ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የስበት ማዕከል ናት። የቀጣናውን ሀገራት ከማስተሳሰር ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩሏን ጥረት የምታደርግ ሀገርም ነች።
በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ቶሎ እንዲፈቱና ሀገራቱ በፍጥነት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሠላም ዋጋ ስትከፍል ረጅም ዘመናትን አስቆጥራለች። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ በሰሜን ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል።
ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዩ ግዛትና በሶማሊያ የሠላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ የሠላም ጥላና ከለላ መሆን ችላለች። በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሠላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አሕጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሠላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሠላም እንዲኖራቸው አበክራ ሠርታለች። በመሥራትም ላይ ትገኛለች።
ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዘመናት ቆይታለች። ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መሥርታ አንጻራዊ ሠላም አግኝታለች። ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆሩ ወታደሮቿን አጥታለች።
በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰሠላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋፅዖ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሠላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይም ሱዳን ግጭት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሱዳን ወደ ተሻለ ሠላምና መረጋጋት እንድትመጣ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በሱዳን የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረትም ግንባር ቀደም ሚናዋን መወጣቷ የሚታወስ ነው።
ሰሞኑንም በግጭት አዙሪት ውስጥ የምትገኘውን ይህችን ሀገር ወደ ሠላሟ እንድትመለስ የየትኛውም ሀገር መሪ ባላደረገው መልኩ ፖርት ሱዳን ድረስ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተው ተመልሰዋል። ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ‹‹“የወንድም ሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር ፤ሠላማቸውም ሠላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታ እና የብልፅግና ጉዞ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከልብ እንሠራለን።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ውስጥም ተፈጥሮ የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት እንዲያባራና አንጻራዊ ሠላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች።
በጎረቤት ሀገራት የሚታየውን ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃ ከመሥራት ጎን ለጎንም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በልማት እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድም የኢትዮጵያ ሚና የጎላ ነው።
ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በቀጣናው የሚታየውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ከዚያም ባሻገር የአካባቢ መራቆት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋነኛ ችግር መሆኑን በመረዳት የአረጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ዘንድ እንዲተገበር የመ ሪነት ሚናውን ወስ ዳ በመንቀሳ ቀስ ላይ ትገኛለ ች።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት ልማት በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተችው ያለችው ሚና በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገታ አይደለም። በተለይም ከዓባይ ግድብና ከጊቤ ሦስት ግድቦች የሚነጭ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ ቀጣናው በኃይል እንዲተሳሰር በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በድርቅና ረሃብ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንዴን በማምረት ከራሷ አልፋ ኤክስፖርት የማድረግ ደረጃ ላይ ደርሳለች። ይህ የአካባቢውን ሀገራት ከማነቃቃቱም ባሻገር አባል ሀገራቱ ስንዴን ከቅርብ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት ከማስተሳሰር ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገው ጥረት እንደትላንትናና ዛሬ ሁሉ ነገም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም