የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር በር ከፋች ነው

አዲስ አበባ፡- የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ አዳዲስ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለመጀመር በር የሚከፍት ነው ሲል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዓባይ ግድብ ከፍጻሜው ደርሷል። ግድቡ እዚህ እንዲደርስም የኢትዮጵያ ሕዝብም በአንድነት መንፈስ ከልቡ በመደገፍ እና በተግባር አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የሕዝብ እና የመንግሥት መተባበር የታየበት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ይህ መተባበርም በቀጣይ ሌሎች አዳዲስ

የልማት እቅዶች እና መርሃ ግብሮች ለመጀመር በር የሚከፍት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ትልቁ፣ በዓለም ደረጃም አሉ ከሚባሉት አስር ግድቦች አንዱ የሆነው የዓባይ ግድብ፤ በሚያመነጨው አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ከኢትዮጵያ ባሻገር ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን በመጠቆምም፤ ይሄን ግድብ እውን ማድረግ የቻልነው በአንድነት እና በኅብረት በመቆማችን ነው ሲሉ አመላክተዋል።

እንደ አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ በብድር እና በርዳታ ያሳለፈችው ጊዜ በእድገታችን ላይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ እንዳይመጣ አድርጎት ቆይቷል። ዛሬ ላይ ግን የራሳችንን አቅም፣ ጥሪት እና ችሎታ አስተባብረን ስንጠቀም መሥራትም፣ መልማትና ማደግም እንደሚቻል ታይቷል። በመሆኑም በቀጣይ በመተባበር መንፈስ፣ በራስ አቅምና ጥሪት ታግዞ ወደ ልማት እና ሰላም ትኩረት በማድረግ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ማበልጸግ የተገባ ነው።

ግድቡ በክረምቱ መውጫ ላይ እንደሚመረቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መነገሩን ያስታወሱት አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር)፤ የግድቡ ግንባታ ጉዞም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ  አጠቃላይ በሁሉም የሀገራችን ማዕዘን የተባበረበት እና ለፍጻሜ ያበቃው መሆኑን ተናግረዋል። ይሄን ዓይነት የሕዝብ እና የመንግሥት ትብብር በታሪክ አይተው እንደማያውቁም ጠቁመዋል።

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You