የኢትዮጵያ የጋዝ ምርት በኢኮኖሚ መነጽር

አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1825 የተፈጥሮ ጋዝን በማውጣት ለኢንዱስትሪ ጥቅም በማዋል ከዓለም ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡ 32 ከመቶ የኃይል አቅርቦቷን የምትሸፍነው በዚሁ ጋዝ መሆኑን የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር እ.ኤ.አ በ2023 ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ይህ ሽፋን በ2025 ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት ሩሲያ 18 ከመቶ፣ አሜሪካ 24 ከመቶ፣ ካናዳ አምሥት ከመቶ፣ ኳታር አራት ከመቶ የተፈጥሮ ጋዝ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በፈረንጆቹ በ2025 የዓለም የተፈጥሮ ጋዝ ፍላጎት አራት ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መድረሱን ገልጾ፤ ተፈላጊነቱ የጨመረበት ምክንያትም ከድንጋይ ከሰልና ከነዳጅ ጋር ሲወዳደር የካርቦን የልቀት መጠኑ አናሳ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል። ይህም የተፈጥሮ ጋዝን ለሃይል ምንጭ መጠቀም ተመራጭና ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የክረምት ረፍታቸውን አጠናቀው ሳይመለሱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት እንደምትጀምር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የምስራች ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከጋዝ አምራች ሀገራት ተርታ የመሰለፏ ጉዳይ እውን ሆኗል፡፡

ለመሆኑ ተፈጥሮ ጋዝ ምንድነው? ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚስ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል? ስንል በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደሳለኝ ገዛኸኝ (ዶ/ር)ን እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባላቸው ማዕድናት ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ወራሽ ጌታነህን ጠይቀናል።

የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደሳለኝ ገዛኸኝ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የተፈጥሮ ጋዝ በቀደመው ጊዜ በተለምዶ አጠራር ጋዝ እየተባለ ይጠራል፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ የዕጽዋትና የእንስሳት ቅሬተ አካላት ለረጅም ጊዜ ኬሚካላዊ ለውጥ በማድረግ የሚፈጥሩት ውህድ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ የሚፈጠረው ካርቦንና ሃይድሮጅን ከተባሉ ንጥረ-ነገሮች መሆኑን አንስተው፤ በኬሚስትሪ አጠራሩ ሃይድሮካርቦን የሚባል ሲሆን ዘይትና ቤንዚንን በውስጡ ይይዛል፡፡ እንደ ጋዝ፣ ዘይት፣ ቤንዚንና ሃይድሮካርቦን ሲቀላቀሉ ፈሳሹ ክሩድኦይል ይባላል፡፡ ስለሆነም የተፈጥሮ ጋዝ በሃይድሮ ካርቦን የበለጸጉ የጋዞች ቅልቅል ነው ይላሉ፡፡

80 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው ሚቴን የተባለው ጋዝ ሲሆን ፕሮፔን፣ ቡቴን፣ ኢቴንና ሌሎችንም ጋዞች ይይዛል፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ሳይጣራ ጥቅም ላይ አይውልም ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፤ በሚይዘው የኬሚካል አይነትና ከመሬት በሚኖረው ጥልቀት መሠረት በውስጡ የያዛቸውን ኬሚካሎች በማስወገድ ወይም በማጣራት እንደሚመረት ይገልጻሉ።

በተጣራው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ አማካኝነት ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ በማስተላለፍ ሃይል ያመነጫል፡፡ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ በተለያዩ ዘዴዎች አማካኝነት የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ኤሌክትሪክ ይለውጠዋል፡፡ ከተፈጥሮ ጋዙ በማጣራት የተለዩት ሌሎች ጋዞች ደግሞ ለሌላ ጥቅም እንደሚውሉ ተናግረዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ ያሉ ሀገሮች ሃያ ከመቶ የሚሆነውን የትራንስፖርት የነዳጅ ፍላጎታቸውን የሚሸፍኑት ከተፈጥሮ ጋዝ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገሮችም ናይጀሪያ፣ አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላቸው ሀገሮች ናቸው።

ሀገራችንም የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከሚገኝባቸው የዓለም ሀገራት ተርታ ተቀላቅላለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ ማቅረብ ትጀምራለች መባሉ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ማዕድናት ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወራሽ ጌታነህ (ፕ/ሮ) በበኩላቸው፤ የተፈጥሮ ጋዝ እንደ ናፍጣ እና ቤንዚን ሁሉ ለትራንስፖርት አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለአየር ትራንስፖርት በተለይ ለመለስተኛ አውሮፕላኖች ይጠቅማል ብለዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ለውሃ ማሞቂያነት፣ ለምግብ ማብሰያነት፣ ለልብስ ማድረቂያነትና ለሌሎችም ተግባራት ይጠቅማል። በገጠር አካባቢም ለምግብ ማብሰያነት ያገለግላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጋዙ ተጣርቶ የሚቀረው ዝቃጭ አሞኒያን በማምረት ለማዳበሪያነት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

ዋጋው ከናፍጣ እና ከቤንዚን ጋር ሲነጻጸርም ዝቅተኛ ነው፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ሌላው ጥቅሙ በፋብሪካ ውስጥ ብርጭቆ፣ ብረታብረት፣ የፕላስቲክ ቀለም፣ የምግብ ውጤቶችንና ሌሎችንም ለማምረት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት እንደምትጀምር መገለጹን አንስተው፤ የኢንዱስትሪው መገንባት ብቻ በገበያው ላይ ከፍተኛ የሥራ እድል እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም ጋዙን በመፈለግ ረገድ፣ በማምረት፣ በማጓጓዝና በማሰራጨት የሚፈጠር የሥራ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የተፈጥሮ ጋዝን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚጠቀሙ እንደፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ፋይበርና ኬሚካል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እና የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ላይ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዲኖራቸው ያስችላል። ይህም በኢትዮጵያ አምራቾች እንዲበራከቱ ያደርጋል ነው ያሉትየተፈጥሮ ጋዝን ማምረት መቻል ከውጭ የሚመጣውን ሲሊንደር በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ያስችላል። ከውጭ የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል። ለአፈር ማዳበሪያው የሚወጣውን ዶላር ይቀንሳል። ከዚህም ባለፈ ማዳበሪያውን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን የትራንስፖርት ወጪ ያስቀራል ብለዋል።

ይህም በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለውን እድገት ከምርትና ምርታማነት አንፃር ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸው፤ በዚህም የግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። በተለይ በተፈጥሮ ጋዝ ተረፈ ምርት የሚመረት ማዳበሪያ ለም በመሆኑ ጤናማ የግብርና ምርቶች ለማምረት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በአንፃሩ ከውጭ ሀገራት የሚገባ ማዳበሪያ ከተፈጥሯዊነቱ ይልቅ የኬሚካል ይዘቱ ከፍ ስለሚል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖሩት አንስተው፤ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት መቻል በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እድገት ለማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት መቻል ኢትዮጵያ ከሃይድሮ ኃይል ባለፈ ሌላ የኢነርጂ ምንጭ እንዲኖራት እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ይህም የኢነርጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከምትከተለው የአረንጓዴ ኢነርጂ ፖሊሲ ጋርም የተጣጣመ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ይህ ማለት ከቤንዚንና ናፍጣ አንፃር የተፈጥሮ ጋዝ በአየር ንብረት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ዝቅተኛ እንደሆነም ተናግረዋል። ኢነርጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ፍላጎት በመሆኑም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን እና ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን ቤዚን አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ የማውጣት ጥረት በይፋ የተጀመረው እ.አ.አ በሰኔ ወር 2018 ሲሆን፣ ፖሊ-ጂሲኤል የተሰኘ የቻይና ኩባንያ በሶማሌ ክልል በሚገኙት የካሉብ እና ሂላላ የጋዝ መስኮች የሙከራ ምርት አካሂዶ ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት ከሚችሉ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን እውን ማድረግ መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ በቅርቡ ምርቃቱ እንደሚከናወንና ወደ ሁለተኛው ምዕራፍም እንደሚሸጋገር አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት ከጀመረች በሀገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት መኖሩ የማይቀር መሆኑን ሁለቱም ምሁራን ይስማማሉ። በተለይ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በጤና ዘርፎች ከፍተኛ እድገት እንደሚመዘገብ ገልጸዋል። አሁን ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You