በሕንድ ዋና ከተማ የሚገኙ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ7 ቀናት የሚቆይ የጸሎት ሥነሥርዓት ጀምረዋል።
“ሂንዱ ሲና” በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቡድኖች ትራምፕ ፖለቲካውን ከተቀላቀሉበት 2016 ጀምሮ በየዓመቱ የልደት ቀኑን አስታውሰው ያከብራሉ።
ከሰሞኑ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ የሰሙት አማኞቹ “የኃይል እና ጥበቃ ጌታ” በሚል በሚጠሩት “ባግላሙኪ” ከተሰኝው የሂንዱ አምላክ ምስል ከፍ ብሎ ረጂም ዕድሜ ለትራምፕ የሚል ጽሑፍ ያረፈባቸውን የዶናልድ ትራምፕ ፎቶዎችን በመስቀል ሃይማኖታዊ ሥርዓትን አከናውነዋል።
የጸሎቱ መሪው የአምልኮ ሥርዓቱን ባከናወኑበት ወቅት አምላካቸው ለትራምፕ ጥበቃ እና ደኅንነትን እንዲያወርድለት ጠይቀዋል ሲል ሮይተርስ ነው ያስነበበው።
ዛሬ እንደተጀመረ የተሰማው የአምልኮ እና ጸሎት ሥነሥርዓቱ የትራምፕ ደኅንነት እና ጤንነት ላይ በማተኮር ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት ይዘልቃል ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ወደ አሜሪካ ፖለቲካ ብቅ ካሉበት ወቅት ጀምሮ በአንድ ላይ በመሰባሰብ ልደታቸውን የሚያከብሩት አማኞች ኬክ፣ ፊኛዎችን እና የድግስ ኮፍያዎችን በመጠቀም አሜሪካውያን ልደቶችን በሚያከብሩበት መንገድ የትራምፕን ልደት ሲያከብሩ ቆይተዋል፡፡
ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አማኞቹ ለሂንዱ ማኅበረሰብ ደኅንነት እና እድገት ብቻ ነው የምንሠራው ይላሉ።
200 ሚሊዮን የሚጠጉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚኖሩባት ሕንድ የሂንዱ እምነት ተከታዮች በሙስሊሞች እና በመስጂዶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈጸም ይታወቃሉ።
የሂንዱ ብሔርተኛ እንደሆነ የሚነገርለት የናሪንድራ ሞዲ ባሃራቲያ ጃንታ ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በሙስሊሞች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ወንጀሎች መጨመራቸው ይነገራል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም