አገልግሎቱ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት መስጠቱን ገለጸ

– ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም አስታውቋል

አዲስ አበባ፡- የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አንድ ሚሊዮን 465 ሺህ 989 ፓስፖርት መስጠቱን አስታወቀ። ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች 34 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንም ጠቁሟል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ ከመዝጋቢና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገውን ሴክቶሪያል ጉባኤ ትናንት ሲከፍቱ እንዳሉት፤ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተቋሙን ሪፎርም በማድረግ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በእዚህም በ2017 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን 465 ሺህ 989 ፓስፖርት ተሰጥቷል።

በአገልግሎት ማሻሻያው ታግዞ ባከናወናቸው ተግባራት የተቋሙን ዓመታዊ ገቢ 34 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይሄም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ከሁለት እጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ገለጻ፤ አዲሱን የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በአዲስ ሲስተም፣ በጎተራ በሚገኘው ቢሮ የአስቸኳይ አገልግሎት ጀምሯል። ተጨማሪ አዳዲስ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት አጠቃላይ  ቅርንጫፎችን 28 አድርሷል። እነዚህም በ2018 በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል።

የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች በማጸደቅ የተቋሙ አሠራር ይበልጥ ሕጋዊ ሥርዓት የተከተለ እንዲሆን ጥረት መደረጉን የሚናገሩት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ቁልፍ የሕዝብ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት አባል እንድትሆን በማድረግ የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በአባል ሀገራቱ ያለምንም እንግልት እንዲጓጓዙ መደረጉንም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን በጠበቀ አሠራር በአየር እና በየብስ ድንበር በጉዞ ሰነድ አማካኝነት ከሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመው፤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የሚፈጥሩ የማጭበርበርና የማታለል ተግባር፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በኦንላይን አስቸኳይ ፓስፖርት የሚሞሉ 231 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል።

በተመሳሳይ ሦስት ሺህ 868 ግለሰቦች የተጭበርበረ ሰነድ በመጠቀም ፓስፓርት ሊያወጡ ሲሞክሩ በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን ያስረዱት ወይዘሩ ሰላማዊት፤ 12 ሺህ 127 የውጭ ዜጎች ሃሰተኛ ሰነዶችን በመያዝ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ተይዘው አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ተናግረዋል። ሦስት ሺህ 263 የቪዛ እና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳያድሱ የቀሩ ሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውጭ ዜጎችን በመያዝ የክፍያ መመሪያው በሚያዘው መሠረት አስፈላጊውን ውዝፍ ከፍለው ከሀገር እንዲወጡ መደረጉንም አስረድተዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተቋሙ የሚሰበሰበውን የጉዞ ሰነድ፣ የይለፍ መረጃዎች በማዕከል አደራጅቶ በመያዝ፣ ደህንነቱ እንዲጠበቅ በማድረግ እና አጠቃላይ የተቋሙን አሠራሮች በማዘመን አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ እየተሠራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች 75 በመቶው ዲጂታላይዝ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በአጠቃላይ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እያካሄደ ባለው የሪፎርም ሥራ ወረቀት ላይ የተመሠረተ አሰራርን ወደ ዲጂታል ሥርዓት፣ ከቢሮክራሲያዊ አሠራር ወደ ዜጋ-ተኮር አገልግሎት፣ ከተናጠል ጉዞ ይልቅ ወደ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ሽግግር ማድረግ ተችሏል።

በ2018 በጀት ዓመትም የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ የዲጂታል ለውጥን በማጠናቀቅ የተጀመሩ የኦንላይን አገልግሎቶችን በማጠናከርና ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሥርዓት በማሸጋገር፤ እንዲህም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማስፋፋት ለዜጎች ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እውን ለማድረግ ይሠራል።

ለእዚህም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማዊ ችግሮችን ከስር መሠረቱ ለመለወጥ የሕግ ማሕቀፎችን ማሻሻል፣ ተቋማዊ አደረጃጀትን ማስተካከል፣ የሰው ኃይል ክፍተት ማሟላት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ 11 የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይነትም እነዚህን ሥራዎች በማጠናከር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለዜጎች ለመስጠት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You