና ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ሙቼንዴ የስም ማጥፋት ክስ መሥርተውበታል። የኮሚሽኑ ሌሎች አባላትም ተመሳሳይ ክስ በኦብሪን ካባ ላይ ሊመሠርቱ ይችላሉ እየተባለ ነው። በፀረ ሙስና ኮሚሽኑ መሪዎች ላይ የቀረበውን ክስ ተከትሎ ከዛምቢያው ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ የተቋሙ የቦርድ አባላት መባረር አስፈለጊ የሆነው “ወሳኝ የሆነውን የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ኃላፊነት ለማደስ ነው” ብሏል።

የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ቶማስ ሻማካምባ ከሥልጣን መልቀቃቸው ይፋ የተደረገውም ከፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት በወጣ መግለጫ ሲሆን፤ ይህም ባለሥልጣኑ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀው ሳይሆን ተባረው ነው የሚል ግምትን ፈጥሯል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You