ግዛትና ደስታ፤ ግዞትና ዋይታ

ግዛት እና ግዞት በአፋዊ (ድምፁ) ቃሉ እና በፊደሉ አብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆኑም ቅሉ የተወሰኑ የሚያለያዩዋቸው ፍቺዎች አሉ :: ያው የተወሰኑ የሚያመሳስሏቸው ፊደሎቻቸውና ድምጾቻቸው ትርጓሜዎቻቸው ጭምር መሆኑ ሳይዘነጋ::

ግዛትና ግዞት በዘመናቸው ሁነኛ ቃላት እንዳልነበሩ ዛሬ መናኛ ሆነው ቀሩ:: ጃጁ፣ አረጁ፤ በእኛ ደግሞ ካረጁ አይበጁ የሚባል ነገር አለ:: ቃላቶቹ እምብዛም አገልግሎት ላይ ሲውሉ አይሰሙም ፣ አይነበቡም :: በነቢብም (theory) በገቢርም (practice) ጠፉ ወይም ቅርስ ቃላት፤ አልያም ቅሪተ ቃላት ሆነው ሊሆን ይችላል ብለን እንገምት:: መገመት ፣ መላ መምታት እንጂ ማምታታት አንችልም:: የቀረውን ለስነ ልሳን ምሁራን እንተወዋቀለን :: (እዚህ ላይ ግዛት ሲባል፤ መግዛት መሸመት የሚለውን ፍቺ ሳይካተት መሆኑ ነው ታዲያ) ያው ግን ቃላቶቹ ከከበርቴው ሥርዓት ጋር ወድቀው የቀሩ ቃላቶች ይመስላሉ:: ዴሞክራሲያዊ ፣ አፋዊም አልያም ብዕራዊም መብታችሁን ተጠቅማችሁ የበዝባዥ ርዝራዥ ቃላቶች በሉዋቸው::

ግዛትን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሲፈታው የተወሰነ የአስተዳደር ክልል ይለዋል:: በእንግሊዝኛ State አቻው ነው :: ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሲባል የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች መሆኑ ይታወቃል:: ገዛ ሲባልም አስተዳዳሪ፣ መሪ ወይም ባለሥልጣን ፣ መራ፣ አስተዳደር፣ አፈራ አበጀ በገንዘቡ ወዳጅ ገዛ ማለትም ነው:: ገዥ የሚለው ቃልም የበላይ አስተዳዳሪ፣ ባለሥልጣን የሚል ብያኔ አለው ፤ በጥንቱ ዘመን ሀገር ገዢ ይባል ነበር:: አስተዳዳሪ መሪ ለማለት :: በዘመናችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተዳዳሪ የብሔራዊ ባንክ ገዢ በሚል ስያሜ ይጠራሉ::

ምዕራባውያን የአፍሪካንና የሌሎች አህጉሮችን ቅኝ በመግዛት ሰዎችን እንደ ባርያ በመሸጥ፣ ቀጥሎም ሀብት ንብረት በመመዝበር ወደ ሀገራቸው ያግዙ ነበር :: ለቅኝ ገዥው ሀገር የያዘው የሰው መሬት ግዛት ሲሆን፤ ለቅኝ ተገዥው ሀገር ደግሞ የገዛ ሀገሩ ምድሩ ግዞት የሆነበት ማለት ነው:: ቅኝ ገዥው በያዘው መሬት በሚበዘብዘው ጉልበት በሚመዘብረው ሀብት ወዘተ ይዝናናበታል :: ቅኝ ተገዥው ዜጋ ደግሞ ዕትብቱ በተቀበረት ሀገሩ ጉልበቱና ሀብቱ ሲበዘበዝ ያዝንበታል::

በሌላ አባባል ቅኝ ገዥዎች በሰው ግዛት ሲያጌጡበት፤ ቅኝ ተገዥዎች ግን ግዛታቸው ግዞታቸው ይሆንና ይቀጡበታል፤ይቀጠቀጡበታል:: ለዚህ ነው ግዛትና ደስታ ግዞትና ዋይታ ያልነው:: እናም በግዛት ይዝናኑበታል ፣ይሞላቀቁበታል ፣ በግዞት ደግሞ፤ ያዝኑበታል ፣ ይሳቀቁበታል:: በዘመናችን በሀብት የበለጸጉት ምዕራባውያን የሌሎች ሀገሮችን መሬት ይዘው ጉልበት እየበዘበዘቡ የማዕድን ሀብቶች በቁፋሮ በማስወጣት፤ ባካበቱት ሀብት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው::

በፈሊጣዊ አነጋገርም ‹‹ግዛቱን ጠቅልሎ ያዘ›› ሲባል ሁሉንም ቦታዎች ተቆጣጠሮ ያዘ ማለት ነው:: በቀድሞ ዘመን በጦር፣ በዘመናችን ደግሞ በብር (ኢንቨስተር ) መሬትን እንደመያዝ እንበለው :: ልዩነቱ የቀድሞው ዘመን ግዛት በጦር በግድ የሚያዝ ሲሆን በዘመናችን ግን ባለ ሀብቱ ሀብት ንብረት ለማፍራት ለዜጎች የሥራ እድል ለመስጠት ግዛቱ መሬቱ በብር በውድ የሚያዝ ነው:: ወደው ፈቅደው መንግሥትም ፈቅዶበት :: እዚህ ላይ አንድ ሀገር ለሰዎች ግዛትም ግዞትም የሚሆንበት አመክንዮ እንዳለ ማስታወስ ያሻል:: ቅኝ ለሚገዛው ሀገር ግዛቱ ሲሆንለት ቅኝ ለተያዘው ተወላጅ ሀገሩ ግዞቱ ይሆንበታል::

በሀገራችን በንጉሡ ዘመን የነበረው አስተዳደር ጠቅላይ ግዛት የሚባል ስያሜ ይጠራ ነበር:: ደረጃው በወታደራዊ ዘመን እንደነበረው ክፍለ ሀገር እና ከዘመናችን ክልል ጋር አቻ ነበር ማለት ይቻላል:: አቻ ነው ያልኩት የሥልጣን ደረጃቸውን ሳይሆን የክልል አስተዳደራቸውን መሆኑን እንድታውቁልኝ እሻለሁ:: ይሁን እንጂ አስተዳደሩን ሁሉ ሲያጣጥሉ ሲያብጠለጥሉ የሚውሉ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ‹‹ያም ዘውዳዊ ይሄም ዘውጋዊ ›› የሚሉ አሉ:: አንዳንዶቹ ሲናገሩም ያም የዘውድ ሐረግ ፣ይሄም የዘር ሐረግ ስለሚሳሳቡ፤ መሳ ለመሳ ናቸው ይላሉ:: ዝም ከተባሉ ዘውዳዊ እና ወታደራዊና ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተመሳሳይ ናቸው ሊሉን ነው:: እነሱ ምንም ቢሉም እኛ ግን የሚበጀን ዴሞክራሲ ነው::ሞናርኪ፣ አናርኪና ቢሮክራሲን ወደዛ ጣሉልን::

በንጉሡ ዘመን የነበረው ጠቅላይ ግዛት በሥሩ አውራጃዎችና ወረዳዎችን ያካተተ ነበር:: ግዛት የሚለውን ቃል አንዳንድ መዝገበ ቃላቶች ወረዳ ፣አውራጃ፣ ቀበሌ ይዞታ ርስት ጉልት መንግሥት መክ 6፥2 ሕዝ 29 ፥18 በሚል ይፈቱታል:: በደርግ ዘመን የነበረው የክፍለ ሀገር አስተዳደር በውስጡ አውራጃዎች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንደነበሩት ይታወሳል::

በዘመናችን ያለው አገዛዝ ደግሞ ወይም አስተዳደር በክልል ተከፋፍሎ በሥር በሥሩ የዞኖችና ወረዳዎችን አስተዳደር የሚያካትት ነው:: የቀበሌዎች አስተዳደር በወረዳ ሥር እንዲዋቀር ተደረገ :: ማለትም አራት አምስት ቀበሌዎች በአንድ ወረዳ ሥር እንዲዋቀሩ ተደርገው ተጨፈለቁ:: ያው ቀበሌ ተቀበረ እንበለው :: የት ነው የተቀበረው ? እንዳትሉ ብቻ:: ነፍስ ይማር ማለት ግን መብታችሁ ነው::

የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ግዞት የሚለውን ቃል ሥርወ ቃሉ ጋዘ የሚለው ነው:: ብያኔው ሁለት ዓይነት ነው :: ተጋዘ ሲባል በግዞት ተወሰደ ማለት ሲሆን በሌላ ብያኔውም አንድ እቃ ከቦታ ወደ ቦታ ተወሰደ፣ ወይም ተጓጓዘ ይለዋል:: አጋዘ ሲባልም እቃን ከቦታ ቦታ ወሰደ ወይም አጓጓዘ ማለት ነው:: የቁም እሥር ሲባልም ሳይታሰር የተጋዘ፣ ከዚህ አትለፍ የተባለ ሰው ነው ሲል መዝገበ ቃላቱ ይገልፃል::

በሌላኛው ብያኔ ስንመጣ ግዞት የሚለውን ቃል አንድን ሰው ከሚኖርበት አካባቢ አንስቶ ወደ ሌላ አካባቢ በመውሰድ በዚያው ቦታ ብቻ ተወስኖ እንዲቆይ የሚደረግበት የእስራት ዓይነት ነው:: አሁን ግዞት ተብሎ የሚታወቅ የእስራት ዓይነት የለም :: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ለዚህ ዓይነት ኢፍትሐዊ እስራት ክፍተት አይሰጥም:: ግዞተኛ ማለትም በግዞት ያለ ሰው ማለት ነው:: ተጋዘ ሲባል በግዞት እንዲቀመጥ ተደረገ :: አጋዘ በተመሳሳይ በግዞት አስቀመጠ ማለት ነው :: አንዳንድ ብያኔዎችም ግዞት የሚለውን ቃል (ግእዝት) ፤ ሽረት እስራት ቅጣት ውርደት :: ኢሳ 42፥7 ማቴ 5፥25 ግዞተኛ የተጋዘ ፣ የተሸፈነ፣ የታሰረ እስረኛ ግዞተኝነት እሥረኛነት በሚል ይፈቱታል:: መጽሐፍ ቅዱስም በግዞት ውስጥ ለነበሩት ነፍሳት ነፃነትን ሰበከላቸው ይላል::

የተለያዩ የአማርኛ መዝገበ ቃላቶች ለማየት እንደሞከርኩት ግዞት የሚለውን ቃል እንደ እስራት አድርገው ብቻ ነው ያስቀመጡት:: ነገር ግን በነገሥታቱ ዘመን በነበረው አገዛዝ መሠረት አቅራቢያቸው ያለ ሹመኛ፤ ንጉሡ ካልጣማቸው፣ አልያም በዙፋኔ ላይ ሴራ ይሸርባል፣ አልጋዬን ለመገልበጥ ያስባል ብለው የሚጠራጠሩ ከሆነ፣ ወይም ዐይነ ጥላው ከከበዳቸው ነገሥታቱ ካሉበት ራቅ ወዳለ ግዛት አልያም ወደ ጠረፍ አካባቢ በግዛት አስተዳዳሪነት በሹመት ይልኩታል:: አንዳንድ መጽሐፎች ግን በነገሥታቱ ራቅ ብሎ ወደ ጠረፍ አካባቢዎች እንዲያስተዳድር የተደረገ ግለሰብ ወይም ሹመኛ አስተዳዳሪ ፤ በነፃነት ቢያስተዳድርም ዓላማው ግን ንጉሡ ሹመኛውን ከቤተመንግሥታቸው ራቅ ለማድረግ የሚሰጥ ሹመትን፤ ግዞት ነው ይሉታል :: በወቅቱ ሥረ ታሪኩን የሚያውቁ በግዞት መልክ ተሾሙ እያሉ ይጽፉ ነበር:: ሲብስ ደግሞ በአቅራቢያቸው ክፉኛ የሚያዩት ሹመኛ ካለ ወደ ግዞት ይወስዱታል:: በሹመት መልክ ሳይሆን በእስራት ማለት ነው:: የት እንደታሠረ ግን የሚያውቁት ንጉሡና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ብቻ ናቸው::

ከዚሁ ጋር የተያያዘ ከቃላቱ የሚመሳሰል ግዝት የሚባል ቃል አለ:: ግዝት ማለት፣ መገዘት፣ መ፞ገዘት ( ማለትም ገዘተ ፣ተገዘተ ፤ ሲጠብቅ ሲላላ) ዓይነት ፍቺዎች ማለትም ገዘቱት፣ ተገዘተ ዓይነት ብያኔዎች:: ነገርን ነገር ያነሳዋልና ኦላና ዞጋ ግዝትና ግዞት የሚል መጽሐፍ አላቸው :: መጽሐፉ ስለ መጫና ቱሉማ መረዳጃ ማኅበር ታሪክ የሚያትት ነው:: መጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር ሆኖ በ1955 ዓ.ም በኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢመሠረትም በ1959 በንጉሡ መንግሥት እገዳ ተጣለበት:: ደርግ ሲተካም ማኅበሩን ሊመሠረት አልቻለም:: የደርግ አመራሮችም ማኅበሩን የጎሪጥ እያዩት ስለነበር በድጋሚ ተመሥርቶ መቀጠል አልቻለም:: ለማኅበራዊ ዓላማ የተመሠረተውን ማኅበር ሲገፉት ሲገፉት ወደ ፖለቲካው ከተቱት:: ደርግ ሲወድቅ በድጋሚ መረዳጃ ማኅበሩ በ1984 ቢመሠረትም እንደገና በ1996 ታገደ::

ግዝት መሃላ ፣ክልከላ፣ ውግዣ፣ ርግማን ማለት ነው:: በቀደሙት ዘመናት ቃላቶቹን ከሃይማኖት ያፈነገጠን ሃሳዊ መምህር ወይም መናፍቅን ለማግለል፤ ሲጠቀሙበት የሚሰጡት ስያሜ ነው :: ማውገዝ ፤ አወገዘ፣ ተወገዘ ይባላል:: ምንም እንኳን መገዘት ብዙም ከጽሁፍ እየጠፋ ቢሄድም ፤ በዘመናችን የዓለም ሀገሮችን ያስተሳሰረው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ወዘተ የበለጠ በመጠንከሩ በሀገሮች መካከል ግንኙነት ሲሻክር ዲፕሎማሲያዊ ፣ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀብ በመጣልና ርዳታና ብድር በመከልከል ግንኙነቱን ለማሻሻል ይጥራሉ:: ‹‹የተገዘተች ነፍስ፤ የተለጎመች ፈረስ›› የሚለው ምሳሌያዊ ብሂልም ስለመገዘት፣ መወገዝ የሚነገረን ነገር አለ:: እናም ማዕቀብ ግዞት ከሚለው ቃል ተቀራራቢ ይመስላል::

ማዕቀብ ማገድ፣ መታገድ፣ ታገደ ፣ መገደብ፣ ገደብ ማለት ነው:: ( adoption of sanction ,embargo, prohibit ) በብዛት ያደጉት ሀገሮች ታዳጊ ሀገሮችን እኛ የምናደርገው ደግፉ፤ ከእኛ ውሳኔ አትለፉ ፣ የምንተነፍሰውን ተንፍሱ፣ የምንለውን በሉ፣ የሚሉት ሀገርና አመራር ችላ ሲላቸው እንዲደግፋቸው ለማድረግ የሚያደርጉበት ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጫና ነው:: ይህም ላይ ከጠቀስነው ማውገዝ ፣ግዝት ከሚሉት ቃላት ጋር ይመሳሰላል:: ግዝት ሲባል በብዛት ግለሰብ አልያም ቡድን ተኮር ናቸው :: በብዛት ማዕቀብ የሚለው ግን በሀገሮች ላይ የሚደረግ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ዲፖሎማሲያዊ ጫና አልያም ተፅዕኖ መሆኑ ነው ልዩነቱ::

ይቤ ከደጃች.ውቤ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You