ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እሥራኤል ያሉ 14 መኖሪያ መንደሮች ቤታቸውን እንዲለቁ አስጠነቀቀ

ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እሥራኤል ያሉ 14 መኖሪያ መንደሮች ቤታቸውን እንዲለቁ አስጠንቅቋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእሥራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በሊባኖሱ ሂዝቦላህ እና እሥራኤል ጦር መካከል ይፋዊ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን የእሥራኤል ጦር ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ገብቶ ከሂዝቦላህ ተዋጊዎች ጋር እየተዋጋ ይገኛል፡፡

በሁለቱ ድንበር አቅራቢያ የነበሩ ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን እየለቀቁ ሲሆን በሰሜናዊ እስራኤል 14 መኖሪያ መንደሮች ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ ሂዝቦላህ አስጠንቅቋል፡፡

ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እሥራኤል የሚኖሩ እሥራኤላውያን መኖሪያ ቤታቸውን እንዲለቁ ያስጠነቀቀው የሀገሪቱ ጦር ነዋሪዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰፍሯል በሚል ነው፡፡

ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ለሚደርስባቸው ጥቃት ኃላፊነቱን እንደማይወስድም ሂዝቦላህ አስታውቋል፡፡

እሥራኤል ሂዝቦላህ እና ሐማስን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ውስጥ ያሉ ፀረ እሥራኤል ድርጅቶች በእስራኤል የሚደገፉ ናቸው ስትል ትከሳለች፡፡

የየመኑ የሁቲ አማፂ ቡድን በኢራን ይደገፋሉ ተብለው ከተለዩ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን በቀይ ባሕር ከእሥራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ መርከቦችን እየመታ ይገኛል፡፡

እሥራኤል በየመኑ ሁቲ አማፂ ቡድን ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ ያደረገች ሲሆን አሜሪካም የምድር ቦምቦችን በመጠቀም በቡድኑ ላይ ተደጋጋሚ የአየር ላይ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡

በኢራን ይደገፋሉ ከሚባሉት ውስጥ እሥራኤል ከሐማስን እና ሂዝቦላህ ጋር ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ስትሆን የቡድኖቹን አመራሮችም ገድላለች ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You