ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን (ጀርሞች) አማካኝነት ሰዎችን፣ እንስሳትንና እፀዋትን የሚያጠቁ በሽታዎችን ለማከምና ስርጭታቸውን ለመግታት ያገለግላሉ፡፡ መድኃኒቶቹ በተደጋጋሚና ያለአግባብ በሰዎችና በእንስሳት ሲወሰዱ ግን የበሽታ አምጪ ጀርሞችን ሙሉ በሙሉ መግደል፣ መቆጣጠር ወይም እርባታቸውን መግታት እየተሳናቸው ከጀርሞቹ ጋር ይላመዳሉ፡፡
መድኃኒቶቹ በበሽታ አምጪ ጀርሞች ለመለመዳቸው ዋነኛዎቹ ምክንያቶች የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅና አያያዝ ልምድ አለመኖር፣ እንስሳትን በጤና ባለሙያ አለማስመርመርና መድኃኒቶችን በእንስሳት ጤና ባለሙያ ምክር ያለመስጠት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
የፀረ ተህዋሲያን ቅሪት ያለበትን የእንስሳት ተዋፅኦ መመገብ፣ ጥቅም ላይ የዋሉ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በአግባቡ አለማስወገድና የጥራት ጉድለት ያለባቸውን ህገወጥ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ለፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውንም ያብራራሉ፡፡
የመድኃኒቶቹ በጀርሞች መለመድ የሚያስከትላቸው አሉታዊ የጤና ጉዳቶች በርካታ መሆናቸውንም ባለሙያዎቹ የሚጠቁሙ ሲሆን፣ የመድኃኒቶቹ መለመድ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከፍ ያለና የማዳን ኃይላቸው ዝቅ ያለ ውድ መድኃኒቶችን ለመጠቀም ከማስገደዱም በላይ አንዳንዴም በሽታውን ለማዳን አማራጭ እስከ ማሳጣት ያደርሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከእንስሳት ወደ ሰውና ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎች የስርጭት መጠን ይጨምራል፡፡
የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዜጎች ጤና ስጋት እየሆኑ ከመጡ ችግሮች ውስጥ ዋነኛው መሆኑን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ፣ በኢትዮጵያም ችግሩ ለሰዎች፣ ለእንስሳት፣ ለአካባቢ እና ኢኮኖሚ ከፍተኛ ስጋት ሆኗል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ተላላፊ በሽታዎች በስፋት የሚታዩባት መሆኗ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ በየዓመቱ 100 ሺ የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ ችግር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ እና አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቱም የ5 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ እንደሚገመት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኬይረዲን ረዲ እንደሚሉት፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድን በተቀናጀ ሁኔታ ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ በ2015 እቅድ አፅድቋል፡፡ በኢትዮጵያም ከዚሁ እቅድ ጋር የተጣጣመ ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
ስትራቴጂው የተለያዩ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት ቢሆንም፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በቁጥጥር ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም በጀትና ባለሙያዎችን በመመደብ፣ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ አማካሪ ኮሚቴዎችን በማዋቀርና እቅዶችንና የማስፈፀሚያ የህግ ማእቀፎችን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የመድኃኒቶችን ደህንነት፣ ጥራት፣ ፈዋሽነትና አግባብነት በማረጋገጥ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች ተለምደው በሰዎች ጤና ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት መቀነስ ይቻላል ይላሉ፡፡ህብረተሰቡን በቁጥጥር ሥራዎች ላይ ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ህገወጥ የመድኃኒት አዘዋዋሪዎችን በመቆጣጠር ህጋዊ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ፤የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር ብሎም የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት አግባባዊ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች አጠቃቀም እንዲተገብሩ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በተቀመጠው አሰራር መሰረት የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማያደርጉ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላይም አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መለመድ በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ በርካታ ችግሮችን እየፈጠረ መሆኑን የሚጠቅሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጉዳዩ የአንድ የዘርፍ መሥሪያ ቤት ሥራ ብቻ አይደለም ይላሉ፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጉዳቱን ለመቀነስ ፈጣን ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበው፣ ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመቀነስ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ሥልጠናዎችን በመስጠት የተጀመሩ የህብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥና የንቅናቄ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመድኃኒት ብግርነት/ የዳሰሳ ጥናት ተጠሪ ወይዘሮ ራጂያ አቡበከር የመድኃኒት ብግርነት ወይም የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማሉ፡፡ በመድኃኒቶቹ በጀርሞች መለመድ ምክንያት ሰዎች የሚይዟቸው በሽታዎች የማይድኑ መሆናቸውና በሽታዎቹን ሊያድኑ የሚችሉ መድኃኒቶች አለመፈብረክ ደግሞ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ያብራራሉ፡፡
ተጠሪዋ እንደሚሉት፤ የችግሩን አሳሳቢነት ለመቀነስና በተለይም ሰዎች ያለሐኪም ትእዛዝ መድኃኒቶችን የመውሰዳቸው ልምድ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ መድኃኒቶቹን ለሚያስፈልጉ በሽታዎች ብቻ በትክክለኛው መጠንና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ሌሎች አካባቢያዊ ምክንያቶች በተለይም እንስሳት ለመድኃኒት ብግርነት አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው የእንስሳት ጤና አጠባበቅና አያያዝ ልምድን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ደካማ በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃንም ህብረተሰቡን በማስገንዘብ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ እንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የብሔራዊ ፀረ ተህዋሲያን አማካሪ ኮሚቴ ተጠሪ ወይዘሮ ሃያት ሰይድ እንደሚገልፁት፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የሚያሳስበው አንድ ዘርፍን ብቻ ሳይሆን፣ በእንስሳት ጤና ላይም ተመሳሳይ ችግሮችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በተለይም እንስሳት መድኃኒት ከወሰዱ በኋላ ታክመው መዳን ካልቻሉ በሽታውን መቆጣጠር ስለማይቻልና ለሞት ስለሚዳርጋቸው በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ ጉዳት ያስከትላል፤ በዚህም አርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ያሳያል፡፡
እንደ ተጠሪዋ አባባል፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን የተላመዱ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን መመገብ በሽታው በቀላሉ ወደ ሰዎች የሚተላለፍበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በጤንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ እንስሳትን በፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች ማዳን የማይቻል ከሆነ መድኃኒቶቹ በጀርሞቹ ስለሚለመዱና ከመጀመሪያው የመድኃኒት ዋጋ ውድ የሆኑ መድኃኒቶችን ለመጠቀም ስለሚያስገድዱ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የሚያስከትሉት ጉዳት መጠነ ሰፊ ነው፡፡ ችግሩ አዲስ ከመሆኑ አኳያና ህብረተሰቡም መድኃኒቶቹ በሽታዎችን መፈወስ እንዳልቻሉ እንጂ ለምን መፈወስ እንዳልቻሉ በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ሰፊ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል፡፡
ተጠሪዋ እንደሚሉት፤ ችግሩን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን ለጤና ባለሙያዎችና ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የህብረተሰብ ንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት በህገ ወጥ መንገድ የተገኙና ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ መድኃኒቶች የጤና ጉዳት እንደሚያስከትሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባሮች እየተከናወኑ ነው፡፡ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች ሀገር አቀፍ ስትራቴጂው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዘቦች ክልሎች እንዲወረድ ተደርጓል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት የመሰረታዊ መድኃኒቶች ፕሮግራም የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ መንግስታብ ወልደ አረጋይ፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ዓለም አቀፋዊ ችግር እየሆነ መጥቷል ይላሉ፡፡ መድኃኒቶቹ ጀርሞቹን በቀላሉ መለማመድ እንደሚችሉም የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ ሀገራት በሰብሰባቸው መረጃዎችን ለማረጋገጥ መቻሉን፣ በአሁኑ ወቅትም በርካታ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በበሽታ አምጪ ጀርሞች መለመዳቸውን አብራርተው፣ ለአብነትም በአባላዘር በሽታ፣ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ፣ ቲቢ፣ ወባና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ይገኙበታል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድን ለመፍታት የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2015 ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅትና ከዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ጋር በመሆን በአምስት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ አውጥቷል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለህብረተሰቡና ለጤና ባለሙያዎች መስጠት፣ የቅኝትና የምርምር ሥራዎችን ማጠናከር፣ ህብረተሰቡን ከተላላፊ በሽታዎች ለመከላከል የኢንፌክሽን መከላከል ሥራውን ማሻሻልና የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን እደላ፣ ማጓጓዝና ቁጥጥርን ውጤታማ ማድረግ ስትራቴጂው ካቀፋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድን ለመከላከል ሀገራት ስትራቴ ጂዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲያደርጉ በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም ስትራቴጂውን በጤና ሥርዓት ውስጥ በማካተት ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የፋርማሲ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ይድነቃቸው ደገፋው እንደሚገልፁት፤ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት አንፃር ሲታይ እየተባባሰ በመምጣቱ ችግሩን ለመፍታት በርካታ ተግባሮችን ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በስሩ ባሉ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችም ስፋት ያላቸው ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግሮችን ለመከላከል በእቅድ ከተያዙ አምስት ስትራቴጂዎች መካከል በተለይ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን አጠንክሮ እየሠራም ነው። ችግሩን ለመከላከል የሚሠሩ ሥራዎች ተቀናጅተው የሚሄዱበትን መንገድም ያመቻቻል፡፡ በቅርቡም ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር የመከላከል ሥራዎቹን ማን እያከናወናቸው እንደሆነና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ የሚያስችል የተደራጀ መረጃ ለማግኘት መሥራት ጀምሯል፡፡ በቀጣይም ሥራዎቹ በትክክል እየተሠሩ ስለመሆናቸውና እያንዳንዳቸው የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ስትራቴጂዎቹን ስለማካተታቸው ክትትልና ግምገማ ይካሄዳል፡፡
የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በአሁኑ ወቅት ለሰው፣ ለእንስሳትና ለአካባቢ ጤና እንዲሁም ለኢኮኖሚ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ እንደመጣ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት የጋራ ርብርብ ካልተደረገበት በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅእኖ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል በርካታ ወገኖች ይስማማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011
አስናቀ ፀጋዬ
Thank you for sharing your personal experience and wisdom with us Your words are so encouraging and uplifting