ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት እንደ መንግሥት በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በትኩረት እየተሠሩ ከፍ ያለ ውጤት እየተመዘገበባቸው ካሉ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አንዱ ነው:: ይሄ መርሐ ግብር እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈላት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር መፍትሔ ከመሆን ባለፈ፤ ለኢትዮጵያውያን የበዛ ፋይዳ ያለው ነው::
ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚታዩ የድርቅ፣ የጎርፍ፣ የአውሎ ነፋስ፣ ወጀብና ሱናሚ እንዲሁም ሰደድ እሳት እና መሰል አደጋዎች መከሰት መንስኤ ነው:: ኢትዮጵያም የዓለም አንድ አካል እንደመሆኗ የከፋ ድርቅ፣ ጎርፍና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ደጋግመው ጎብኝተዋታል:: በዚህም ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊም ሰብዓዊም ጉዳትን አስተናግዳለች::
ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯ ይሄንን ችግር ለማቃለል የሚያስችል አንድ አቅም ሲሆን፤ ከዚህ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፤ ለአከባቢ ውበት፣ ለመድኃኒት እና መሰል ጉዳዮች አገልግሎት የሚውሉም ናቸው:: መርሐ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ የሚከናወኑ የችግኝ ተከላ ሂደቶችም እነዚህም ማዕከል አድርገው የሚካሄዱ እና ለሀገር በቀል ዕፅዋትም ትኩረት የሰጡ ናቸው::
በዚህ ረገድ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፤ መድኃኒትነት ያላቸውን ዕፅዋት ማብዛት ተችሏል፤ ለምግብነት የሚውሉ እንዲሆም ለገንዘብ ማግኛ (ለገበያ) የሚውሉ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ አይነት ችግኞችን በመትከል ውጤታቸውን ማየት ተችሏል:: በተለይ ለምግብነት የሚውሉ እና ለገበያ የሚሆኑ እንደ አቮካዶ፣ አፕል፣ ፓፓያ፣ ማንጎ እና ቡናን የመሳሰሉት ላይ በሰፊው ተሠርቶባቸዋል፤ ከፍ ያለ ውጤትም አስገኝተዋል::
ለአብነት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት የተተከሉ የአቮካዶ እና ፓፓያ ችግኞች ዛሬ ላይ ለሀገር ውስጥም፣ ለውጪ ገበያም መቅረብ ችለዋል:: በዚህም የሀገር ውስጥ ገበያን ማረጋጋት፤ በወጪ ንግዱም የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት ተችሏል:: በቡና በኩልም ቢሆን ከዓመት ዓመት የቡና ችግኞችን በማብዛት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የቡና ዛፎችን መትከል ተችሏል::
በተለይ ቡና የሀገሪቱ የወጪ ንግድ የጀርባ አጥንት ሆኖ ከመዝለቁ ጋር በተያያዘ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ እየተከናወነ ያለው ተግባር ይሄን አቅምነቱን ከፍ እያደረገው ይገኛል:: ለዚህም ነው ዘንድሮ በቡና የወጪ ንግድ ከወትሮው ከፍ ያለ ቡና በመላክም ሪከርድ የሆነ ገቢ ማግኘትም የተቻለው:: ለዚህ ዐብይ ማሳያ የሚሆነው፤ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሰጠው መግለጫ ነው::
እንደ ባለሥልጣኑ መግለጫ፣ በ2016 በጀት ዓመት 298 ሺህ 500 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: ይሄም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 ሺህ ቶን ብልጫ ያለው ሲሆን፤ በዚህ መልኩ እያደገ ከመጣው የቡና ወጪ ገበያ የሚገኘውን ገቢ ለማላቅ፣ እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ ሌሎች ሀገሮች ከሚያገኙት ገቢ ጋር ለማስተካከል በትኩረት እየሠራ ስለመሆኑም ነው ባለሥልጣኑ ያብራራው::
ይሄን ገለጻ የሚያጠናክረው ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለቡና ችግኝ የተሰጠው ትኩረት ሲሆን፤ ይሄም ከዓመት ዓመት እያደገ በመምጣት ዘንድሮ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኝ ለዚህ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ እየተተከለ ይገኛል:: ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል የደን ሽፋንን የማሳደግ እና የሥራ ዕድል የመፍጠር ግብ ያለው ሲሆን፤ በዋናነት ግን ቡና ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ጥራትም ብዛትም ያለው ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የሚያሳድግ ነው::
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ፣ እንደ ሀገር ካሉት ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መካከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የወጪ ንግድ ምርቶችን በመጠንም በዓይነትም ማሳደግ ነው:: በዚህ ረገድ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የታየው ውጤት ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታን መሸፈን የሚቻልበትን አቅም ፈጥሯል:: እንደ አቮካዶ ባሉ ምርቶችም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማዋልም፣ ለወጪ ገበያ ማቅረብም ተችሏል:: በቡና እና ሌሎች ለወጪ ንግድ አቅም የሚሆኑ ምርቶችን መጠንና ዓይነትንም ማሳደግ አስችሏል::
ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን ማስገኘት የሚያስችሉ ምርቶችን በብዛትና በዓይነት ከፍ በማድረግ የወጪ ምርቶች ዕድገት አቅም መሆኑን በመገንዘብ፤ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለእነዚሁ ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ መከወን ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም