ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት፤ መልከ ብዙነቷ ደግሞ ውበትም ኅብረትም ሆኖ የሚገለጥ እምቅ አቅሟ የሚታገዝ ነው:: ኢትዮጵያ መልኳ ኅብራዊ፣ አቅሟም ኅብረብሔራዊ አንድነቷ ነው:: ይሄ መልክና አቅም ሲዳመር ከሚሰጠው ከፍ ያለ ሀገራዊ ገጽ ባሻገር፤ ተፈጥሮ የቸራት ሀብቷ፣ ሕዝቦቿ ከሚበጁላት እሴቶቿ ጋር ተዳምረው ቢገለጹ ዓለም ተመልክቶ የማይጠግበው የኢትዮጵያን ድምቀት ይፈጥራል::
ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ የገናና ታሪክ ባለቤት ናት፤ ኢትዮጵያ የብዝኃ ማንነት ምድር ናት፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋ አብዝቶ የተቸራት የምድር ገነት ናት፤ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿ የጥበብ ዐሻራ ጎልቶ ያረፈባት የዘርፈ ብዙ ጥበብና ኪነት ሰገነት ናት፤… በጥቅሉ ኢትዮጵያ ተፈጥሮም፣ ዜጎቿም አሳምረው ለከፍታዋ እንዲሆኑ የለገሷትን ዘርፈ ብዙ በረከቶች በጉያዋ አቅፋ የያዘች፤ ግን እነዚህን ለአደባባይ ሳታበቃ ዘመናትን የኖረች ሀገር ናት::
ይሄ የፈካና የደመቀ ገጽ ታዲያ ከዚህ በላይ ተሸፍኖ መዝለቅ አይኖርበትም:: ምክንያቱም በመገለጡ ውስጥ ሊገኝ የሚገባው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ፤ ባለመገለጡ ብቻ እየቀረ፣ ሀገርም ሕዝብም ሳይጠቀሙበት እየባከነ ነው:: የለውጥ ማግስት አመራርም በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይሄንን እውነት እና ውበት ወደመግለጥ ነው የገቡት::
ይሄን እውነትና ውበት በመግለጥ ሂደት ደግሞ የ”ገበታ”ን ተምሳሌትነት ነው የተጠቀሙት:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ተሟልቶላት የቀረበች ገበታ ናት:: ይሄንን ገበታ በልኩ ተገንዝቦ ለተመጋቢው በሚማርክ መልኩ ማዘጋጀት የባለገበታው ሥራ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሲረከቡ የተገነዘቡት ይሄንኑ ሙሉ ሆና የተዘጋጀች ገበታ መሆኗን ነው::
ዋና ሥራ ያደረጉትም፣ ያዩትን ማሳየት፤ የተረዱትን ማስረዳት፤ ከፍ ሲልም በጥቂቱ ገልጦ በማሳየት ለብዙ ተግባር ማነሳሳትን ነው:: እናም ይሄን መንገድ በ”ገበታ” አምሳል ይዘው፤ ዜጎችን ወደ ገበታው ጋበዙ:: አንድ ብለው ሲጋበዙም፣ ገበታውን በሸገር ላይ አኑረው “ገበታ ለሸገር” ብለው ጋበዙ:: እናም በሸገር ገበታ መንገድ አንድነት ፓርክን፣ ወዳጅነት አደባባይን፣ እንጦጦ ፓርክን እና ሌሎችንም የአዲስ አበባን ውበት ገልጠው፤ አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብና አበባ መሆኗን አሳዩ::
ይሄ የሸገር ገበታ የገለጠው እውነት ታዲያ ሥራውን ከፍ አድርጎ ወደ ሀገር ማሳደግ እንደሚገባ አስገነዘበ:: እናም ገበታውን ከፍ አድርገው ሀገር ላይ በማኖር “ገበታ ለሀገር” ብለው ግብዣ አቀረቡ:: በሸገር የተገለጠውን ውበት ያየ ኢትዮጵያዊም በሀገሩ ይሄው እንዲገለጥ በመሻቱ፤ የጎርጎራን፣ የኮይሻን እና የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክቶችን ገበታ ገለጠ:: በዚህም ሀገር ጉያዋ አያሌ ውበቶችን፤ እልፍ በረከቶችን አቅፋ መያዟ ተገለጠ::
ሸገርን አስቀድሞ፣ በሀገር አስከትሎ የተጀመረው የውበት ገለጣ መንገድ፤ ለትውልድ የሚተርፍና የሚተላለፍ ሥራን ሠርቶ በከፍታ መገለጥ ስላለበትም፤ ገበታው ከሸገርና ሀገር አልፎ ለትውልድ እንዲሆን በማሰብ “ገበታ ለትውልድ” ተዘረጋ:: በዚህም ትውልድ ተመልክቶ ሊነሳሳባቸው እና ተቀብሎም ሊያሰፋቸው የሚያስችሉ ሰባት የትውልድ ገበታዎች ተወጥነው ወደ ተግባር ገቡ::
ከሸገር ተነስተው፣ በሀገር ተራምደው ወደ ትውልድ የተሸጋገሩት እነዚህ ሁሉ የ”ገበታ” ፕሮጀክቶች ታዲያ ከፕሮጀክትነት ያለፈ ፋይዳ ያላቸው ናቸው:: ይሄም በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በልኩ ተረድቶ ማልማትና መጠበቅ እንደሚገባ ያስገነዘቡ መሆናቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ሳይገለጡ የኖሩ ግን በመጠኑ የመግለጥ ሥራ ቢከናወንባቸው ኢትዮጵያን ታይታም ተጎብኝታም የማትጠገብ የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ እንደሚቻል ያሳዩም ሆነዋል::
ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ በ”ገበታ ለሸገር” የተከናወኑ የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ እና የእንጦጦ ፓርክን የመሳሰሉት፤ በቆሻሻ ተሸፍነው ውበታቸው ሳይሆን መጥፎ ገጻቸው ይታይ የነበሩ ቦታዎች፤ በትንሽ ግን በውጤታማ ሥራ ፍጹም የተለየ እና ማራኪ ገጽታን ተላብሰው ለብዙዎች የዓይንም፣ የልብም፣ የአዕምሮም ምግብና እረፍት መሆን ችለዋል::
በ”ገበታ ለሀገር” የተገለጡት እነ ጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ወንጪ ደንዲ ፕሮጀክቶችም፣ ማንም ልብ ያላላቸው ድንቅ ስፍራዎች፤ የሚያስተውል መሪ እና ሠሪ ሲያገኙ ለሀገር አልፈው ለዓለም የዓይን ማረፊያ፤ የቱሪዝም ስበት ማዕከል መሆን የቻሉበትን እውነት ተመልክተናል:: በዚህ መልኩ የተጀመሩት የ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶችም ከጅምራቸው ከዚህ ልቀው እንደሚገለጡ በሶፍዑመር ዋሻ እና ሌሎችም ላይ ምልክታቸውን አይተናል::
እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ ሀገር ምን አላት የሚለውን አውጥቶ በማሳየት ውስጥ፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎቿን በማልማት እና በአካባቢያቸው የሚገኙ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶቿን አጉልቶ በማሳየት ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው:: ቱሪዝም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሥራዎችን በመደገፍ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል:: ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በሚያደርገው ቀጥተኛ አስተዋፅኦም ጉልህ ነው::
በመሆኑም የ“ገበታ” ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የተደበቁ ውበቶች አውጥቶ በመግለጥ የቱሪዝም ዘርፉን ለማዳበር፣ ብዙ ጎብኝዎችን ለመሳብ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፤ መዳረሻዎችን ለማልማት እና ለማሻሻል ታልሞ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ናቸው:: በዚህ ረገድ ሀገር ያላትን አቅም ለይቶ ለማልማት እና ለመግለጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያሳዩት ቁርጠኝነት እጅጉን የሚደነቅም፤ እውቅና ሊቸረው የሚገባውም ነው::
ከዚህ ባሻገር የ”ገበታ” ግብዣዎችን ተቀብለው የገበታው ተቋዳሽ እና የሀገርን ገጽ አድምቆ በመግለጽ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ዜጎች፤ ከሸገር እስከ ሀገር፣ በኋላም ለትውልድ በሚተርፈው ተግባር ላይ የሚጠበቅባቸውን አበርክተዋል እና ሊመሰገኑም፤ እውቅና ሊቸሩም ይገባል:: ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት የሀገርን ገጽ ገላጭ ተግባራት የአንድ ሰሞንና አካል ተግባር ሆነው ሊቀሩ ስለማይገባቸው፤ በ”ገበታ” ፕሮጀክቶች የታየው የኢትዮጵያ እምቅ ሃብትና ውበት የመግለጥ ተግባር ሳይቆራረጥ በሁሉም ቦታ፤ በሁሉም አካል ሊከወን ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም