የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት በተገኙበት በይፋ ተመርቋል። ፕሮጀክቱ በቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎች እየተመዘገቡ ካሉ ውጤታማ ሥራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በመዳረሻ ልማት ዙሪያ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን እየተመለከትን ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን የተፈጥሮ መስህቦችን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ መዳረሻዎችን (ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ፣ የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጨምሮ) ከማስተዋወቅ አንፃር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጎርጎራም የዚሁ አካል ነው። ጎርጎራ ፊትም በቱሪስት መስህብነት ቢታወቅም፣ ይህን እምቅ አቅሙን በመመልከት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ቱሪስቶችን በእጅጉ ሊስብ በሚያስችል መልኩ ግንባታ ተካሂዶለታል፡፡ እንደታሰበውም የቱሪስት ፍሰቱን በእጅጉ መጨመር እንደሚችል ይጠበቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ገበታ ለሀገር” ውጥን እንደ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ እና ጎርጎራ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና በአካባቢያቸው የሚገኙ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን አጉልተው በማሳየት ረገድ ከፍተኛ እመርታን አስመዝግቧል። እነዚህ ጥረቶች ለዘላቂነት እና ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ በመሰጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ፣ ሥራ ለመፍጠር እና በዙሪያው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ ያለሙ ናቸው።
‹‹ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሥራዎችን በመደገፍ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል›› የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መልእክት፤ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) በሚያደርገው ቀጥተኛ አስተዋፅኦም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል።
በኢትዮጵያም ቱሪዝም መንግሥት ላስጀመረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የማዕዘን ድንጋይ ሲሆን፤ ከአምስቱ ቁልፍ ምሰሶዎች አንዱ ነው። እንደ “ገበታ ለሀገር” ያሉ ሥራዎች የቱሪዝም ዘርፉን ለማዳበር፣ ብዙ ጎብኚዎችን ለመሳብ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት፣ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፤ መዳረሻዎችን ለማልማት እና ለማሻሻል ታልመው በሥራ ላይ በመዋል ላይ ይገኛሉ።
ከጽህፈት ቤቱ መልእክት እንደምንረዳው፤ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ምረቃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አራት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎችን በ “ገበታ ለሀገር” ውጥን ስር ለማልማት ያሳዩት ቁርጠኝነት ተጨማሪ ማሳያ ሲሆን፤ በ2012 ቃል በገቡት መሰረት ገንብተው ተጠናቆ ማስረከባቸውንም ያመላክታል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ራዕያቸው ተስፋፍቶ በግንባታ ላይ ያሉ ሰባት ተጨማሪ መዳረሻዎችን ለማልማት ያቀደ “ገበታ ለትውልድ” የተሰኘ አዲስ ፕሮ ጀክትም አስጀምረዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በተመረቀበት ወቅት ስለ ፕሮጀክቱ ስኬታማነት የተናገሩት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ፤ የገበታ ለሀገር አካል የሆኑትና በክልሉ እየተገነቡ ያሉት ፕሮጀክቶች ለማህበረሰቡ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልፀዋል። ወሳኝ በሆነ መልኩ የቱሪዝም ፍሰትን የሚጨምሩ፣ ለአካባቢው የልማት ትስስር የስበት ማእከል ሆነው የሚያገለግሉ፣ በትልቁ የሥራ እድል የፈጠሩ ለሕዝቡ የተበረከቱ ታላቅ ገፀ በረከቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በግል ባለሀብቱ ዘንድ ለቱሪዝም ልማት አቅም የሆኑ የኢንቨስትመንት ተግባራትን በማከናወን አካባቢውን ለማልማት የሚያስችል መነሳሳትን ፈጥሯል። ይህ ፕሮጀክት በኮንስትራክሽንና በቱሪዝም ልማት ላይ ለተሰማሩ አልሚዎች በአጠቃላይ በፕሮጀክት አስተዳደር በተለይም ደግሞ በጥራት ሥራ አመራር ረገድ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው። ከዚህም በላይ በጣና ሀይቅ ዳርቻ አካባቢ በምን አይነት የልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ፣ተግባራቱንም በምን ያህል የጥራት ደረጃ ማከናወን እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከፍተኛ የሥራ ደረጃ አስቀምጧል። ከሁሉም በላይ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት የመንግሥትን የሥራ ፈጣሪነት ጠባይና ፍላጎት በግልፅ ያመላከተ ነው።
አቶ በቀለ ኡማ የቱሪዝም ባለሙያ ናቸው። በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህር፣ አማካሪ፣ ተመራማሪ እንዲሁም የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤትነት ሆነው በዘርፉ ለዓመታት ሰርተዋል። የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት መመረቅን አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ጎርጎራንና አካባቢውን በአስጎብኚነት በሚሰሩበት ወቅት የመመልከት አጋጣሚው ነበራቸው። ይህ ስፍራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ውስጥ ከታቀፉት መካከል በመሆኑና በኢኮ ሪዞርትነት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመዳረሻ ልማት ተሰርቶለት በመመረቁ ተደስተዋል።
በአጠቃላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በፕሮጀክቱ (በገበታ ለሀገር) ታቅፈው የተሰሩትና እየተሰሩ የሚገኙት ሁሉ አበረታች ውጤት የታየባቸው መሆናቸውን አቶ በቀለ ይናገራሉ። ‹‹በመንግሥት ደረጃ ታቅደው እየተሰሩ ያሉ ትላልቅ የመዳረሻ ልማቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው›› የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያውና መምህሩ፤ በግል ባለሀብቱ አቅም የማይሰሩ የመብራት፣ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማትን ጨምሮ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚጠይቁ ግንባታዎች በመንግሥት መከናወናቸው አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ዘርፉ የሚፈለገውን እድገት እንዲያመጣ መሰረት የሚጥል መሆኑን ያስረዳሉ።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም በመንግሥት አቅም ከተሠሩ ፕሮጀክቶች መሀል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በመስህብ ቦታው ላይ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ቱር ኦፕሬተሮች ጎብኚዎች እንዲመለከቱት የሚወስዱበት ተመራጭ መስህብ መሆኑን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪዎች በጥራትና በሚፈለገው ደረጃ የተሟሉ እንዳልነበሩ አንስተው፤ የጎርጎራ ኢኮ ቱሪዝም መገንባቱ ይህንን በላቀ ጥራት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹የጎርጎራ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን በዋናነት ለክልሉም ሆነ በአካባቢው ለሚኖር ማህበረሰብ ጠቀሜታ አለው›› የሚሉት አቶ በቀለ፤ በተለይ ማህበረሰቡን ያቀፈ የኢኮ-ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖር በማሰብ ግንባታው መከናወኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደሚኖሩት ይጠቁማሉ። ከዚህ ውስጥ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ (የመብራት፣ ውሃና ሌሎችንም ጨምሮ) የመሆን እድል ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰዋል።
አንድ መዳረሻ ሲለማ ማህበረሰቡ በጋራ እንዲያድግ በር ይከፍታል የሚሉት አቶ በቀለ ኡማ፤ የቱሪዝም መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብም ማህበረሰቡን በመሰረተ ልማት፣ እንዲሁም በሥራ እድል ፈጠራ (በሪዞርቱ በየእርከኑ የሚቀጠሩ ባለሙያዎችን) ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ። የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም ይህንን መስፈርት እንደሚያሟላ ነው ያመለከቱት። በተለይ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ነዋሪው የምግብ ጥሬ እቃ እንዲያቀርብ፣ ባህላዊ ቁሶችን፣ በራሱ በማህበረሰቡ የተዘጋጁ ባህላዊ ምግቦችን፣ የሚከራዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ለመዝናኛ ጉዞ የሚያገለግሉ እንደ ፈረስ ያሉ መጓጓዣዎችን በማቅረብ እድል የሚከፍት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በሚገኝበት አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች መዳረሻውን እንደራሳቸው እንዲመለከቱት ቀዳሚ ተጠቃሚዎች መሆን ይገባቸዋል የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያውና መምህሩ፤ ይህ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መዳረሻው ዘላቂ እንዲሆንና የሚፈለገውን አገልግሎት ለጎብኚዎች እንዲሰጥ ተግባራዊነቱ ሊረጋገጥ ይገባል ይላሉ። ይህ አካሄድ ለጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ልዩ ልዩ መስህብ ስፍራዎች እየተሰሩ ባሉ መዳረሻዎች ላይ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባውና የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ የአካባቢው ማህበረሰብ መሆን እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በሰው ሰራሽ እንዲሁም በባህል በርካታ የሚጎበኙ ቦታዎች አሏት የሚሉት አቶ በቀለ፤ እነዚህን ሀብቶች የገበያ ስልት በመንደፍ፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው ታዋቂ ሰዎች እና ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በመስራት እንደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት (ኬንያ፣ ኡጋንዳ) ተፅእኖ ፈጣሪ በሆኑ መገናኛ ብዙኃን ላይ ማስተዋወቅ እንደሚገባ መክረዋል። በተለይ በቅርቡ ታዋቂ ሰዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት መጀመሩና የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ መዳረሻዎችን ማስጎብኘቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ መስህቦቿን እንድታስተዋውቅ እንደሚያግዛት ይናገራሉ። በቅርቡ የተመረቀው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም ከዚህ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የመዳረሻ ልማት ሥራ በጎርጎራና ሌሎች አካባቢዎች መሰራቱ ተገቢ መሆኑን የሚያነሱት አቶ በቀለ ኡማ፣ ይህ ጥረት ይበልጡኑ ስኬታማ እንዲሆን ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች መኖራቸውንም ይገልፃሉ። ከእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የቱሪዝም ባለሙያዎች መስህቦቹን እንዲመሩት ማድረግና ተገቢውን ባለሙያ በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ የሚለው አንደኛው መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹ኢኮ ቱሪዝም የማህበረሰቡን ሀብት ለማህበረሰቡ ማዋል ነው›› የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያው፣ ይህ እንደ ጎርጎራ ባሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣትም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ላይ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል። በተጨማሪም በጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትና በሌሎችም ፕሮጀክቶች (በቅርቡ በገበታ ለሀገር የተገነቡ) በግል ባለሀብቶች (በአካባቢው ተወላጆች በማደራጀትም) እንዲተዳደሩና የተሻለ አገልግሎት በዘላቂነት መስጠት እንዲችሉ መመቻቸት ይኖርበታል። መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ባሻገር መንግሥት እነዚህን ፕሮጀክቶች የማስተዳደር ኃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ ማስረከብ ይገባዋል በማለትም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
እንደ መውጫ
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ትኩረትና የጥራት ደረጃ ግንባታው ሲከናወን ቆይቶ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቋል። ከወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ፣ ከሀላላ ኬላ እንዲሁም ከጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ ቀጥሎ በገበታ ለአገር ፕጀክቶች ውስጥ ተካትተው ግንባታቸው ከተጠናቀቁ መዳረሻዎች ተርታም ተቀላቅሏል።
የቱሪስት መስህብ እንደነበረች የሚነገርላት ጎርጎራ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰላም በመጥፋቱ የጎብኚው ቁጥር እየተቀዛቀዘ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ከሚስተዋለው የሰላም መቀዛቀዝ ሲወጣ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ፕሮጀክት ከባህር ዳር እና ጎንደር እንዲሁም በዙሪያው ካሉ የቱሪስት መስህቦች ጋር ተሳስሮ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ጠቀሜታ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም