አሜሪካ ኢራን በእሥራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ አስጠነቀቀች

ኢራን በበኩሏ ራሴን የመከላከል መብት አለኝ ከማለት ውጪ የአጸፋ እርምጃ ስለመውሰዷ እስካሁን አልተናገረችም

አሜሪካ ኢራን በእሥራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ አስጠንቅቃለች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእሥራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል፡፡

እሥራኤል በኢራን ይደገፋሉ የምትላቸው የሐማስን እና የሊባኖሱን የሂዝቦላህ መሪዎችን ገድላለች፡፡

ኢራን ለእሥራኤል ጥቃት በያዝነው ወር መግቢያ ላይ በእሥራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ከትናንት በስቲያ ደግሞ እሥራኤል ለኢራን ጥቃት የአፀፋ እርምጃ ወስዳለች፡፡

ይህን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ወደ ፊት ለፊት ጦርነት እንዳይገቡ የተሰጋ ሲሆን አሜሪካ ኢራን እሥራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ አስጠንቅቃለች፡፡

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮልድ ኦስቲን እንዳሉት የመካከለኛው ምስራቅ ወደ ተባባሰ ጦርነት እንዳይገባ ሁለቱም ሀገራት የገቡበትን መካረር እንዲያረግቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የእስራኤልን የአየር ድብደባ በማውገዝ፤ ኢራን ራሷን የመከላከል መብት እና ግዴታ አለባት ሲል አስታውቋል።

የኢራን ጦር በበኩሉ፤ እሥራኤል በኢላም እና ኩዜስታን ግዛቶች ድንበር አቅራቢያ ላይ የሚገኙ የኢራን ራዳር ሥርዓት ላይ ቀለል ያሉ ሚሳዔሎችን ተጠቅመው ጥቃት መሰንዘራቸወን አስታውቋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኢራን ለእሥራኤል ጥቃት የአፀፋ እርምጃ ስለመውሰዷ እስካሁን ያለችው ነገር የሌለ ሲሆን ለአሜሪካም ማስጠንቀቂያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You