ቻይናውያን ሀገራቸውን ‹‹ቹንጓዋ› ሲሉ ይጠሯታል ይባላል፡፡ በቹንጓዋ ወይም በቻይና የአንድ ሰባት ቆይታ ያደረግነው ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በተቀጣጠርነው መሰረት እሁድ ማለዳ ተነስተናል፡፡ እለቱ በቤጂንግ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን የምንጎበኝበት ነው፡፡ በታላቁ የቻይና ግንብ አሀዱ እንላለን፡፡ይህን ታሪካዊ ስፍራ እንደምንጎበኝ አስጎብኚያችን አንዲ ቀደም ብሎ በነገረን ወቅት ሁሉንም የቻይና ግንብ ከመነሻው እስከ መድረሻ የምንጎበኝ አርገን ያሰብን ነበርን፡፡እሱ ግን የቻይናን ግንብ ጎብኝቶ ለመጨረስ ወራትን እንደሚወሰድና እኛ የምንጎበኘውም የግንቡን ትንሽ ክፍል ብቻ መሆኑን ነገረን።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ፤ታላቁ የቻይና ግንብ የተገነባው የቻይና መንግስትን እና ነገስታትን በወቅቱ ከነበሩ ተስፋፊ ወራሪዎች ለመታደግ ነው፡፡ይህ ከሀገሪቱ ምስራቅ ክፍል አንስቶ በምእራብ ክፍል አድርጎ እስከ ሰሜን የሚዘልቀው ግንብ ከድንጋይ ፣ ከሸክላ፣ከእንጨትና ሌሎች የተለያዩ ግብአቶች የተገነባ ነው ፡፡
ታላቁ ቻይና ግንብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይገኛል፡፡8 ሺ ኪሎ ሜትርም ይረዝማል፡፡ አብዛኛው ክፍል የተገነባው ግን በሚንግ ዘመነ መንግስት ከ1368 እስከ 1644 ባሉት ዘመናት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው፤የቤጂንግ ቅዝቃዜ ኮርመት አርጎን የቆየ ቢሆንም መኪና ውስጥ ከገባን በኋላ ፈታ ማለት ጀምረናል፡፡ጉዟችንን ወደ ቤጂንግ ምእራባዊ አቅጣጫ አርገናል፡፡
በርቀት ከፊታችን በግራም በቀኝም አቅጣጫ የተራራ ሰንሰለት ማየት ጀመርን፡፡የቻይና ታላቁ ግንብ መገኛም እነዚህን የተራራ ሰንሰለቶች ይዞ መሆኑን አስጎብኚያችን ነገረን፡፡
ወደ ተራራው ሰንሰለት በቀረብን ቁጥር የቻይና የህንጻ አሰራር መገለጫ የሆኑ ቤቶችን ማየት ጀመርን፡፡ከመንደሩ ጉያ ስር ገባን፡፡ጎብኚዎች ይገባሉ፤ይወጣሉ፡፡ ወቅቱ በጣም ቀዝቀዛ በመሆኑ ሁሉም ወፋፍራም ጃኬት ለብሰዋል፤የጃኬቶቻቸውን ኮፍያም አጥልቀዋል፡፡እጅ በኪስ ነው፡፡እኛ አዲስ አበቤዎች ግን ቅዝቃዜ እንደሚገጥመን መረጃው ቢደርሰንም ፣ብዙም የእነሱን ያህል አልተጠነቀቅንም፡፡የቆዳ ቀለማችንና ቋንቋችን እንዳለ ሆኖ ይህ ብቻ ጸጉረ ልውጥ ያደርገናል፡፡በርካታ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው ቆመዋል፤ፎቶ ግራፍ አንሺዎች፣ምስል ሻጮች በብዛት የቅርሳ ቅርስ መሸጫዎች በአካባቢው በብዛት ይታያሉ፡፡
በግንቡ የተወሰነ ርቀት የጥበቃ ማማ የሚመስሉ የቻይና መገለጫ በሆኑ የህንጻ ጥበቦች የተገነቡ ቤቶች ከፍ ብለው ይታያሉ፡፡ በእርግጥም የጥንቱ የጥበቃ ማማዎች ናቸው፡፡እዚህ አካባቢ ላይ አረፍ ማለት የፈለገ አረፍ ይላል፡፡
አዛውንቶች፣ወጣቶች፣ጎልማሶች በጉብኝቱ ላይ ይታያሉ፡፡አልፎ አልፎ የተለያዩ ሀገሮች ዜጎች ቢታዩም አብዛኞቹ ጎብኚዎች ግን ቻይናውያን ናቸው፡፡ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች በስፍራው የተገኙ ኢትዮጵያውያንም አጋጥመውናል፡፡በሀገራችን በእለተ እሁድ በዚህ ሰዓት ብዙ ሰው የሚታየው ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ሰዓቱ አራት ሰዓት አካባቢ ቢሆንም በአካባቢው ያለው የጎብኚዎች እንቅስቃሴ እሁድ ጠዋት ቤተክርስቲያን አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴ አስታወሰኝ፡፡
ሁኔታው ‹‹ቹንጓውያን›› ለታሪካቸው ምን ያህል ፍቅር እንዳላቸው ያመለክታል፡፡ አንዳንዶች አካባቢውን ምንአልባትም የአካል እንቅስቃሴ ማድረጊያ እና ራስን እንደመፈተሻ ሳይቆጥሩትም አልቀረም ስል አሰብኩ ፡፤
አስፈላጊው ፍተሻ እና ክፍያ ተፈጽሞ ጉብኝት ወደ ምናደርግበት በስተቀኝ አቅጣጫ ወዳለው ክንፍ ተሰባሰብን፡፡አስጎብኚያችን አንዲ ሰብሰብ አረገን ፡፡ በስተቀኝ ወዳለው የግንቡ ክፍል እያሳየን መጨረሻው ደርሶ ለመመለስ አንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ ሰጥቶን የምንገናኝበትን ስፍራም አሳውቆን ተለየን፤ እኛም ጉዞውን ጀመርን፡፡
ከግንቡ ረጅም እድሜ ማስቆጠር አንጻር በግንቡ ስር የሚያልፈው የፍጥነት መንገድና የባቡር ሀዲድ መቼ እና እንዴት ተገንብተው ይሆን ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ለነገሩ ለቻይናውያን ምን ይሳናቸዋል፡፡መንገዱን እና ሀዲዱን ገንብተው ግንቡን ወደ ቀድሞ ይዞታው መልሰውት ሊሆን ይችላል ስል አሰብኩ ፡፡አካባቢው ጥንታዊነት እና ቴክኖሎጂ የተጣጣሙበት መሆኑን ተረዳሁ፡፡
ደረጃውን መውጣት ቀጥለናል፡፡ የእግር ጉዞ አድርጎ እንዲሁም ብዙ ደረጃ ወጥቶ ለማያውቅ በእርግጥም ፈተና ነው፡፡በተለይ ትንሹንም ትልቁንም መንገድ በተሸከርካሪ ላደረገ ከባድ ነው፡፡
በጀመሩት ፍጥነት መጓዝ አይታሰብም፡፡ የበረታው ቀድሟል፤ያልበረታው እየቆጠረ ይጓዛል፤አረፍ ስል ትንፋሼን ዋጥ ለማድረግ ስሞክር ከግንቡ ግራና ቀኝ ወደ ውጪ እንዲሁም ሽቅብ ወደ ግንቡና ተራራው በተቃራኒ አቅጣጫ ወደአለው የግንቡ አካል ተመለከትኩ፡፡ ወደ ግራና ቀኝ ሲታይ አካባቢው ገደላማ ነው፡፡
አንዳንዱ አካባቢ ላይ ያለው የግንቡ ደረጃ አጭር ስለሆነ በቀላሉ መውጣት ይቻላል፡፡
የመልሱ ጉዞ ይቀላል ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ቁልቁለት የራሱ የቤት ስራ አለው፡፡ እርግጥ ለሚቀል ይቀል ይሆናል፡፡ ገና ቁልቁለቱን ሲመለከቱ ሀሞታቸው የሚፈስ ጥቂት አይደሉም፡፡ ከሚታሰበውም በላይ በጣም ቁልቁለት ያለባቸው ስፍራዎች ያጋጥማሉ፡፡ደረጃዎቹ አጫጭር በሆኑባቸው ስፍራዎች ፈጠን ፈጠን ብሎ መውረድ ይቻላል ደረጃዎቹ ከፍ ያሉበት ቦታ ላይ ግን ተጠንቅቆ መውረድ የግድ ነው፤ቋንጃ እና ሳምባ ይፈተናሉ፤ልብም እንዲሁ፡፡ ትንሽ ቢያደናቅፍ፣የሆነ ነገር ቢጠልፍ መድረሻው እንጦርጦስ ነው፡፡አቅምን ፈትሾ ከግንቡ ግድግዳ ጋር የተያያዙትን ብረቶች ደገፍ እያሉ መውረድ የግድ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡
አንዳንዶች ወርቅማ ሜዳሊያ አጥልቀው ሲመለሱ ይታያሉ፡፡ ይህ ያነሳሳቸው አቅማቸውን አሰባስበው የቀረውን ለመውጣት ይጣጣራሉ፤ወጥተው የጨረሱም አጋጥመ ውኛል፡፡ ግንቡን በሙሉ የወጣ መጨረሻው ማማ ላይ ከሚገኙ የቱሪስት መደብሮች ደረጃውን ወጥቶ ማጠናቀቁን የሚያመለክት ወርቃማ ሜዳሊያ አጥልቆ ይመለሳል፡፡ በሜዳልያው ላይም ስሙን ማጻፍ ይችላል፤ለእነዚህ አገልግሎቶች ግን 30 ዩዋን መክፈል ይኖርበታል፡፡ የቻይና ግንብ ጉብኝት ይህን ታሪካዊ መስህብ መጎበኘት ያስቻለ ከመሆኑ በተጨማሪ የቻይናውያንን የሀገር ውስጥ ቱሪስትነት በሚገባ አመልክቶኛል፡፡
በታያናንሜን አደባባይና ፎርቢድን ሲቲ ባደረግነው ጉብኝትም ይህንኑ የቻይናውያን የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ፍቅር ያመላከተ ነው፡፡ወደ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተጠጋን ስንሄድም ያረጋገጥነውም ይህንኑ ነው፡፡ የህዝቡ ብዛት እየጨመረ መጣ፡፡ከአደባባዩ መግቢያ ስንደርስም ቻይናውያን እነዚህን ስፍራዎች ለመጎብኘት ተሰልፈዋል፡፡
አስጎብኚያችን ወደ አንዱ ሰልፍ ይዞን አመራ፤ሰልፉ ረዘመበት መሰለኝ ቆየት አለና ደግሞ ፓስፓርታችንን እንድናዘጋጅ ነግሮን እንድንከተለው አደረገ፡፡ እንዳለውም ፓስፓርታችንን አሳይተን ገባን፡፡ ወደ አደባባዩ እየዘለቅን መጣን፤የሰላሌ ሜዳ ማለት ነው፡፤
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ታያናሜን አደባባይ ‹‹የገነት የሰላም በር›› በመባል ይታወቃል፤በሚንግ ዳይናስቲ ዘመን በ1415 የተገነባው የቱሪስት መስህብ ‹‹የንጉሱ ከተማ መግቢያ በር›› ም ይባላል፡፡አደባባዩ በ1651 ዲዛይን ተደርጎ መገንባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ዘመን አንስቶም አምስት ጊዜ ስፋቱ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡
በአደባባዩ የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ ይውለበለባል፡፡ ከበስተጀርባውም ቻይናን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ፕሬዚዳንት ማኦ ሴቱንግ መታሰቢያ ፣ በአደባባዩ ግራን ቀኝ የቻይና ብሄራዊ ሙዚየም እና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ግዙፍ ህንጻዎች ይታያሉ፡፡
አስጎብኚያችን እንደገለጸልን፤አደባባዩ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡በአደባባዩ ዘወትር የሰንደቅ አላማ መስቀል ሥነ ሥርአት እንደሚካሄድ አንዲ ነገረን፡፡ይህም በቻይናውያን ዘንድ ልዩ ስፍራ አለው፡፤ ባንዲራ በሚሰቀልበትና በሚወርድበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ መንገዶች ከአስር ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ እንደሚዘጉ በየአቅጣጫው የሚገኙ ቻይናውያን በሙሉ ቆመው የባንዲራውን መስቀልና መውረድ ሥነ ሥርአት እንደሚታደሙ አንዲ ገለጸልን፡፡
የቻይናውያንን የመጎብኘት ፍቅር በቀጣዩ የጉዞ መዳረሻችን ‹‹ፎርቢድን ሲቲ››ም ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ዘ ፎርቢድን ሲቲ ከታያናሜን አደባባይ በስተጀርባ ነው የሚገኘው፡፤ወደ ፎርቢድን ሲቲ የገነባነው በአደባባዩ ስር ለእግረኞች በተገነባ ሰፊ የመሬት ውስጥ የእግረኞች መንገድ አርገን ነው፡፡
‹‹የተከለከለው ከተማ ››በመባል የሚታወቀው ይህ ታሪካዊ ስፍራ የቱሪስት መስህብ ከመደረጉ በፊት የጥንት የቻይና ነገስታት ፣ቤተሰቦቻቸውና ባለሟሎቻቸው ብቻ ይሰሩበትና ይኖሩበት ነበር፡፡ ይህ ቢሄዱት ቢሄዱት የሚያልቅ ከተማ ፣በቻይና ጥንታዊ የህንጻ ጥበብ የተሰሩ በርካታ ቤተመንግስቶች፣ህንጻዎች ፣አደባባዮች፣ የተካተቱበት ነው፡፡
ቤጂንግን በአረንጓዴ ስፍራዋ ያደነቅኳትን ያህል እዚህ አካባቢ ላይ አንድም አረንጓዴ ስፍራ አልተመለከትኩምና ለምን የሚል ጥያቄ አጫረብኝ፡፡ ዛፍ አይደለም ዛፍ ነበረ የሚያሰኝ አንድም አሻራም የለም፡፡ለምን ስል አስጎብኚያችንን ጠየቅሁት፡፡ህንጻዎቹ የተሰሩት ከእንጨት፣ ከድንጋይ ከአፍርና ከመሳሰሉት እንደመሆኑ ለደህንነታቸው ሲባል ለደህንንታቸው ስጋት በከተማው ዛፍ እንዲኖር አይፈለግም ነበር ሲል መለሰልኝ፡፡
ያመረኝን ዛፍ ያዩሁት በእዚሁ የተከለከለ ከተማ መጨረሻ አካባቢ የንግስታቱ የመናፈሻ ስፍራ በመባል በሚታወቀው አካባቢ ነው፤ በዚህም እጅግ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ የተጠማዘዙ ዛፎች ይታያሉ፡፡
የፎርቢድን ሲቲ ጉብኝታችንን አጠናቀናል፤ወደ መጣንበት የተመለስነው ግን በገባንበት በር አርገን አይደለም፡፡ ያ ቢሆን አዳር በሉት፡፡ጉብኝታችንን ባጠናቀቅንበት በር ከፎርቢድን ሲቲ የወጣነው፤ በመውጫችንም ትልቅ የውሃ አካል አየሁ፡፡ወንዝ ነው ወይ ስል አንዲን ጠየቅሁት፡፡ ‹‹ዴድ ሪቨር›› ነው ሲል መለሰልኝ፡፡ ሙት ወንዝ ማለት ምን ማለት ነው ስል አሰብኩ፡፡
ቆይቶ እንደተረዳሁት ታዲያ ሞት ወንዝ ፎርቢድን ሲቲን ከጥቃት ለመከላከል ሲባል የተገነባ የውሃ አካል ነው፡፡ አቤት የጥንታውያኑ ቻይናውያን የመከላከያ መንገዶች ስል አሰብኩ፡፡ የእለቱ ጉብኝታችንም በዘመናዊቷ ቤጂንግ ውስጥ የሚገኘውን የአሁኑን የቱሪስት መዳረሻ የጥንቱን ፎርቢድን ሲቲ የከተማ ውስጥ ከተማ በማድረግ ቢያበቃም፣ ቸንጓዋ ታሪካዊ ስፍራዎቿን ምን ያህል እየተንከባከበች እንደምትገኝ ፣ቹንጓዋውያንም የመስህብ ስፍራዎች የመጎብኘት ባህላቸው ምን ያህል የጎለበተ እንደሆነ በመረዳትም ጭምር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል