ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሯን አድንቀዋል:: የአድናቆታቸው ምክንያት ደግሞ በዚህ ሁሉ ወቀሳና ጫና ውስጥ ሆነው በትጋት በመሥራታቸው ነው:: ተቋሙ ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ ወቀሳ ሲወርድበት የቆየ ነው:: በተለይም ተገልጋዩ ደግሞ በስፋት ሲያማርር ስንሰማው የቆየነው ነው:: የምርምር በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆኖ መሥራት ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጥንካሬ ይጠይቃል::
ዳሩ ግን፤ አድናቆቱ ሕዝባዊ የሚሆነው አገልግሎቱ በተግባር ተቀላጥፎ ሲታይ ነው:: አንድ ቀላል ማሳያ እንውሰድ:: ተቋሙ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ፤ ከሚቀጥለው ዓመት (ከመስከረም በኋላ መሆኑ ነው) ጀምሮ የቤት ለቤት የፓስፖርት አገልግሎት ይሰጣል ብሏል:: የብዙ ሰዎች አስተያየት ግን ‹‹ቤት ለቤት መስጠቱ ቀርቶ እዚያው መጥተን አገልግሎቱን ባገኘን!›› የሚል ነው:: በሌላ በኩል የቤት ለቤት አገልግሎቱ የሚሰጠው ምናልባትም ለሀብታምና ለታዋቂ ሰዎች ስለሚሆን ‹‹ይሄማ ድሮም ስትሠሩበት የነበረ ነው›› የሚል ነው:: ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለተራ ዜጎች የቤት ለቤት አገልግሎት መስጠት የሚቻል አይመስልም፤ ከሆነም እሰየው ነው!
የትኛውም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ቢሰጥ ሁሉም በአንድ ድምፅ እንደማያመሰግንና እንደማያደንቅ ግልጽ ነው:: ፀጉር መሰንጠቅ የሚቀናው ብዙ ወገን እንዳለ ይታወቃል:: ከብዙ ቀልጣፋ አገልግሎት ውስጥ አንዲት ስህተትን አጉልተው የሚያጮሁ መኖሩ አያከራክርም::
ዳሩ ግን፤ ወቀሳው በጣም ከተደጋገመ፣ የብዙ ሰዎች አጀንዳ ከሆነ፣ የአሠራሩ አታካችነትና ተስፋ አስቆራጭነት የሚታይ የሚሰማ ከሆነ… ጉልህ ችግር አለ ማለት ነው:: ምንም እንኳን በአንድ ድምፅ እንዲሆን ባይጠበቅም በብዙዎች የሚደነቁ ተቋማትንና የሥራ ኃላፊዎችን እናውቃለን:: ለምሳሌ፤ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ብዙ ጊዜ በቀልድም ሆነ በቁም ነገር ስማቸው የሚጠቀሰው በአድናቆት ነው:: በነገራችን ላይ የሕዝብን ትርታ ማዳመጥ በትልልቅ መድረኮችና በትልልቅ ሰዎች (ፖለቲከኞች፣ ባለሥልጣናትና ምሑራን) አይደለም:: የሕዝብ ትርታ የሚለካው ተራ በሚመስሉ ነገሮች ነው:: የድሮ ነገሥታት ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ይሉ ነበር ይባላል:: በአስተዳደራቸው ላይ ያለውን አስተያየት የሚወስዱት ከታዋቂ ሰዎችና ባለሥልጣናት አይደለም:: ከታች ያለው ምን ይላል? በሚል ነው::
እስኪ በዚህኛው ዘመን ዓውድም ልብ እንበለው! ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞችና ምሑራን ገለልተኞች አይሆኑም፤ የሆነ ጫና ይኖርባቸዋል:: ለምሳሌ፤ የኢትዮ ቴሌኮምን አገልግሎት ከተራ ዜጎች እና ከፖለቲከኞች አስተያየት ብናሰባስብበት አድናቆት የሚበዛው ከተራ ዜጎች ነው:: በተቃራኒው አንዳንድ ተቋማት ደግሞ የበለጠ ቅሬታና ምሬት የሚበዛባቸው በተራ ዜጎች ነው:: ስለዚህ አንድ ተቋም ወይም የሥራ ኃላፊው ሊደነቁ የሚችሉት የአብዛኛውን ወገን ፍላጎት ካሟሉ ነው ማለት ነው:: በዚህ መሠረት ካየነው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፍተኛ ወቀሳ የሚበዛበት ተቋም ነው፤ በተጠቃሚው ዘንድ የመደነቅ ደረጃ ላይ አልደረሰም:: በአገልግሎቱ አሰልቺነት ምክንያት ‹‹ወይ ይቺ አገር!›› የሚል ይበዛል::
እዚህ ላይ ግን አንድ ልብ መባል ያለበት ወሳኝ ነጥብ አለ፤ ይህ ነጥብ ራሴው በዓይኔ አይቼ የታዘብኩት ነው:: አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች ማለት ይቻላል ከገጠር አካባቢዎች የሚመጡ ናቸው:: ለሰልፍና ለወረፋ አዲስ ናቸው:: ለእንዲህ አይነት ወከባና ግርግር እንግዳ ናቸው:: እነርሱ ከሚኖሩበት የአሠራር ዘይቤ ጋር አይሄድም:: ሰልፍና ግርግር የከተማ ባሕል ሆኗል:: ስለዚህ በጣም ስልቹ ይሆናሉ ማለት ነው:: ለእንደዚያ አይነት አሠራር እንግዳ ስለሚሆኑ ግራ መጋባት ይበዛል:: በዚህም ምክንያት ግርግሩን የበለጠ ያባብሰዋል፤ አገልግሎቱን ያራዝመዋል::
ለምሳሌ፤ የመረጃ ማጣሪያ ቦታው ላይ ብዙ ጭቅጭቅ አለ:: አንዳንዶቹ መጠይቁ ግራ ይገባቸዋል:: በዚያ ላይ አገልግሎቱን የሚሰጡት የተቋሙ አንዳንድ ሠራተኞች በሰዎቹ ዓውድ የማስረዳት ትዕግስት የላቸውም:: ያመናጭቋቸዋል፤ በአንድ ጊዜ የሚረዱት ይመስላቸዋል:: እንደዚያ አይነት ነገር አዲስ እንደሚሆንባቸው አይገምቱም:: ልክ የእነርሱን ያህል የሚያውቁት አስመስለው ነው የሚጠይቋቸው:: ከሥራው ጫና አንፃር ትዕግስት እንደሚፈታተን ግልጽ ነው:: ሰው ናቸውና ይሰላቻሉ፤ ዳሩ ግን የሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ፣ የሕዝባቸውን ባሕልና ልማድ ማወቅና ማክበር አለባቸው::
ዐሻራ የሚሰጥበት ቦታ ላይ የአንድ ሰው ብቻ እስከ ግማሽ ሰዓት ሊያቆይ ይችላል:: በተለይም በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ወንዶች፣ የቤት ውስጥ ሥራ የሚበዛባቸው ሴቶች እጃቸው ለዐሻራ እያስቸገራቸው መሰለኝ ብዙ ሲቆዩ አስተውያለሁ:: ስለዚህ ተቋሙ ለእንዲህ አይነት ሁኔታዎች መፍትሔ የሚሆን አሠራር ሊኖረው ይገባል:: መስኮት ላይ ያሉት አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችም እንዲህ አይነት ሰዎችን በማሳሳቅ፣ በማዋዛትና በማረጋጋት ማስፈረም እንጂ ጭራሽ በመቆጣትና ‹‹ኤጭ!›› በማለት ሲሆን እጃቸውን ያልባቸውና የባሰውን ለዐሻራ አስቸጋሪ ይሆናል::
አንድ አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ከተሜ ወደ ገጠር ሄደ እንበል:: የተፈታታ ሞፈርና ቀንበር እያሳዩ ‹‹በል ይህን ገጣጥመህ፣ በሮችን ጠምደህ እረስ!›› ቢባል ብላችሁ አስቡት:: የሚይዘው የሚጨብጠው ነው የሚጠፋበት፤ አርሶ አይበላም ማለት ነው:: ይህ ከተሜ የዚያ ታታሪ ገበሬ ጥገኛ ነው:: ልክ እንደዚህ ሁሉ የገጠሩ ነዋሪም ጥገኛ የሚሆንባቸው ነገሮች አሉት ማለት ነው:: ተቋሙ ደግሞ የሥራው ባሕሪ ሆኖ አገልግሎቱን የሚሰጠው ከዜጎች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ነው::
በነገራችን ላይ አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ናቸው፣ የተማሩ ናቸው የሚባሉት ይብሳሉ:: ለቴክኖሎጂ ቅርብ ያልሆኑት ቢያንስ አይጨቃጨቁም፣ አይጣሉም:: የተማረ የሚባለው ደግሞ ይሳደባል፣ ይጣላል፣ ካላጭበረበርኩ ይላል:: በአጠቃላይ የተቋሙን አሠራር አሰልቺ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የእኛ የዜጎች ቀልጣፋ አለመሆንም ጭምር ነው::
ይህ ብቻውን ግን ተቋሙን ከወቀሳ አያድነውም:: ምክንያቱም ሁሉም ተቋማት ሕዝባዊ አገልግሎት ነው የሚሰጡት፤ ሁሉም ደንበኛ ያስተናግዳሉ:: ምንም እንኳን ሌሎች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ነው የሚሰጡ ባይባልም፣ አንድ ተቋም የበለጠ ወቀሳ ሲበዛበት ግን ‹‹ምን ቢሆን ነው? ችግሩ የት ጋ ነው?›› ብሎ ማጥናት አለበት:: በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበፊቱ አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመስጠት መሻሻል ታይቷል:: ቀደም ሲል የወሰዱ ሰዎች ‹‹ይህን ያህል ጊዜ ነው የቆየብኝ›› ሲሉ፤ በቅርቡ የወሰዱ ደግሞ ‹‹ኧረ እኔ በሁለት ወር ነው ‹ና ውሰድ!› ያሉኝ›› ያሉ ሰምቻለሁ:: ሕዝቡ ጥሩ አገልግሎት ካገኘ ለማመስገን ችግር የለበትም:: ችግሩ ግን ወከባና ትርምሱ አሁንም ያለ መሆኑ ነው:: በቦታው ላይ ላለው ትርምስና ወከባ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ መፍትሔ መደረግ አለበት:: ከላይ ያለው አሠራር የቱንም ያህል ትኩረት ቢደረግበት ከታች ያለው ቀልጣፋ ካልሆነ ከወቀሳ አይድንም:: ምክንያቱም አብዛኛው ዜጋ የሚያየው ከታች ያለውን ነው:: ስለዚህ ዐሻራ መሥጠት ላይ ያለው ወከባና ግርግር አሁንም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል! ያኔ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይሆኑ ሕዝቡ ያደንቃል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም