ኢራን በሁሉም መስመሮች በረራዎችን አቋረጠች

እሥራኤል በትናትናው ዕለት በኢራን ላይ የወሰደችውን የአጸፋ ርምጃ ተከትሎ በቀጣይ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ ከኢራን የሚነሱም ሆነ በኢራን የሚያርፉ በረራዎች መቋረጣቸውን የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።

በኢራን የአየር ክልል የሚደረግ በረራ ቆሟል። የሀገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ቃል አቀባይ ጃፋር የዝርሉ “በቀጣይ እስክናሳውቅ ድረስ ሁሉም በረራዎች ተቋርጠዋል” ብለዋል።

ኢራን መነሻ እና መዳረሻቸውን ወደ ሀገሪቱ ያደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንዲቋረጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ቴህራን በረራዎች እንዲቋረጡ ያደረገችው በእሥራኤል ከተሰነዘረባት ጥቃት ከሰዓታት በኋላ መሆኑም ተመላክቷል።

የበረራ መረጃዎችን የሚያጋራው ፍላይት ራዳር የእሥራኤልን ጥቃት ተከትሎ የኢራን የአየር ክልል ከአውሮፕላኖች ነፃ መሆኑን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።

የኢራን አየር ኃይል እሥራኤል በቴህራን ኩዜስታን እና ኢማን ግዛቶች ሊፈጽመው የነበረውን ጥቃት ማክሸፍ መቻሉን ገልጿል።

በተወሰኑ አካባቢዎች መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የጠቀሰው ታስሚን የዜና ወኪል በበኩሉ ቴህራን ለቴልአቪቭ ጥቃት አጸፋውን እንደምትመልስ መዛቷን ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።

የእሥራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ በሰጡት መግለጫ “እሥራኤል ግቧን አሳክታለች፤ እሥራኤልን የሚተነኩሱ ከባድ ዋጋ ይከፍላሉ” ብለዋል።

ቴህራን ሌላ ዙር ጥቃት በእሥራኤል ላይ ከፈጸመች ቴልአቪቭ ከበድ ያለ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።

“መልዕክታችን ግልጽ ነው፤ እሥራኤል ላይ አደጋ የሚደቅንና ቀጣናውን ወደ ከፋ ውጥረት የሚከት አካል ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉም ተደምጠዋል።

እሥራኤል የትናንትናውን ጥቃት የፈጸመችው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ኢራን 200 በሚጠጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ለፈጸመችባት አጸፋውን ለመመለስ ነው።

ቴህራን ግን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን ከመግለጽ ውጭ እሥራኤል ስኬታማ ነበር ስላለችው የአጸፋ ጥቃት ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልሰጠችም።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You