
እስራኤል እና ሃማስ በጋዛ አዲስ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረስ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ በኳታር እያደረጉት ያለው ንግግር እስራኤል ባቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምክንያት እየተጓተተ እንደሆነና ሊፈርስም ጫፍ ላይ መሆኑን ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ‹‹የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከቀናት በፊት ወደ ዋሽንግተን ዲ.ሲ ባደረጉት ጉዞ እስራኤል ጊዜ ገዝታለች›› ሲሉ ተናግረዋል። እስራኤል በዋና ዋና አከራካሪ ነጥቦች ላይ ውሳኔ ለመስጠት እውነተኛ ስልጣን የሌለውን ልዑካን ወደ ዶሃ በመላክ ሆን ብላ ሂደቱ እንዲቆም አድርጋለች ሲሉም ከስሰዋል።
ከእነዚህ የንግግር ነጥቦች መካከል የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ እና የሠብዓዊ ርዳታ እንዲሰራጭ የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል። እስራኤል ግን ወታደሮቿን በጋዛ የማቆየት ሃሳብን እያራመደች ትገኛለች። እንዲያውም እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ራፋህ አካባቢ ወደሚገነባ ካምፕ የማዛወር እቅድ እንዳላት እየተገለፀ ነው።
ካለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ የእስራኤል እና የሃማስ ተደራዳሪዎች በዶሃ በተለያዩ ስፍራዎች ውስጥ ተቀምጠው ስምንት ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮችን አድርገዋል። ንግግሮቹ የተመቻቹት በኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱል ራህማን አል ታሃኒ እና በግብፅ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ሲሆን የአሜሪካው ተወካዮችም በድርድሩ ላይ ተገኝተዋል። አደራዳሪዎቹ በሃማስ እና በእስራኤል ልዑካን መካከል በርካታ የቃልና የጽሁፍ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ይሁን እንጂ ሁለቱ ወገኖች በበርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም በእጅጉ የተራራቀ በመሆኑ ድርድሩ ሊፈርስ እንደተቃረበ ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለስልጣናት ለ‹ቢቢሲ› ተናግረዋል።
የመጨረሻዎቹ ንግግሮች በጋዛ የሠብዓዊ
ርዳታ በሚደርስበት እና የእስራኤል ጦር በምን ያህል ደረጃ ከጋዛ ለቅቆ ይወጣል በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል። ሀማስ፤ የሠብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ መግባትና መሰራጨት ያለበት በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እና በዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች በኩል ነው በሚለው አቋሙ ጸንቷል። እስራኤል በበኩሏ፤ የርዳታ ስርጭቱ ‹‹የጋዛ የሠብዓዊ ርዳታ ፋውንዴሽን›› (Gaza Humanitarian Foundation – GHF) በተባለው በእስራኤልና በአሜሪካ በሚደገፈው የርዳታ አቅርቦት ሥርዓት በኩል እንዲከናወን ግፊት እያደረገች ነው። በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ አደራዳሪዎች እንደሚገልጹት፤ በገዳዩ ላይ ያለውን ልዩነት ማጥበብን በተመለከተ ውስን ውጤት ታይቷል። ነገር ግን መደበኛ ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
ሁለተኛው ዋነኛ አከራካሪ ነጥብ፤ እስራኤል በምን ያህል መጠን ከጋዛ ለቅቃ ትውጣ የሚለውን ጉዳይ የሚመለከት ነው። በአምስተኛው ዙር ንግግር ወቅት፤ የእስራኤል ተደራዳሪዎች እስራኤል ጋዛ ውስጥ ከአንድ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የተገደበ የመከላከያ ቀጣና ይዛ እንደምትቆይ የሚገልጽ የጽሁፍ መልዕክት ለአደራዳሪዎች እንደሰጡ ተዘግቧል። በውይይቶቹ ላይ የተገኙ አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን፤ ሀማስ ይህንን ሃሳብ ለስምምነት መነሻ ነጥብ አድርጎ እንደተመለከተው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ሀማስ፤ እስራኤል ለቅቃ የምትወጣበትን ዞን የሚያሳይ ካርታ እንዲቀርብለት ከጠየቀ በኋላ የተሰጠው ሰነድ ጦሩ እጅጉን ወደ ውስጥ ገብቶ እንደሚሰፍር የሚያሳይ እና አስቀድሞ ከተላለፈው መልዕክት የሚቃረን እንደሆነ ተነግሯል። የቀረበው ካርታ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ሶስት ኪሎ ሜትር ድረስ ጥልቀት ያላቸው የመከላከያ ዞኖች እንደሚኖሩ የሚያመለክት እና በግዛቱ ሰፊ ክፍል ውስጥ እስራኤል እንደምትኖር የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።
የቀረበው እቅድ፤ ደቡባዊውን የራፋህ ከተማ ሙሉ በሙሉ፣ ከኻን ዩኒስ በስተ ምስራቅ የሚገኘውን የኩዛ መንደር 85 በመቶ፣ ሰሜናዊዎቹን የቤት ላሂያ እና ቤት ሐኑን ከተሞችን ሰፊ ክፍሎች እንዲሁም በጋዛ ከተማ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙትን እንደ ቱፋህ፣ ሸጃያ እና ዘይቱን ያሉ ሰፈሮችን በሙሉ ይሸፍናል። የሀማስ ባለስልጣናት የቀረበውን ካርታ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን መተማመን የበለጠ እንዲቀንስ የሚያደርግ እና በእስራኤል በክፉ ልቦና የተፈጸመ ተግባር እንደሆነ አድርገው ቆጥረውታል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት፤ የእስራኤል የልዑካን ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በቅርቡ በዋሺንግተን ላደረጉት ጉብኝት አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ለመፍጠር ሲሉ ሆን ብለው ንግግሩ እንዲጓተት አድርገዋል ሲሉ ይከስሳሉ። ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት ከአሜሪካ ከመመለሳቸው በፊት በጥቂት ቀናት ውስጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል አዎንታዊ አመለካከት መያዛቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
አንድ ከፍተኛ የፍልስጤም ተደራዳሪ ‹‹የእስራኤል ተደራዳሪዎች ንግግሮቹን በጭራሽ በቁም ነገር አይመለከቷቸውም። ንግግሮቹን ጊዜ ለመግዛት እና ውጤት እየተገኘ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ምስል ለማቅረብ ተጠቅመውባቸዋል›› ብለዋል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ እስራኤል በሠብዓዊ እቅድ ሽፋን የረጅም ጊዜ በግዳጅ ማፈናቀል ስትራቴጂን እየተከተለች ነው ብለዋል። የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ባለፈው ሳምንት ለእስራኤላውያን ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሠራዊቱ 600ሺህ ፍልስጤማውያንን የሚያስተናግድ አዲስ ካምፕ በራፋህ እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል። ይህ ቁጥር ግን በኋላ ላይ ወደ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ከፍ ተደርጓል።
በእቅዱ መሠረት፤ ፍልስጤማውያን ወደ ካምፑ ከመግባታቸው በፊት በእስራኤል ኃይሎች የደህንነት ምርመራ የሚደረግባቸው ሲሆን መውጣትም አይፈቀድላቸውም። በርካታ አካላት የካትዝን እቅድ አውግዘዋል፤ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን እና የሕግ ባለሙያዎችም እቅዱን ‹‹የማጎሪያ ካምፕ ንድፍ›› ሲሉ ጠርተውታል።
እስራኤል ካትዝ ፍልስጤማውያንን ራፋህ ውስጥ ወደሚገኝ ‹‹ሠብዓዊ ከተማ›› ለማዛወር ያቀዱት፤ የጋዛ ነዋሪዎችን በቋሚነት ለማፈናቀል የሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል እንደሆነ የፍልስጤሙ ተደራዳሪ ተናግረዋል። ‹‹ሰላማዊ ዜጎችን በግብፅ ድንበር አቅራቢያ የማሰባሰብ ዓላማ፤ በራፋ ወደ ግብጽ በሚሻገረው ወይም በባህር በሚያቋርጠው መስመር እንዲባረሩ መንገድ መጥረግ ነው›› ብለዋል።
ውይይቱ አሳሳቢና መስቀለኛ መንገድ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ በፍልስጤም በኩል ያሉ አካላት አሜሪካ የበለጠ ጠንከር ያለ ጣልቃ ገብነት እንድታደርግ እና እስራኤል ትርጉም ያለው ስምምነት ላይ እንድትደርስ ግፊት እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ አይነቱ ጣልቃ ገብነት የማይደረግ ከሆነ የዶሃው ድርድር ሙሉ በሙሉ ሊፈርስ እንደሚችልም አደራዳሪዎች አስጠንቅቀዋል።
እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ለመፍጠር እና ጋዛ ውስጥ ሰፊ ሠብዓዊ አደጋን ለማስቀረት በቀጣናው የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ያወሳስበዋል ተብሏል። በዶሃ የሚገኙ ዲፕሎማቶች አሁንም ቢሆን ለስምምነት የሚያበቃ ጠባብ መስኮት እንዳለ ይናገራሉ። አንድ ባለስልጣን ‹‹ይህ ሂደት በገመድ ላይ ተንጠልጥሎ ነው ያለው። በከፍተኛ ሁኔታ እና በፍጥነት ካልተለወጠ በስተቀር ወደ መክሸፍ እየሄድን ሊሆን ይችላል›› በማለት ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በበኩላቸው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈረም ከጫፍ እንደደረሰ ተናግረው ነበር። ልዩ መልዕክተኛው በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በሳምንቱ መጨረሻ ስምምነቱ ሊፈረም እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ‹‹በቅርበት እየተወያየን ነው። አራት ጉዳዮች ነበሩ፤ ከሁለት ቀናት ውይይት በኋላ አንድ ጉዳይ ብቻ ቀርቶናል። ስለዚህ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ 60 ቀናት የተኩስ አቁም የሚያደርሰን ስምምነት እንደሚፈረም ተስፋ አለን። የትራምፕ አስተዳደር ስምምነቱ በጋዛ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወደሚያስችል አቅጣጫ እንደሚመራን እምነት አለው›› ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ኪንግደም የተኩስ አቁም ስምምነቱ የማይፈረም ከሆነ በእስራኤል ላይ ርምጃዎችን እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደቪ ላሚ፣ ለሀገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹እስራኤል ለተኩስ አቁምና ለሠብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ዝግጁ ካልሆነች ዩናዩትድ ኪንግደም ርምጃዎችን ትወስዳለች›› ብለዋል። ‹‹የጋዛ የሠብዓዊ ርዳታ ፋውንዴሽን›› ጥሩ ሥራ እየሠራ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
ባለፈው ወር በፍልስጤማውያን ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ አድርገዋል በተባሉት ሁለት የእስራኤል ሚኒስትሮች፤ ኢታማር ቤን-ግቪር እና ቤዛሌል ስሞትሪች ላይ የጉዞ ክልከላና የንብረት እገዳ ማዕቀቦችን ከጣሉ ሀገራት መካከል አንዷ ዩናይትድ ኪንግደም ናት።
ከእዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ እስራኤል ለጋዛ የሠብዓዊ ርዳታ እንዳይደርስ በማድረጓ ዩናይትድ ኪንግደም ከሀገሪቱ ጋር ስታደርገው የነበረውን የነፃ የንግድ ስምምነት ድርድር አቋርጣለች። ባለፈው ዓመት ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ለእስራኤል ታቀርባቸው የነበሩ የአንዳንድ የጦር መሣሪያዎችን ሽያጭ ማቋረጧ ይታወሳል።
እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ ለማቆም በየፊናቸው ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ ሆነው ይታያሉ። እስራኤል ሃማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ትፈልጋለች፤ ሃማስ በበኩሉ እስራኤል ጠቅልላ ከጋዛ እንድትወጣ ይፈልጋል። ተባብሶ በቀጠለው የጋዛ ጦርነት በርካታ ንጹሃን በየቀኑ እየሞቱ እንደሆነና አስከፊ ሠብዓዊ ቀውስ እንደተከሰተም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ባለፈው ጥር 11 ቀን ተጀምሮ ለስድስት ሳምንታት ከዘለቀ በኋላ በመጋቢት ወር አጋማሽ የፈረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ እንኳን ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። የዚህ ስምምነት ሁለተኛው ደረጃ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስን፣ በእስራኤል ውስጥ ለታሠሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ ታግተው የነበሩትን እስራኤላውያን መልቀቅን እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን ያካትት እንደነበር ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም