ሴቶች በሕይወታቸው ልዩ ልዩ ችገሮች ይገጥማቸዋል:: እነዚህ ችግሮች ማኅበራዊ አልያም ኢኮኖሚያዊ ሊሆኑ ይችላሉ:: ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ወደተለያዩ ዓረብ ሀገራት ተሰደው ስንት ደክመው የሠሩበት ሳይከፈላቸው ባዶ እጃቸውን የሚመለሱ ሴቶች ጥቂት አይደሉም:: በቤተሰብና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ሳይፈልጉ ኑሯቸውን በሴተኛ አዳሪነት የሚገፉም ብዙ ናቸው:: እጅ አጥሯቸው በየጎዳናው ወድቀው ምፅዋት የሚለምኑ ሴቶች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም::
ለእነዚህ ሴቶች በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ወደ አንድ ማዕከል አስገብቶ የተሐድሶና ክህሎት ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ የሚሰማሩበትን መንገድ ማመቻቸት የተቻለውን ግን በዚህ ዘመን ይመስላል:: ይህም እውን የሆነው በነገዋ ሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ነው::
የነገዋ ሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሂርጳሳ ጫላ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ማዕከሉ በአስራ አንድ ወራት ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል:: ወደማዕከሉ የሚመጡ ሴቶች አራት መሠረታዊ ነገሮችን ያለፉ ሊሆኑ ይችላሉ:: የመጀመሪያዎቹ የጎዳና ላይ ሕይወት ይመሩ የነበሩ ናቸው:: ሁለተኛዎቹ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉ በየቤቱ ያሉ ጥገኛ የሆኑ ወረዳቸው እነዚህ ሴቶች መታገዝ አለባቸው ብሎ የለያቸው ናቸው::
ሦስተኛዎቹ ሴተኛ አዳሪ የነበሩና በዚህ ሥራ ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ሲሆኑ አራተኛዎቹ ደግሞ ውጪ ሀገር ሄደው ሳይሳካላቸው የተመለሱ ናቸው:: ከአስራ አምስት እስከ አርባ ባለው እድሜ መካከል ያሉ ሴቶች ናቸው ወደ ማዕከሉ የሚቀላቀሉት:: ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አንስቶ እስከታችኛው ድረስ ባለው የወረዳ መዋቅር መሠረት ሴቶቹ ተመርጠው ይመጣሉ::
ሴቶች ወደ ማዕከሉ ሲገቡ በቅድሚያ በማዕከሉ ለመቆየት ፍቃደኝነታቸው ይጠየቃል:: ፍቃደኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል:: ለዚህም በማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ ክሊኒክ ተዘጋጅቷል:: ምርመራው አንድም ቀደም ብለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ ሴቶች ወደ ማዕከሉ ከገቡ በኋላ ሕክምናቸው እንዳይቆረጥ ያደርጋል:: በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል ያልተመረመሩና ራሳቸውን ያላወቁ ከሆነ በምርመራ ያለባቸውን የጤና ችግር ለመለየትና ሕክምና ለማግኘት ያስችላቸዋል::
ፍቃደኝነታቸው ተረጋግጦ የሕክምና ምርመራ ካገኙ በኋላ ሴቶቹ በርካታ አገልግሎቶችን በማዕከሉ ያገኛሉ:: ከነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ አንደኛው የሕክምና አገልግሎት ሲሆን ከማዕከሉ አቅም በላይ የሆኑ የጤና ችግሮች ሲያጋጥሙ ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ጋር በመሆን ተጨማሪ ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል:: በሁለተኛ ደረጃ ሴቶቹ በማዕከሉ የምግብ አገልግሎት ያገኛሉ:: ሦስተኛ ደግሞ የተሟላ የማደሪያ አገልግሎት ያገኛሉ:: ሴቶቹ ከዚህ ቀደም የነበሩበት ሕይወት ጥሩ ስላልነበር መሠረታዊ ፍላጎቶቻው በማዕከሉ በበቂ ሁኔታ እንዲሟሉ ይደረጋል::
እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከተሟሉላቸው በኋላ ወደ ሥልጠና ከመሄዳቸው በፊት ለሥልጠናው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና በፊት ከነበሩበት ሕይወት ወጥተው ወደራሳቸው ቀልብ እንዲመለሱ ተከታታይነት ያላቸው የሥነ ልቦና፣ ማይንድ ሴት፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠዎች ይሰጣቸዋል:: እነዚህን የተሐድሶ ሥልጠናዎች ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ክህሎት ሥልጠና እንዲገቡ ይደረጋል:: በማዕከሉ በርካታ የክህሎት ሥልጠናዎች አሉ:: ሴቶቹ ወደነዚህ የክህሎት ሥልጠናዎች የሚገቡትም የሚፈልጉትን ሙያ መርጠው ነው::
ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ፣ ልብስ ስፌት፣ ጥልፍና የሹራብ ሥራ ሥልጠናዎች አሉ:: እነዚህን ሥልጠናዎች በሚገባ ይሠለጥናሉ፤ ይሠራሉ:: በተመሳሳይ በሥነ ውበትና የፀጉር ሥራም ሥልጠናዎችን ይወስዳሉ:: የቧንቧ፣ ኤሌክትሪክና የከተማ ግብርና ማለትም በከብት ማደለብ፣ በወተት ላሞች፣ ዶሮ ሥጋና የእንቁላል ተዋፅዖ ሥራዎችም ሴቶቹ በተጨማሪነት የሚያገኟቸው ሥልጠናዎች ናቸው:: የሕፃናት እንክብካቤ፣ የምግብ ዝግጅት፣ በቤት አያያዝ፣ ልብስ ንፅሕና አጠባበቅ ዙሪያም ሥልጠና ያገኛሉ:: ሴቶቹ ወደማዕከሉ ከገቡ አራት ወር የሞላቸው ሲሆን ሥልጠናውን ከሦስት እስከ ስድስት ወር ባለው ግዜ ውስጥ አጠናቀው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል::
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ቀደም ብለው ወደ ማዕከሉ የገቡት 500 ሴቶች ናቸው:: ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደተለያዩ እርዳታ ድርጅቶች ተወስደዋል:: አሁን ሥልጠና ላይ ያሉት በቂ ሥልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው:: እነዚህ ሴቶች ትናንትና ሕይወታቸው ጥሩ እንዳልሆነ ይታወቃል:: ከዚህ አንፃር ሴቶቹ ሥልጠናውን ከተከታተሉ በኋላ ዝምብለው እንዲበተኑና ወደነበረው ሕይወታቸው እንደሚመለሱ አይደረግም:: በዚህ ላይም የከተማ አስተዳደሩ በሁለት መልኩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል::
አንደኛው የሥራ ዕድል ፈጠራ ማመቻቸት ሲሆን ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ንግግር እየተካሄደ ነው:: ሁለተኛው ከተለያዩ ባለሃብቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው:: ስለዚህ ሴቶቹ ከማዕከሉ ከወጡ በኋላ ሥራ ሠርተው ገቢ የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል:: በአሁኑ ዙርም ሴቶቹ ሥልጠናውን አጠናቀው በሙያቸው ሥራ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው::
እንዲህ አይነት ማዕከል ገንብቶ ሴቶችን በተሐድሶና ክህሎት ማሠልጠንና ወደ ሥራ ማሰማራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ልምድ ነው:: ክልሎችም መጥተው ልምድ እየወሰዱበት ይገኛሉ:: ምክንያቱም ክልሎች እዛው ዜጎችን በእንዲህ አይነቱ ማዕከል መያዝ ከቻሉ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ሕይወት መታደግ ይቻላል:: ስለዚህ በቀጣይ ማዕከሉ አቅሙን በደምብ ማሳደግ ከቻለ አንድ ግዜ 2 ሺ ሴቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ ይችላል:: ለዚህ ግን በሂደት ማዕከሉ ልምድ እየወሰደና ራሱን እያጠነከረ መሄድ ይኖርበታል::
ሴቶቹ ወደ ማዕከሉ ከገቡ በኋላ ከዚህ በፊት የነበራቸው የሰውነት ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል:: ከአመለካከት፣ ከአስተሳሰብ፣ ከጤናና ከብዙ ማኅበራዊ አቅጣጫ የጎደላቸው ነበሩ:: ወደ ማዕከሉ ከመጡ ወዲህ ግን ይህ ሁሉ ተቀይሯል:: ሴቶች መሠረታዊ ነገሮች ከተሟሉላቸው፣ ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት ካገኙ የትኛውንም አይነት ሥራ የመሥራት አቅምና ብቃት እንዳላቸው ወደ ማዕከሉ ከገቡት ሴቶች ማረጋገጥ ተችሏል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም