የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም ግብይቱን ለማሳለጥ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፤ ይህን ተከትሎም ለውጦችን እያስመዘገበ ነው፤ በተለይ ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ ባደረገው የቀጥታ የገበያ ትስስር የግብይት አማራጭ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በዚህም አምራችና አቅራቢው እንዲሁም ላኪው ቡናውን በቀጥታ ወደ ለውጭ ገበያ መላክ የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በግብይት አማራጩ ቡናን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ቢሆኑም፣ አሁን ላይ ወደ ውጭ ለሚላከው የቡና መጠን እና የገቢ መጠን መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመላክታል።
በቅርቡም ይህንኑ የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ ይበልጥ ለማስፋት ብሎም በግብይት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማረም እንዲቻል ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ አቅራቢዎችንና ላኪዎችን በቀጥታ የሚያገናኝ አውደርዕይ አዘጋጅቷል። አውደርዕዩ የተዘጋጀው በሃዋሳ እና በጅማ ከተሞች ሲሆን፤ የዝግጅት ክፍላችን በጅማ ከተማ በተዘጋጀው አውደርዕይ በመገኘት ከቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል። በዚህ አውደርዕይ ላይ ከጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመጡ ቡና አቅራቢና ላኪዎች ተሳትፈዋል።
ቡና አቅራቢውና ላኪው በቀጥታ በተገናኙበት አውደርዕይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ማዕሩፍ ዓሊ ቡና አቅራቢ ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱ ተወካይ አቶ አህመድ እስማኤል እንዳሉት፤ ከደረጃ ሁለት እስከ ደረጃ አምስት ቡናዎችን በአውደርዕዩ ይዘው ቀርበዋል። የቡናዎቹ መገኛም በጅማ አካባቢ አጋሮና ጌራ ነው። ባለሸሚዝ ወይም የታጠበ ቡናን ጨምሮ ቅሽርና ያልታጠበ ቡና ይዘው ቀርበዋል። አውደርዕዩ ከነባር ገበያዎች በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ ዕድሎች የሚገኙበት እንደሆነና ከላኪው ጋር በቀጥታ በመገናኘት የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ቡና ከማቅረብ ባለፈ በቡና ልማትም የተሠማራ ሲሆን፤ የሚያመርተውን ቡና ጨምሮ በአቅራቢያው ከሚገኙ ቡና አምራቾችም ቡና በመግዛት ለውጭ ገበያ አዘጋጅቶ ያቀርባል። ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውን ቡና በማጠቢያ ጣቢያዎቹ አጥቦ፣ ቀሽሮና አበጥሮ ያቀርባል። ድርጅቱ ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ በቀጥታ መላክ የሚያስችል አቅም ላይ እስኪደርስ ለአቅራቢዎች እያቀረበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ በቀጣይ ልምድ ወስዶ ቡናውን በቀጥታ ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረው የቡና ቀጥታ የገበያ ትስስር ምቹ የገበያ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ ድርጅቱ በቅርቡ ቡና ኤክስፖርት ወደ ማድረጉ ይገባል። እስከዚያው ግን ቡናውን ለኤክስፖርተሮች በቀጥታ የገበያ ትስስር ያቀርባል። ቀጥታ የገበያ ትስስር አምራቹን፣ አቅራቢውንና ላኪውን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ምንም እሴት የማይጨምረውን ደላላ ከመሀል ማስወጣት የቻለና የቡናውን ባለቤት አምራቹን፣ አቅራቢውንና ላኪውን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
እንዲህ አይነት አውደርዕይ ቡና አቅራቢውን በቀጥታ ከላኪው ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የጎላ ጥቅም አለው ሲሉ ጠቅሰው፣ በተለይም የቀጥታ ትስስሩ ገበሬውን ከአቅራቢውና ከተረካቢ ጋር ለማገናኘት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ይሁንና አልፎ አልፎ አቅራቢውና ላኪው በስምምነት ግብይት ፈጽመው ገንዘቡን በወቅቱ ያለማድረስ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ጠቅሰው፣ ለዚህም ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስቀመጠውን ሕግና ደንብ ተከትሎ በመሥራት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
‹‹አውደርዕዩ ከቡና አቅርቦት ጋር ተያይዞ የቡናን ዋጋ ሊያሳምር እና ቡና አቅራቢን ከላኪ ጋር በቀጥታ ማገናኘት የሚችል ነው›› ያሉት ሌላኛው ቡና አቅራቢ አቶ ዝናቡ አባዱራ የዝናቡ አባዱራ ቡና አቅራቢ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ቡና አቅራቢዎች ቡናቸውን በብድር ለላኪዎች በመስጠት መጉላላት ይገጥማቸው ነበር። አሁን ግን ችግሩን መቅረፍ እየተቻለ ነው። የዛሬ ሁለትና ሶስት ዓመት የቡና ቀጥታ የገበያ ትስስር እንደተጀመረ አቅራቢው ቡናውን በብድር ለላኪው በመስጠት ገንዘቡን በወቅቱ አይከፈለውም ነበር። አሁን ግን ችግሩ ተቀርፎ ቡናው የሚንቀሳቀሰው ለአቅራቢው መቶ በመቶ ተከፍሎት ነው። ከዚህ ባለፈም አቅራቢውና ላኪው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ውል የሚገባበትና ግብይት የሚፈጽምበት ዕድል መፈጠሩ የሚበረታታ ነው።
የቡና ቀጥታ የገበያ ትስስር ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ናሙና ብቻ ሳይሆን ሙሉ ቡናውን አይቶ የመግዛት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህም ከፍተኛ መጠንና ጥራት ያለው ቡና ወደ ገበያ መውጣት ችሏል። በቀጥታ የገበያ ትስስር ቡናው ለላኪው ከቀረበ በኋላ አቅራቢው ተደራድሮ በሚያዋጣው ዋጋ መሸጥ ይችላል። ይህም ለአቅራቢውና ለላኪው ብቻ ሳይሆን አምራቹን ጨምሮ ለአጠቃላይ የቡና ቤተሰብ አዋጭና ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንዳሉት፤ ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ተግባራዊ በተደረገው የቡና ቀጥታ የገበያ ትስስር ቡና አቅራቢን ከላኪ በማገናኘት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። እንደሀገር የተገኘውን ለውጥ ለማሳደግም እንዲህ አይነቱ ቡና አቅራቢውን በቀጥታ ከቡና ላኪው ጋር የሚያገናኝ አውደርዕይ ትልቅ አቅም አለው።
ከዚህ ቀደም በምርት ገበያ ብቻ በአስገዳጅ ሁኔታ ቡና ወደ ውጭ ገበያ ይላክ ነበር። ይሁንና ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የግብይት አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ በአዋጅ ሰባት የሚደርሱ የግብይ አማራጮች ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።
ከእነዚህም መካከል ቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ አንዱ ነው። ይህ ማለት ደግሞ በአቅራቢና በላኪው መካከል የሚደረግ የግብይት ሥርዓት ነው። የዚህ የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ አፈጻጸምም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ቡና ወደ ውጭ ገበያ የተላከው በቀጥታ የግብይት ሥርዓት በመገበያየት ነው። የቀጥታ ግብይት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ወደ ውጭ ገበያ የተላከው የቡና መጠን እንዲሁም የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍ ብሏል።
በተለይም በቡና አቅራቢና በላኪ መካከል ያለውን ሶስተኛ አካል በማስቀረት ላኪውና አቅራቢው ተቀራርበውና ተነጋግረው በጋራ በመወሰን ምርት መረካከብ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል። የቀጥታ ገበያ ትስስር በቡና ግብይት እጅግ ወሳኝ የሆነ ለውጥ ያመጣ ሲሆን፤ ይህንን ለማስቀጠልና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይሠራል። ላኪና አቅራቢዎችን እንዲሁም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም በቡና ንግድ እንደ ሀገር ከሚሊዮኖች በመውጣት ወደ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ወደ ማግኘት መግባት ያስቻለ ነው።
‹‹የተገኘውን ውጤት የበለጠ ለማስፋት የቀጥታ የገበያ ትስስሩን አጠናክሮ መቀጠል ይግባል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት የቡና ግብይቱ አንድ ነጥብ አራት አምስት ቢሊዮን ደርሷል› ሲሉም ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም በሃዋሳና በጅማ ከተማ የተዘጋጀውና አቅራቢውን ከላኪው በቀጥታ ያገናኘው አውደርዕይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በሃዋሳ ላይ የተካሄደው አውደርዕይ ውጤታማ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በጅማ የተካሄደው አውደርዕይም እንዲሁ የተሳካ መሆኑን ነው ያመለከቱት። አውደርዕዩ በዋናነት ከዚህ ቀደም የማይተዋወቁ የነበሩትን አቅራቢና ላኪን ፊት ለፊት በማገናኘት ቡናን በጥራትና በብዛት መረካከብ የሚቻልበትን ዕድል ፈጥሯል ሲሉም አስታውቀዋል።
‹‹ከዚህ ቀደም አቅራቢና ላኪ አይተዋወቁም። አቅራቢውም ላኪውም የራሱ ወኪል አለው። ስለዚህ ወኪሎች በመነጋገር የቡና ዋጋና መጠን ይወስናሉ። ይህ ደግሞ አቅራቢውንም ሆነ ላኪውን ተጠቃሚ ያላደረገ በመሆኑ በርካታ ቅሬታዎች ይቀርቡበት ነበር›› ሲሉ ገልጸዋል።
ከነበሩት ቅሬታዎች መካከል ገንዘብ አቀባበልና ክፍያ ላይ የነበሩ ክፍተቶች ይጠቀሳሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቀጥታ የገበያ ትስስር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አማራጭ መፍትሔ እንደሆነ አስረድተዋል። ይህንንም ሲያስረዱ ባለቤት የሆነው ቡና አቅራቢና ባለቤት የሆነው ቡና ገዢ መገናኘት እንዳለባቸውና ውሳኔ መወሰን የሚችሉትም እነሱ ብቻ እንደሆኑ ነው። ለዚህም መሀል ላይ ያለውን ሶስተኛ ወገን ማስወጣት ተችሏል። በዚህም አቅራቢና ገዢው በዋጋና በጥራት መደራደር ይችላሉ። ክፍያውን በተመለከተም ወዲያው መቀባበል የሚችሉበት ሥርዓት በመኖሩ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ግብይት መፈጸም ይችላሉ።
ቀጥታ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ በሆነበት ወቅት ክፍያ የማዘግየት ችግር የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሲያስረዱ ቡና አቅራቢው ቡናውን ለላኪው ሲያስረክብ ሙሉ ለሙሉ ክፍያ መፈጸም እንዳለበት መመሪያው አስቀምጧል። ይሁንና በወቅቱ አንዳንድ አቅራቢዎች ገንዘብ ሳይወስዱ ወስደናል ብለው ፈርመው ለላኪው ይሰጣሉ። ላኪዎችም በተመሳሳይ ከፍለናል በሚል ሲረካከቡ ነበር። ያም ሆኖ ታዲያ በወቅቱ በርካታ ችግሮች ተስተውለዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በወቅቱ የነበሩትን በሙሉ በማጣራት አሁን ላይ መቶ በመቶ ክፍያ ያልተፈጸመበት ቡና ሽኝት አይደረግለትም። በመሆኑም እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት እና በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግር የሚፈጠርበት ዕድል የለም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አቅራቢውንና ላኪውን በማገናኘት መረካከብ እንዲችሉ አድርጓል። ይሁንና አሁን ላይ እንዲህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር ባሉት 13 የሽኝት ጣቢያዎች ላይ ከላኪ አካውንት ወደ አቅራቢ አካውንት ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አቅራቢው ይዞ ሲመጣ ብቻ የሚተላለፍ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ክፍያ አልተፈጸመልኝም ብሎ የሚመጣ አቅራቢ ካለ በራሱ ጊዜ የሰራው ስህተት በመሆኑ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በወንጀል የሚጠይቀው ይሆናል።
ሌላው ለቡና ሥራ ብር ከባንክ ተበድረው ሌላ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ ላኪዎች እንደነበሩ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም ችግር ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ለማስተካከል መሠራቱን ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በብቃት ማረጋገጫ ብቻ ብድር እንዳይሰጥ መደረጉንም ገልጸዋል። ይህም ማለት ከዚህ ቀደም በብቃት ማረጋገጫ ብቻ ብድር ይወስዱና ሌላ ሥራ የሚወስዱ ነበሩ። አሁን ላይ ግን ብቃት ማረጋገጫው ብቻ ዋስትና እንዳይሆን ተደርጓል። በሌላ በኩል ለአቅራቢዎች ብድር ሳይመቻች መቆየቱን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ማስተካከል እንዲቻል ከባንኮች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አቅራቢዎችንና ላኪዎችን ለመገናኘት ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው በዚህ አውደርዕይ ከዚህ ቀደም ሳይተዋወቁ ሲገበያዩ የነበሩ ቡና አቅራቢና ላኪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው መገበያት የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። ጅማ ላይ በተካሄደው አውደርዕይ ከሶስት መቶ በላይ የሆኑ አቅራቢና ላኪዎች ተሳታፊ በመሆን የገበያ ትስስር ፈጥረዋል፤ ሁለቱ አካላት ተገናኝተው፣ ተቀራርበው፣ በመካከላቸው ያለውን ችግር ቀርፈው በተመሳሳይ ያለሶስተኛ ወገን /ደላላ/ ጣልቃ ገብነት በተስማሙበት መጠን፣ ጥራትና ዋጋ መገበያየት ችለዋል።
የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ ተግባራዊ ከተደረገበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ግብይት ሲፈጸምበት የነበረው አጠቃላይ ሰባት በመቶ ያህሉ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት ብቻ 90 በመቶ ያህሉ የቡና ግብይት በቀጥታ የገበያ ትስስር አማራጭ ተፈጽሟል። ይህም ከአርሶአደሩ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኘውን የዘርፉ ተዋናይ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል። ተገበያዮችም ምርቱን አይተው እና ፈቅደው እንዲገበያዩ አስችሏቸዋል። ይህም የምርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ ወደ ውጭ የሚላከውን ቡና በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍ ማድረግ አስችሏል።
ሀገሪቱ ከቡና የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይበልጥ ለማሳደግና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ታልሞ የተዘጋጀው ይህ አውደርዕይ፤ በሀገሪቱ የሚመረቱ የቡና ዓይነቶችንና የጥራት ደረጃዎቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ታምኖበታል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም