የቤት ኪራይ እና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከሕግ ባሻገር ያሉ ጉዳዮች ቢፈተሹ!

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሌሎች ትላልቅ በከተሞች አካባቢ በተፈጠረው የሥራ ዕድል ዜጎች ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሱ በመምጣታቸው የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል:: ይህም ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እና ለሸቀጦች ዋጋ ንረት አንዱ መንስኤ ነው ብዬ አስባለሁ:: ሆኖም የችግሩ መንስኤ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ብቻ ነው ብሎ መደመድም ግን የዋህነት ይመስለኛል::

ምክንያቱም የዓለም አቀፍ የዋጋ ንረትና የሕገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ተፅዕኖም ሊዘነጋ አይገባም:: እናም በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት በመቋቋም አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይና የሸቀጦችን ዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከሕግ ማውጣት ባሻገር ሌሎች የችግሩን መፍቻ መንገዶችም ቢፈተሹ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባይፈታውም በመጠኑ ሊቀንሰው ይችላል የሚል ሃሳብ አለኝ::

እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ኪራይና የሸቀጦችን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምረው መመሪያዎችን እያወጡ የተለያዩ ርምጃዎችን ሲወስዱ ቢቆዩም ለሕገ ወጥ ደላሎችና ለአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ችግሩን አባባሰው እንጂ ሲፈታው አልታየም:: ስለዚህ አቅርቦትና ፍላጎት ሳይጣጣም ችግሩን ለመፍታት መሞከር “ጉም የመዝገን” ያህል ነው:: በመሆኑም በፌዴራል መንግሥትና በየከተማው ያሉ አመራሮች ሕገ ከማውጣትና በመገናኛ ብዙሃን ብቅ እያሉ መግለጫ ከመስጠት ባሻገር አቅርቦትና ፍላጎትን እንዲጣጣም መሥራት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል::

አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች ያለው ነዋሪ ቁጥር እየጨመረ፤ የመሬት አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ ቀደም ሲል እንደሚደረገው ለእያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት በግል በመስጠት ባይቻልም ነዋሪዎችን በማህበር አደራጅቶ ቤት ሠርተው እንዲኖሩ በማድረግ፤ መንግሥት በዝቅተኛ ወጪ (Low cost) ቤቶችን ሠርቶ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማከራየት ቢችል በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በመጠኑ ቢሆን ሊያረጋጋው የሚችል ይመስለኛል:: ቤት አከራዮችም እንደፈለጉ የቤት ኪራይ ዋጋ ከመጨመር ይልቅ ተወዳድረው እንዲያከራዩ ስለሚያደርጋቸው የመኖሪያ ቤት ኪራይ እንዲቀንስም መፍትሔ ይሆናል ብዬ አስባለሁ::

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተደራርበው የተሠሩ የድሮ ቤቶችን በማፍረስና ዘመናዊ ቤቶችን በአጭር ጊዜ መልሶ በመገንባት ምቹ ባልሆነ አካባቢ ሲኖሩ ለነበሩ የከተማው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ኑሮ ሲኖሩ ለነበሩ ሌሎች የከተማው ነዋሪዎችንም ጭምር የዘመናዊ ቤት ባለቤት አድርጓቸዋል:: ድሃ ለሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ቤት ሲሰጣቸው በመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ አይቼ እኔ በግሌ አድንቄያለሁ፤ እናንተም ያደነቃችሁ ይመስለኛል::

ይህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የከተማይቱን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከሚወስዷቸው ርምጃዎች መካከል ጥሩ ማሳያ ነው ብዬም አስባለሁ:: ስለሆነም የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመፍታት ከተፈለገ እንደነዚህ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋትና አጠናክሮ በማስቀጠል እንጂ ሕግ በማውጣትና በየጊዜው በመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በመስጠት ብቻ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም:: በዚህ ረገድ በሌማት ቱሩፋት እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ውጤት እያሳዩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል::

ለመኖሪያ ቤት ኪራይም ሆነ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ከአቅርቦትና ከፍላጎት አለመጣጣም ቀጥሎ የሕገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነትም ሌላው ችግር ነው ብዬ አስባለሁ:: ስለዚህ በቤት አከራይና አሻሻጭ ደላሎች ዙሪያ ያለው አሠራር በሥርዓት እስካልተመራ ድረስ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይም ሆነ የሸቀጦች የዋጋ ንረት በቀላሉ ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል::

ስለዚህ የቤት ኪራይና የሸቀጦችን ዋጋ ንረት ለማረጋጋት ሕገ ወጥ ደላሎችን ከመስመር በማውወጣት አከራይና ተከራዩ እንዲሁም አምራቹና ተጠቃሚውን በቀጥታ የማገናኘት ሥራ ቢሠራ አከራዩንና ተከራዩን፣ አምራቹን እና ሸማቹን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል አስተያየት አለኝ::

ምክንያቱም በመንግሥት አመራሮች ሲወሰዱ የነበሩ ርምጃዎች ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠት እንጂ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ስላልነበረ፣ ለሕገ ወጥ ደላሎች እና ለአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የበለጠ በር ከፍቶ ችግሩን አባባሰው እንጂ በዘላቂነት ሊፈታው እንዳልቻለ ሕዝቡ ሲታዘብ መቆየቱን በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሳይገነዘቡት የቀሩ አይመስለኝም::

ስለዚህ የመኖሪያ ቤት ኪራይንና እና የሸቀጦችን ዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት፣ ክልሎችና የየከተማ አስተዳደሩ አመራሮች አቅደው መሥራት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል:: በየደረጃው ያሉ አመራሮች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅደው ካልሠሩ ሕግ በማውጣትና መግለጫ በመስጠት ብቻ በየከተሞቹ ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይና የሸቀጦች የዋጋ ንረት ችግር ይፈታል ብሎ ማሰብም “አባይን በጭልፋ” እንዳይሆን አሰጋለሁ::

ምክንያቱም ችግሩ ውስብስብ በመሆኑ ነው:: ይህን የምለው ጨለምተኛ አስተሳሰብ ኖሮኝ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች የተፈቱት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም እንጂ ሕግ በማውጣትና በመቆጣጠር ብቻ ችግሩ ሲፈታ ስላላየሁ ነው:: እንዲያውም እጥረቱ በጨመረ ቁጥር ሕገ ወጥ ነጋዴዎችና አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያላግባብ ለመበልፀግ በሚያደርጉት ጥረት ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው በሕዝቡ ላይ የበለጠ ጫና ሲፈጥሩ ነው የሚስተዋለው::

ለምሳሌ ባለፉት ዓመታት የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ትልቅ መነጋገሪያ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ክስተት በመሆኑ ማንኛውም ሰው የሚረሳው አይመስለኝም:: በሥራ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ ውጭ በሄድኩባቸው አካባቢዎችም የሲሚንቶ እጥረት ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ሲነሳ አስታውሳለሁ:: ይህን ተከትሎም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተለያዩ መመሪያዎችን እያወጣ ለመቆጣጠር ቢሞክርም እጥረቱን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችን እና ሕገ ወጥ ደላሎችን ተጠቃሚ አደረገ እንጂ ችግሩን ሊፈታው አልቻለም:: አቅርቦት እና ፍላጎት ሲጣጣም ግን ችግሩ ተፈትቶ በአሁን ጊዜ በሲሚንቶ እጥረት የሚነሳ ቅሬታም የለም፤ ትላልቅ ግንባታዎችም በስሚንቶ እጥረት ሥራቸው ሲቆም አይታይም::

እውነት እንነጋገር ከተባለ የሲሚኒቶ እጥረት ሊፈጠር ይችል የነበረው በአሁኑ ወቅት ነበር:: ለምን ሲባል የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ያሉት አሁን በመሆኑ:: ነገር ግን አቅርቦትና ፍላጎት በመጣጣሙ በአሁኑ ጊዜ የሲሚንቶ እጥረት አለ ተብሎ ቅሬታ የሚያነሳ አካል የለም፤ ትላልቅ ግንባታዎችም በሲሚንቶ እጥረት ሲስተጓጎሉ አይታይም:: እንዲያውም በተቃራኒው ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድመው በአጭር ጊዜ እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆኑ ይታያል:: ይህን ተሞክሮ ለመኖሪያ ቤት ኪራይና ለሸቀጦች የዋጋ ንረት ማረጋጊያ ቢጠቀሙበት ስል ተመኘሁ::

ከዓመታት በፊት በ30 እና በ50 ብር ቤት ያከራዩ ሰዎች ቡና ሲያፈሉ ተከራዮች ተጠርተው ቡና አብረው እየጠጡ፤ ሲታመሙ እየጠየቁ፤ የአከራይና የተከራይ ልጆች አብረው ተጫውተው ነበር በስምምነት አብረው የሚኖሩት:: ተከራዮችም በተመሳሳይ ነበር የሚያደርጉት:: ከቤተሰብ ርቀው የሚኖሩ ተከራዮች ትዳር ሲመሰርቱም እንደወላጅ ሆነው የሚድሯቸው፤ አለፍ ሲልም ልጅ የሚድሩላቸው አከራዮች ነበሩ::

አሁን አሁን ግን እነዚህ ሁሉ መልካም ማህበራዊ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ተሸርሽረዋል ማለት ባልችልም እየቀነሱ ለመምጣታቸው በጋራ መኖሪያ ቤቶች ያለውን ሁኔታ መመልከት በቂ ነው:: አከራይና ተከራይም የቤት ኪራይ ሲቀባበሉ ካልሆነ በስተቀር አይተዋወቁም:: ይተዋወቃሉ ከተባለም የቤት ኪራይ የሚከፍለው (የምትከፍለው) እና የቤት ኪራይ የሚቀበለው (የምትቀበለው) ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል:: በተለይ የመውጫና የመግቢያ ሰዓታቸው የተለያየ ከሆነ ሌሎች የአከራይና የተከራይ ቤተሰቦች ላይተዋወቁ ይችላሉ::

በኮንደምኒየም አካባቢ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች ስለማይተዋወቁም የአንዱን ጎረቤት ዕቃ ሌባ በመኪና ሲዘርፍ ጎረቤቴ ቤት ሊቀይር ነው እንጂ ሌባ እየዘረፈው ነው ብሎ ማሰብ ስለቀረ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ሰው የለም:: ሌቦቹም ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ያለምንም ስጋት የሰዎችን ዕቃ በመኪና ጭነው እብስ ይላሉ:: አንድ የሥራ ባልደረባዬም ዕቃውን ሌቦች በመኪና ጭነው እንደወሰዱበት በቅርብ ቀን ነግሮኛል:: ብቻውን የሚኖር ሰው ሲሞት ምን ሆኖ ነው የጠፋው ብሎ የሚጠይቅ ሰው ስለማይኖርም ከሞተ ሦስትና አራተኛው ቀን ሲሆነው አስከሬኑ ሲሸት ብቻ ፖሊስ ተጠርቶ የሚወጣበትን አጋጣሚም እየሰማን ነው:: ቡና ተጠራርቶ መጠጣት፣ በችግርና በደስታ ጊዜ መደጋገፍም እየቀነሰ መጥቷል ማለት ይቻላል:: ታዲያ ይሄንን አደጋ ያሸከመንን ችግር መፍታት አይገባም ትላላችሁ?

በጥናት የተደገፈ ስላልሆነ ሁሉም አከራይ እና ተከራይ ፍጹም ግንኙነት የላቸውም ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር ባልችልም፣ በአሁኑ ጊዜ የአንዳንድ አከራይና ተከራይ ግንኙነት ጥሩ አለመሆኑን እኔም በግሌ ታዝቤያለሁ፤ ከሌሎች አከራዮችና ተከራዮችም ሮሮ ሲሰማ አድምጫለሁ:: ተከራዮች ቤት ለመከራየት ሲጠይቁ ቤተሰብ አለህ

(ቤተሰብ አለሽ) የሚለው ጥያቄ ቀድሞ መምጣቱ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው:: ምክንያቱም ቤተሰብ ካለው (ካላት) ወይ የቤት ኪራይ ይጨመርበታል (ይጨመርባታል)፤ አለበለዚያም ቤተሰብ ካለህ (ካለሽ) አናከራይም ሊባሉም ይችላሉ::

በዚህ ላይ አስገዳጅ የሆነ ሕግ መውጣቱ የአከራይንና የተከራይን ማህበራዊ ግንኙነት የባሰ ያሻክረው ይሆን የሚል ስጋት ያድርብኛል:: ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች ከተሞች አከራይና ተከራይ እንደ ቤተሰብ ጆሮና ጉትቻ ሆነው በፍቅር እንጂ የአይጥና ድመት ሆነው ይኖሩ እንዳልነበረ አስታውሳለሁ:: ይህ በመሆኑ ቀደም ሲል ከነበሩን አከራዮቻችን ጋር እስካሁን ድረስ የምንጠያየቅ ሰዎችም አለን፤ ሌሎችም ሲናገሩ ሰምቻለሁ:: አሁን ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው::

በአከራይ እና በተከራይ መካከል የነበረው አብሮ የመኖር መልካም እሴት ከተሸረሸረ ደግሞ በውጭ ሀገር እንደምንሰማው ሁሉም ሰው በየቤቱ በሩን ዘግቶ ለመኖር ምክንያት ስለሚሆን መልካም ማህበራዊ እሴቶቻችንን ይሸረሽር ይሆን የሚል ስጋትም ያድርብኛል:: ምክንያቱም በእኛ ሀገር ያለው አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴት መልካም በመሆኑ ጎረቤት ሲቸገር ችግሩን አብሮ የሚካፈል፣ የጎረቤቱ ደስታም ደስታዬ ነው ብሎ የሚደሰት ሕዝብ ነበረን::

አሁን አሁን ግን እነዚህ ማህበራዊ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ ለምጣታቸው ከላይ ያነሳኋቸው አብነቶች በቂ ናቸው:: በሀገራችን ጥሩ ጥሩ ማህበራዊ እሴቶቻችን እንዳይሸረሸሩ ሕግ ከማውጣት ባሻገር ሌሎች የችግር መፍቻ መንገዶችም ቢፈተሹ የሚል አስተያየት የማነሳውም እንደ ዜጋ ጉዳዩ ስለሚያሳስበኝ ነው::

በብዙ አካባቢዎች ያለው ገበያም በሥርዓት ሳይሆን በሕገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ስለሚመራ ሸማቾች ብቻ ሳይሆኑ አምራቾችም በለፉት ልክ የሚገባቸውን ዋጋ እያገኙ አይደለም:: በሥራ አጋጣሚ በተዘዋወርኩባቸው አካባቢዎች አምራቾች የሚሸጡበትንና ሸማቾች የሚገዙበትን ዋጋ ሳይ በጣም ያሳዝነኛል:: እንዲህ ዓይነት ልዩነት የሚኖረው ወደ ሩቅ አካባቢ ተጓጉዞ ከሄደ ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ ከዛው ከተመረተበት አካባቢ ጭምር እንጂ:: ይህ ደግሞ የሕገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት መኖሩን ፍንትው አድርጎ ያሳያል::

ስለዚህ የሕገ ወጥ ደላሎችን ጣልቃ ገብነት በመከላከል ገበያው በሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል፤ ኅብረተሰቡም መተባበር አለበት:: ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ካልተባበረ መንግሥት በእያንዳንዱ የገበያ ቦታ ተቆጣጣሪ ማቆም ስለማይችል ችግሩን ብቻውን ሊፈታው አይችልም:: ገበያው በሥርዓት ካልተመራ ደግሞ “ቁጭ ብሎ የሰቀሉት፣ ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል” እንደሚባለው እንዳይሆንም እሰጋለሁ::

ይህን ስል የመኖሪያ ቤት ኪራይን እና የሸቀጦችን ዋጋ ለመቆጣጠር በፍጹም ሕግ ማውጣት አያስፈልግም እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ሊባልልኝ ይገባል:: ምክንያቱም የመኖሪያ ቤት ኪራይንም ሆነ የዕለት ከዕለት የፍጆታ ሸቀጦችን አቅርቦትንና ፍላጎትን ለማጣጣም ከተሠራ በኋላ አከራይም ሆነ ተከራይ በሥርዓት እንዲስተናገዱ እና ገበያው በሥርዓት ለመምራት ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ነው:: ነገር ግን በእኔ ግምት በአዲስ አበባ አስተዳደር ሆነ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይና የሸቀጦችን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ግን አዋጅና ደንብ ማውጣት ብቻ መፍትሔ ይሆናል ብዬ ስለማላምን ነው ሌሎች ተግባራት ሊታሰቡም ባለድርሻዎችም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል የምለው:: ዛሬን አበቃሁ፤ ቸር እንሰንብት!

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሠፈር)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You