የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚህ ሳምንት በሩሲያ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይ በመሳተፋቸው ምክንያት ኪዬቭን ለመጎብኘት የያዙትን እቅድ ውድቅ እንዳደረጉባቸው የዩክሬን ባለሥልጣን ተናግረዋል።
ኪዬቭ ባለፈው ሐሙስ በሩሲያዋ ካዛን ከተማ በተካሄደው ስብስብ ላይ የጉተሬዝ መገኘት እና የጉባኤው አዘጋጅ ከሆኑት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሰላምታ መለዋወጣቸው አበሳጭቷታል።
የተመድ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ በብሪክስ ጉባኤ ሠላም እንዲመጣ ጥሪ ያቀረቡት ጉተሬዝ ባለፈው መስከረም ወር በኒውዮርክ ከዘለንስኪ ጋር በተገናኙበት ወቅት በዩክሬን ስለሚያደርጉት ጉብኝት ተወያይተው ነበር ብለዋል።
ሀቅ አክለውም እንደገለጹት ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ ተመድ እና ዩክሬን ጉብኝቱ የሚያካሄድበትን ለሁለቱም ምቹ የሆነ ጊዜ የመምረጥ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ነገርግን እስካሁን የተወሰነ ጊዜ የለም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
አሁን ላይ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጉተሬዝ በብሪክስ ጉባኤ በመሳተፋቸው ምክንያት ጉብኝቱን መሰረዛቸውን ሮይተርስ አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የዩክሬን ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ እለት ጉተሬዝ የብሪክስን ጉባኤ እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸው የተመድን ዝና የሚጎዳ ነው ብሏል። ዘለንስኪ የጉተሬዝን መሳተፍ አውግዘዋል።
“ምንም እንኳን የተወሰኑ ባለሥልጣናት የካዛንን ስብሰባ ከተመድ ቻርተር ቢያስበልጡም፣ ዓለም የሀገራት መብት እና ዓለም አቀፍ ሕግ መከበር አለበት በሚለው መርሕ ላይ እንደጸና ነው” ብለዋል ዘለንስኪ።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በሚሊዮኖች ደግሞ ተሰደዋል። ባለፈው ሐሙስ በሩሲያ የተካሄደው የብሪክስ ስብሰባ ዓላማው ምዕራባውያን ያልሆኑ ሀገራትን አቅም ለማሳየት ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም