የፖለቲካ ድርጅትነት፣ የፖለቲካ ልሂቃንነት እና የማኅበረሰብ አንቂነት ትርጉም እንዲኖረው!

ተገማችነት እያጣ ባለው አሁናዊ ዓለም እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶችን ተፅዕኖ ለመቋቋም በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገራት እና ሕዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው የሚሠሩበትን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እየፈጠሩ ነው። የቆየ ወዳጅነታቸውንም ስትራቴጂክ ወደሆነ የትብብር ምዕራፍ እያሸጋገሩ ነው።

ይህ ዓይነቱ የሀገራት እና የሕዝቦች አካሄድ፤ ወቅታዊ ስጋቶችን በጋራ ከመከላከል ባለፈም፤ ነገ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ያለብዙ ኪሳራ ለመሻገር፤ ከዚያም አልፎ ፈተናዎችን ወደመልካም አጋጣሚ በመለወጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚያስችል ብዙዎች ይስማማሉ።

ዓለም አቀፋ ሥርዓቶች፤ ሥርዓቶቹ የተገዙበት ሕጎች እና መርሆዎች በተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት አደጋ ውስጥ እየገቡ ባለበት አሁናዊው ዓለም፤ ሀገራት ከሁሉም በላይ ለውስጣዊ ሰላማቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፤ ከግጭት የራቀ የፖለቲካ ባህል እንዲያዳብሩ፤ ለዚህ የሚሆን ማኅበረሰባዊ መነቃቃት እንዲፈጥሩ ይመከራል።

በተለይም በየሀገራቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ማኅበረሰብ አንቂዎች ከግጭት ነፃ የሆነ ማኅበረሰብ በመፍጠር፤ ያሉበት ማኅበረሰብ ተገማች እና ተገማች ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ሰለባ እንዳይሆኑ ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ፤ ለዚህ የሚሆን የተጠያቂነት መንፈስ ማዳበር ይኖርባቸዋል።

ልዩነቶችን በውይይት በሰላማዊ መንገድ መፍታት፤ ይህም አጠቃላይ በሆነው የማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መርሕ የሚሆንበትን የአስተሳሰብ መሠረት መጣል፤ ባህል ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገርበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር፤ ለዚህ የሚሆን የተለወጠ ዘመኑን የሚዋጅ ማንነት መገንባት ይጠበቅባቸዋል።

የሕዝብን ዘላቂ ሰላም እና ከሰላሙ የሚመነጨውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን አደጋ ውስጥ ከሚከቱ የአስተሳሰብ ዝንፈቶች እና የጥፋት ትርክቶች፤ ከአጋጣሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከሚፈጠር የቁመራ እሳቤ እና በሕዝብ የግንዛቤ ክፍተት ለማትረፍ ከሚደረግ ያልተገባ ሩጫ ራሳቸውን መግራት እና መግታት ይኖርባቸዋል።

በተለይም ከሁሉም በላይ የሕዝብ ፍላጎት ሰላም በሆነበት፤ የሰላም እጦት ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ሰላምን ከመፍጠር እና ማጽናት በላይ ተቀዳሚ ተልዕኮ/ሥራ ሊኖራቸው አይገባም።

ልዩነቶችን አስፍቶ የግጭት ምንጭ በማድረግ የሚሰላ የፖለቲካ ትርፍም ሆነ የማንነት ግንባታ፤ ማኅበረሰብን ለተጨማሪ አሁናዊ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ በማጋለጥ የበለጠ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል፤ በዚህም የበለጠ እንዲጎብጥ ከማድረግ ያለፈ ማኅበረሰባዊ/ሀገራዊ ፋይዳ አይኖረውም።

ይህ ደግሞ በራስ ሕዝብ ዛሬ እና ነገዎች ላይ የመፍረድ ትልቅ የክህደት ወንጀል ነው፤ የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪ ትውልድን ዕጣ ፈንታ የሚያደበዝዝ፤ ከዚያም አልፎ የሚያጨልም የጥፋት መንገድ ነው። እስከ መቃብር የሚወርድ የታሪክ እና የትውልድ ተጠያቂነትም የሚያስከትል ነው።

በሀገራችን ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ማኅበረሰብ አንቂዎች ይህንን እውነታ ቆም ብለው በሰከነ መንፈስ እና በተረጋጋ አዕምሮ ሊያስቡት ይገባል። አሁን ላይ ያላቸው የትኛውም አይነት ሀገራዊ ተሳትፎ ለሀገር ሰላም እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያለውን አሉታዊ እና አዎንታዊ አስተዋፅዖ በአግባቡ ሊያጤኑትም ይገባል።

የሕዝባችንን የትናንት መከራ እና ስቃይ በማስቀረት፤ አዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህል በመገንባት እና በማስቀጠል፤ ከዚያም ባለፈ ሕዝባችን በብዙ መስዋዕት እና ተስፋ ለጀመረው ለውጥ ስኬት ያላቸውን አዎንታዊ ተሳትፎ በኃላፊነት መገምገም ይኖርባቸዋል።

እንደሀገር ዛሬ ላይ የተሻሉ ነገዎችን ለመሥራት በተጀመረው ሀገራዊ መነሳሳት ውስጥ ያላቸውን ተጨባጭ አበርክቶ እና የአበርክቶ መነቃቃታቸውን መመዘን፤ ለዚህ የሚሆን ለራስ መታመን መፍጠር እና መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው፤ ፖለቲካ ድርጅትነታቸው፣ የፖለቲካ ልሂቃንነታቸው እና የማኅበረሰብ አንቂነታቸው ትርጉም የሚኖረው!

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You