‹‹ሁሉም ‘መድኃኒቴ ደኅንነቴ’ ብሎ መንቀሳቀስ አለበት›› – ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ – የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የመድኃኒት ደኅንነት ክትትልና የሕክምና ሙከራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ

መድኃኒት የሰው ልጆችን ጨምሮ ሕይወት ላላቸው ፍጡራን በሽታን ለመፈወስ፣ ለመከላከል፣ ለመመርመርና እንዲሁም ሕመምን ለመቀነስ የምንጠቀምበት ንጥረ ነገር ወይም የንጥረ ነገር ውሕድ ነው:: በተለይ የሰውን በሽታ፣ የተዛባ ወይም ጤነኛ ያልሆነ አካላዊ ወይም አእምሯዊ ሁኔታ ወይም ተያያዥ ምልክቶችን ለመመርመር፣ ለማከም፣ ለማስታገስ ወይም ለመከላከል፤ ለማስተካከልና ወደ ነበረበት ለመመለስ ብሎም ለማሻሻል የሚያስችል ነው:: ከዚህ ባሻገር ማንኛውንም የሰውነትን ተፈጥሯዊ ተግባር በጠቃሚ መልኩ ለመለወጥ፤ የሚውል ንጥረ-ነገር ወይም የንጥረ-ነገሮች ውሕድ ነው::

የዘርፉ ምሑራን ሲገልጹ እንደሚሰማውም፣ ሁሉም መድኃኒቶች ማለት ይቻላል የፈዋሽነታቸውን ያህል በጤና ላይ የሚያደርሱት የጎንዮሽ ጉዳትም ቀላል የማይባል ነው:: በተለይም የሐኪም ትዕዛዝን በመከተል መድኃኒቶቹን መጠቀም ካልተቻለ ጉዳቱ በጣም አሳሳቢ ሊሆን ይችላል:: በአብዛኛው መድኃኒትን በመውሰድ የሚከተሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደ አይነታቸው፣ ብዛታቸውና የተጠቃሚው የእድሜ፣ የፆታና የሰውነት ክብደት የሚወሰን ሲሆን ሌሎች የጤና እክሎችም ካሉ ከእነዚህ ጋር በተደራቢነት ሊነሱ ይችላሉ::

ስለ መድኃኒት ደህንነት ሲነሳ የዶክተር ቭላድሜር ለፓኪን ስም ሁሌም አብሮ ይታወሳል:: ዶክተሩ እ.ኤ.አ. በ2005 ጉዳዩን በሚመለከት ያነሱት ሃሳብም ሁሌም እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል:: እርሳቸው በወቅቱ ያነሱት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነው:: ‹‹በበሽታ መሞት አንዳንድ ጊዜ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን በመድኃኒት ደኅንነት ወይንም ጎጂ ክስተት ምክንያት መሞት ተቀባይነት የለውም››::

ይህ አስተያየት ሁለት አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ አነጋጋሪ ነው:: በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት ደኅንነት አንገብጋቢ አጀንዳና ልዩ ትኩረትን የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል:: ኢትዮጵያም ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትን በመስጠት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች::

በዛሬው የጤና ዓምዳችንም የአገሪቱን የመድኃኒት ደኅንነትና ቁጥጥር ወይንም ባሕሪያት ምንነት፣ ሪፖርት አደራረግና ውጤቶች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ኃላፊነት በሚመለከት ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የመድኃኒት ደኅንነት ክትትልና የሕክምና ሙከራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ከወይዘሮ አስናቀች አለሙ ያቀረብነውን ጥያቄና የሰጡንን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል::

አዲስ ዘመን፡- ከመድኃኒቶች ባሕሪይ አንጻር ምን መሠረታዊ መርሕ አለ?

ወይዘሮ አስናቀች፡- መድኃኒት ስንል ንጥረ-ነገር ወይም የንጥረ-ነገሮች ውሕድ ሲደመር መረጃ ነው:: ይህ ማለትም መድኃኒት ሲቀነስ መረጃ ንጥረ-ነገር ወይም የንጥረ-ነገሮች ውሕድ ብቻ ስለሚሆን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣቱ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል:: መድኃኒቶች በጥንቃቄ/በትክክል ከተመረቱ፣ በጥንቃቄ ከተጓጓዙ፣ በጥንቃቄ ከተከማቹ፣ በአግባቡ ታዘዙ፣ ከታደሉና ከተወሰዱ የሚፈውሱ ወይም ጥቅም የሚያስገኙ ከዚህ ውጪ አንዱ እንኳን ተጓድሎ ከተወሰዱ ውጤት የማያስገኙ ወይም የሚመርዙ/ጉዳት የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ:: እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተሟልቶም አልፎ አልፎ ቀላል ጉዳቶች ወይም የደኅንነት ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች ቢታዩም ጥቅማቸው ክጉዳታችው ሲያመዝን አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይደርጋሉ።

አዲስ ዘመን፡-መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት አለው ሲባል ምን ማለት ነው፣ የመድኃኒት አሉታዊ ክስተቶች የምንላቸውስ ምን ምን ናቸው ?

ወይዘሮ አስናቀች፡– የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት ማለት ማንኛውም መድኃኒት በሚወሰድበት ጊዜ ሊያጋጥም የሚችል አሉታዊ ክስተት ነው:: በመድኃኒት አወሳሰድ ምክንያት የሚመጣ የጎንዮሽ ጉዳት በሁለት አይነት መንገድ ሊታይ ይችላል:: አንደኛው መድኃኒቱ ለትክክለኛው በሽታ ባለሙያው ባዘዘው መሠረት በመጠንና በሰዓት ተሰጥቶ ሊኖር የሚችል የተለመደ የጎንዮሽ ጉዳት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመድኃኒቶች አመራረት፣ እደላ፣ የማጓጓዝ ሂደት ላይ በሚፈጠር መመረዝ ምክንያት የሚከሰትና አደገኛ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ነው::

የመድኃኒት አሉታዊ ክስተቶች የምንላቸው፣ መድኃኒት ከተወሰደ በበኋላ ሊያጋጥም የሚችል ማንኛውም የሚታወቅ ወይንም የሚጠበቅ ወይም የማይታወቅ (ያልተጠበቁ) አሉታዊ ክስተቶች ናቸው:: ቀለል ያሉ መለስተኛና የተለመዱ አሉታዊ ክስተቶች ለምሳሌ፣ ራስ ምታት ማቅለሽለሽ፣ ሽፍታ፣ ማስመለስና የመሳሰሉት ናቸው:: ከባድ አሉታዊ ክስተት ማለት ያልተለመዱና ለጤና አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ:: ለምሳሌ ለመተንፈስ መቸገር፣ የልብ ምት መዛባት፣ ራስን መሳት፣ ከባድ ራስ ምታትና ማቅለሽለሽ ተጠቃሽ ናቸው::

አዲስ ዘመን፡-የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር ማለት ምን ማለት ነው? ለምንስ ያስፈልጋል?

ወይዘሮ አስናቀች፡-የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር ማለት በገበያ ላይ ስላሉ መድኃኒቶች ደኅንነት መረጃ የሚሰበሰብበት፣ የሚተነተንበት እና እንደ አስፈላጊነቱ ለማስተማሪያነት እና ለመከላከል የምንጠቀምበት ሥርዓት ነው። የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር መድኃኒቶች ተጠንተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የገበያ ፈቃድ በሚያገኙበት ወቅት ስለ መድኃኒቱ የሚኖሩ የደኅንነት መረጃዎች ውስን በመሆናቸውና መድኃኒቶች በስፋት ጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅት ቀጣይነት ያለው ክትትል ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው።

በተጨማሪም አንዳንድ የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች በተለይም አስከፊ የሆኑ በጥቂት ቁጥር እና በጊዜ ርዝመት የሚከሰቱ ችግሮችን መለየት እና ማወቅ የሚቻለው መድኃኒቱ በስፋት እና ረዘም ላለ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል በመሆኑ የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር በማን ይከናወናል?

ወይዘሮ አስናቀች፡- የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር እንደ ሀገር ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጠው በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሲሆን፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ተግባር ለማከናወን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ይሠራል። ከባለድርሻ አካላት ውስጥ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችና ኅብረተሰቡ (መድኃኒት ተጠቃሚው) ጉልህ ሚና አላቸው።

አዲስ ዘመን፡- የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥር እንዴት ይከናወናል?

ወይዘሮ አስናቀች፡- የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ገበያ ላይ የሚውሉ መድኃኒቶችን ደኅንነት፣ ፈዋሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ዘርግቷል። በዚህም መሠረት የመድኃኒት ደኅንነት ቁጥጥርን ለማረጋገጥ የተለያዩ የመድኃኒት የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርት ማድረጊያ ቅጾችን በማዘጋጀትና ለጤና ባለሙያው በማሰራጨት፣ ለጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የአሠራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማዳረስ እና ተፈፃሚነታቸውንም ክትትል የማድረግ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያና የመድኃኒት ደኅንነት ሥርዓት እንዴት እየተጓዙ ናቸው?

ወይዘሮ አስናቀች፡– ትክክለኛውን የጥቅም አደጋ-ስጋት ግምገማ ለማካሄድ የመድኃኒቱ ወቅታዊ የደህንነት መግለጫ አስፈላጊ ነው። የመድኃኒት ተቆጣጣሪዎችና የመድኃኒት ኢንዱስትሪዎች ይህንን መገለጫ የደኅንነት የክትትል ሥርዓትን (ፋርማኮቪጂላንስ) ለመፍጠር በንቃት የጤና ባለሙያዎችና በሽተኞች ሪፖርት ላይ ይተማመናሉ።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን/ EFDA በአዋጅ ቁ 1112/2011፣ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ (9 እና 10) እንዲሁም አንቀጽ 22 እና 24/2 መሠረት የተጣለበትን ኃላፊነት በተጠናከረ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ማንኛውም በመድኃኒት ወይም በሕክምና መሣሪያ ተቋም ውስጥ የሚሠራ ባለሙያ በመድኃኒት ተቋም ውስጥ ከመድኃኒት ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነት ወይም ከሕክምና መሣሪያ ጥራት፣ ደኅንነትና ውጤታማነት ጋር በተያያዘ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ችግሮች ሲከሰቱ ለአስፈጻሚ አካሉ ወይም ለክልል ጤና ተቆጣጣሪ ወዲያውኑ የማሳወቅ ግዴታ አለበት ይላል። ይህንንም ለማስፈጸም በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

አቅምን ከማጎልበት አንጻር ከ8ሺ ባለሙያዎች እንዲሠለጥኑ ተደርጓል:: በተለያዩ አካባቢ በሚገኙ ሰባት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ስድስት የክትትል ማዕከላት ተደራጅተዋል፣ ወደ ዓለም አቀፉ የመረጃ ቋት የሚላኩ ሪፖርቶች በእጅጉ በመጨመር ኢትዮጵያ ከነበረችበት የመጨረሻዎቹ ተርታዎች ወጥታ ባሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ ትገኛለች::

የሪፖርት ማቅረቢያ አማራጮችን በማስፋትና በማጠናከር ረገድ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል:: አሁኑ ላይ በፖስታ ቤት የሚላክ አስቀድሞ የተከፈለበት ቢጫ ቅጽ፤ በ8482 (ነፃ ክፍያ)መስመርና በኢ-ሪፖርት፡ www. fmhaca.gov.et-አገልግሎት እንዲሁም የኢሜል፡አማራጮችን እንዲቀርቡ ተደርጓል::

አዲስ ዘመን፡- የመድኃኒት ደኅንነት ለማረጋገጥ ከማን ምን ይጠበቃል?

ወይዘሮ አስናቀች፡- ቀዳሚው ከኅብረተሰቡ/መድኃኒት ተጠቃሚው ነው:: ማንኛውም ሰው መድኃኒት በሚታዘዝለት ወቅት ስለ መድኃኒቱ አስፈላጊውን መረጃ ከባለሙያዎች በድንብ መጠየቅ እና መረዳት አለበት። በተጨማሪም፣ መድኃኒት በሚጠቀምበት ወቅት ማንኛውም አይነት የጎንዮሽ ክስተት ሲያጋጥመው መድኃኒቱን ያዘዘለት ባለሙያ ጋር በመሄድ ችግሩን ማሳወቅና የሚሰጠውን ምክር እና ሕክምና በአግባቡ መተግበር አለበት።

የጤና ባለሙያው ኃላፊነትም ከፍተኛ ነው:: የጤና ባለሙያዎች በእለት ተእለት ተግባራቸው ለታካሚዎች በአንድም በሌላም መንገድ ሕክምና ሲሰጡ የሚውሉ በመሆናቸው፤ የመድኃኒት አወሳሰድ ሥርዓትና ከመድኃኒት ጋር ተያይዘው ስለሚያጋጥሙ የጎንዮሽ ክስተቶች ለታካሚዎች ቀድመው የማሳወቅ እና ችግሮች ሲከሰቱም አስፈላጊውን ሕክምና የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። በተጨማሪም፣ የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርቶችን ወደ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የኅብረተሰቡና ከጤናው ባለሙያው ባሻገር ከተቆጣጣሪ አካላት ሚናቸው ግዙፍ ነው:: በየደረጃው የሚገኙ የተቆጣጣሪ አካላት ስለመድኃኒት የጎንዮሽ ክስተት የማሳወቅ፣ የጤና ባለሙያውን ስለ መድኃኒት የጎንዮሽ ክስተቶች ላይ ማሠልጠንና የክትትል ሥርዓቱን ለማከናውን የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማለትም፡- መመሪያ፣ ጋይድላይን፣ ሪፖርት ማድረጊያ ቅጾችን ለጤና ተቋማት የማዳረስ እና የጎንዮሽ ክስተቶች ሪፖርቶችን የመሰብሰብ ኃላፊነት አለባቸው። በተጨማሪም፣ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትል የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርት በሚቀበሉበት ወቅት አስቸኳይ የማጣራት ሥራን በማከናወን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግብረመልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- የመድኃኒት አሉታዊ ክስተቶች ሲያጋጥሙ ምን ማድረግ ይገባል፣ ሪፖርት ማድረግስ ለምን ያስፈልጋል? ሪፖርት ማድረግ ያለበት ማነው፣ መቼና ለማንስ ነው ?

ወይዘሮ አስናቀች፡– ኅብረተሰቡም ሆነ የጤና ባለሙያዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው:: እያንዳንዱ ሰው የመድኃኒቶች ደኅንነት ጉዳይ ይመለከተዋል:: ሁሉም “መድኃኒቴ ደኅንነቴ” ብሎ መንቀሳቀስ አለበት:: ክስተቱ እንደተፈጠረ በአፋጣን በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ባለሙያን ማማከርም ይገባል:: ወዲያው ሪፖርት ማድረግም ተገቢ ነው:: ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ነፃ የስልክ መስመር 8482 በመደወል ማሳወቅ ይገባል::

የመድኃኒት አሉታዊ ክስተቶችን ሪፖርት ማድረግም ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ፋይዳው እጅጉን ከፍ ያለ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ሀገር አቀፍ የጤናው ዘርፍ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ ነው:: በተለይም ለጤና አገልግሎት ሥርአቱን ለማሻሻል የሚኖረው አስተዋፅዖ ግዙፍ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የመድኃኒቶች ደኅንነት ጉዳይ በአግባቡ ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ቀጣይ እርምጃ ምን ይሆን?

ወይዘሮ አስናቀች፡- የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በተለይ፣ የመድኃኒቶች ደኅንነት ክትትል ሥርዓቱን ማጠናከር፣ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል/ወቅታዊ ማድረግ፣ የባለሙያዎች አቅም ግንባታና ክትትልን ማጠናከር፣ የመድኃኒቶች ደኅንነትን አስመልክቶ በሚነሱ ጉዳዮች አስፈላጊና ወቅታዊ እርምጃ መውሰድ፣ ኅብረተሰቡን የቁጥጥሩ ባለቤት እንዲሆን መሥራትን ጨምሮ ተከታታይ የግንዛቤ ማዳበር ሥራዎችን ይበልጥ የሚሠራ ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሪፖርት ሲደርሰው ምን ይደረጋል ?

ወይዘሮ አስናቀች፡- ስለ ሪፖርቱ ትክክለኛነትና ምሉዕነት የማጣራት ሥራ ይሠራል:: ሪፖርቱ ስለመድረሱ የእውቅናና የምስጋና ደብዳቤ ለሪፖርት አቅራቢው እንዲደርሰው ይደረጋል:: ወደ ዓለም የጤና ድርጅት የመረጃ ቋት ሪፖርቱን የማስገባት ሥራ ይሠራል:: ሪፖርቱን የመተንተንና ቀጣይ መለየት ያለባቸው ሥራዎችን የመለየት ሥራ ይሠራል:: አስፈላጊ ከሆነ አሉታዊ ጉዳትን ያማከለ ተጨማሪ መረጃዎን የማሰባሰብና የምርት ናሙናዎችን ወስዶ የላብራቶሪ ትንታኔ ሥራ ይከናወናል:: የተሰበሰበው መረጃም ለብሔራዊ የመድኃኒት ክትትል አማካሪ ኮሚቴ ይቀርባል:: አማካሪ ኮሚቴው በሚቀርቡ አስተያየቶች ላይ በመመርኮዝ ቀጣይ የመማስተካከያ ሥራዎችን ይሠራል:: አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የቁጥጥር እርምጃ ይወሰዳል::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡና መረጃና ጊዜ እናመሰግናለን::

ወይዘሮ አስናቀች፡- እኔም አመሰግናለሁ::

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You