ሰላም አንድ ወጥ ብያኔ እንደሌለው የዘርፉ ምሁራን ይጠቁማሉ። ሰላም ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ሲሆን፤ መንፈሳዊ እና ስጋዊ ትርጉም እንዳለውም ይነገርለታል። ከመንፈሳዊ ብያኔ አንፃር በመፅሃፍ ቅዱስ እና በቅዱስ ቁርዓን ላይ ሰላም በተደጋጋሚ ከመጠቀሱ በተጨማሪ ሰፋፊ ብያኔ ተሰጥቶበታል። በመፅሃፍ ቅዱስ 429 ጊዜ በተደጋጋሚ ሰላም የሚለው ቃል ተፅፏል። የሰላም ምንጭ ፈጣሪ መሆኑ ተገልፆዋል። ሌሎችም በርካታ ከሰላም ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችም በመፅሃፍ ቅዱሱ ተብራርቷል።
በቅዱስ ቁርዓንም ስለሰላም በተደጋጋሚ ከመገለፅ አልፎ እስላም ማለት ሰላም ማለት መሆኑም ይነገራል። በሙስሊም ሃይማኖት ከፈጣሪ ስሞች መካከል አንዱ ሰላም መሆኑ ተገልጿል። በቅዱስ ቁርዓን በተለያየ መልኩ ለ44 ጊዜ ስለሰላም ተፅፏል። ስለዚህ በሁለቱም ቅዱስ መፅፎች የሰላም ምንጩ አምላክ መሆኑ ተገልፆዋል። ከሳይንሳዊ ትንታኔ አንፃር ሲታይ በርካታ ብያኔዎች ያሉት መሆኑን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ እና በወሎ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ በማስተማር ላይ የሚገኙት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ይናገራሉ።
የተለያዩ የምርምር ስራዎችን የሚያከናውኑት እና በተለያዩ መድረኮች ከሰላም ጋር በተያያዘ ሰፋፊ ገለፃዎችን የሚያደርጉት xena ስልጠናዎችን የሚሰጡት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ ከማህበራዊ ሳይንስ አንፃር በዓለም ታዋቂ የሆኑ ምሁራን የኖርዌዢያው ታዋቂው ዮንግራንተን ሰላምን በተመለከተ ብዙ ትንታኔ ሰጥተዋል። አዎንታዊ ሰላም እና አሉታዊ ሰላም መኖሩን አስቀምጠዋል። አሉታዊ ሰላም ማለት ከሁከት እና ከዓመፅ ነፃ መሆን ነው። የትኛው ሰፈርም ሆነ አገር ከብጥብጥ እና ከጦርነት ነፃ ሲሆን ሰላም ሆነ ይባላል። ነገር ግን ኮሽታ እና ቀውስ ሳይኖር ሲቀር ሁከት እና አመፅ ወይም ብጥብጥ እና ጦርነት ስለሌለ ብቻ ሰላም አለ ማለት አይቻልም ብለው የሚሞግቱ አሉ።
ግጭት አለመኖር ብቻውን ሰላም አለ አያስብልም። አውንታዊ ሰላም ያስፈልጋል ይላሉ። አውንታዊ ሰላም በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ትስስር፣ አንድነት፣ ፍትህ፣ ነፃነት፣ መረዳዳት ሲኖር ነው ብለው ይተነትኑታል። ስለዚህ ሰላም ፀጥታ ብቻ አይደለም። የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እኩልነት ሲሰርፅ መከባበር ሲኖር ሰላም ነው ማለት ይቻላል። ሃብት ላይ የሚወስኑት የተወሰኑ ሳይሆኑ ማህበረሰቡ ሁሉም ሲወስንበት ሰላም ነው ማለት ይቻላል ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ሰላም ፍትሃዊነት፣ ከብዝበዛ ነፃ ሆኖ መኖር፣ የሰብዓዊነት እና የስነምህዳር ደህንነት፣ የብዙሃን ፍላጎት እና ማህበራዊ ስልት መፍጠርን ያካትታል። ስለዚህ ሰላም ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊም ነው ይላሉ። ሰላም ምንጩ ምንድን ነው የሚለውንም አስመልክቶ አባተ (ዶ/ር) ሲያስረዱ፤ አንዳንዶች የሰላም ምንጭ ፈጣሪ ነው ይላሉ። ይህ ከመንፈሳዊ እይታ አንፃር የተባለ ነው። ነገር ግን በሳይንሳዊው መንገድ ሰላም የሚመጣው ከእያንዳንዱ ሰው ነው የሚሉ ብዙ ናቸው ይላሉ።
‹‹ሰላም አለን የምንለው በብሔር፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋም፣ ከመሸማቀቅ እና ከማሸማቀቅ የፀዳን ስንሆን ነው።›› ይላሉ። ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ በእርግጥ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በዓለም ዘር፣ ብሔር፣ የፖለቲካ አቋም፣ ሃይማኖት እና እምነት የግጭቶቻችን ምንጮች መሆናቸውን ይናገራሉ።
ስለዚህ ሰላም የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ሰው ነው። አንድ ሰው በዘሩ፣ በብሔሩ፣ በፖለቲካ አቋሙ፣ በሃይማኖቱ እና በእምነቱ መሸማቀቅ ሲቆምለት ወይም ሲቀርለት ነው ይላሉ። እያንዳንዱ ሰው ሲረጋጋ፣ ትዕግስት ሲኖረው፤ ሲራራ ከውስጡ ሰላም ይመጣል። ስለዚህ ሰላም መነሻው ከእያንዳንዱ ሰው ልብ ነው። ስለዚህ ዓለም ሰላም እንዲሆን እያንዳንዱ ሰው ሰላም መሆን አለበት። ‹‹ ሰላም ከፈለግክ መጀመሪያ ልብህ ሰላም ይሁን። አንተ ሰላም ሁን፤ አንተ ሰላም ከሆንክ ቤትህ ሰላም ይሆናል። ቤትህ ሰላም ከሆነ ጎረቤትህ ሰላም ይሆናል። የአንተ ሰላም ከሰፈር አልፎ ወደ አገር ይሻገራል። ስለዚህ የሰላም ምንጭ እያንዳንዱ ሰው ነው።›› ይላሉ።
አንድ ሰው ሌላ ሰውን በብሔሩ፣ በማንነቱ፣ በቋንቋው ካሸማቀቀ ሰላም ሊኖር አይችልም። ይህ ከቆመ ሰላም ይመጣል። ይህ ማሸማቀቅ ከቀጠለ ደግሞ ሰላም ይጠፋል። ስለዚህ ለሰላም መደፍረስ መነሻው እያንዳንዱ ሰው ነው። የሰላም መደፍረስ ይሰፋል። ሰላምም ይሰፋል። ስለዚህ የሰላም መፍትሔውንም ሆነ መነሻውን ለአንድ ወገን ብቻ መስጠት አይቻልም። መሪ ብቻ ሳይሆን ሰላም እንዲሆን የተመሪውም ድርሻ ወሳኝነት አለው ብለዋል።
እንደ አባተ (ዶ/ር) ገለፃ፤ መሪው ከተበላሸ በእርግጥም ሰላም ይጠፋል። ነገር ግን ተመሪም ካበላሸ ሰላም ይጠፋል። ስለዚህ ሰላም ከእያንዳንዱ ሰው ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ሰላም ማለት ከግጭት ነፃ መሆን ማለት ብቻ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ሰላም እንዲሰፍን ጣት ከመጠቆም ይልቅ መሪም ሆነ ተመሪ ሁሉም ከራሱ መጀመር አለበት።
አንዲት አገር ሰላም ናት ለማለት ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ የዓለም የአገራት የሠላም ደረጃን ሲያስቀምጡ፤ ያለፈውን ዓመት ማለትም በ2023 አየርላንድ፣ ኒውዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ሲውዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ስሎቫኒያ፣ ማሌዢያ በመጀመሪያነት የተገለፁ ናቸው። ሰላም የለባቸውም የተባሉት አገራት ደግሞ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሶሪያ ፤ አፍጋኒስታን እና በአብዛኛው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተካተዋል፤ እዚህ ላይ የእኛንም ይጨምራል።
ይህንን ደረጃ ያወጡ አካላት አንድ አገር ሰላም ናት ሰላም የላትም ሲሉ ምን ማለት ነው የሚለው ሲታይ፤ በአገሪቱ ዝቅተኛ የወንጀል አፈፃፀም አንደኛ መለኪያቸው ነበር። የትምህርት እና የበጎ አድራጎት ሥርዓት ሲኖር፤ ትምህርት እና ወንጀል በየሠፈሩ በየቦታው ዝቅተኛ ከሆነ ሰላም አለ ይላሉ። በየቦታው ከፍተኛ ወንጀል ከተስፋፋ ደግሞ ሰላም የለም ተብሎ የአገራት ደረጃ ላይ በመጨረሻው ተርታ ይቀመጣሉ።
እንደ አባተ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በየዓመቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በኢትዮጵያ የሰላም ትምህርት መኖር አለበት የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸውን አስታውሰው፤ ለዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች መኖራቸውን ያብራራሉ። በኢትዮጵያ ለዘመናት ግጭት ከመኖሩ አንፃር ለሰላም ትምህርት ትኩረት አለመሰጠቱ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ይላሉ። በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ቀርቶ በከፍተኛ ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሁሉም ተማሪዎች ከሚሰጡ ከ15 በላይ ኮርሶች መካከል ስለሰላም የሚሰጥ ኮርስ አለመኖሩ ተገቢነት የጎደለው ነው የሚል እምነት አላቸው።
ጃፓን እና ሌሎችም ሰላም ያለባቸው አገሮች ሰላምን በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ አካተው እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁንም ያለው ሃይማኖቶች በሰላም ላይ ጠንካራ አቋም ስላላቸው እንጂ፤ የከፋ ዘግናኝ ጉዳቶች ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። አሁን ግን ከወንጀል ጋር መላመዱ እየታየ መሆኑን ገልፀው፤ ለእዚህ ጠንካራ ትምህርት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።
የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ሰው ሲበደል ፍትህ ሲጓደል፤ በማህበራዊም በኢኮኖሚውም የመደጋገፍ ሁኔታ ሲኖረ ሰላም ይፈጠራል። ሠራተኞች የሚያገኙት ክፍያ የተመጣጠነ ሲሆን፤ የኢኮኖሚ እኩልነት ሲሰርጽ፣ በተለይም የሕግ የበላይነት እና ማህበራዊ ልማት ሲረጋገጥ ሰላም የመስፈን ዕድሉ እንደሚሰፋም ያስረዳሉ።
ሌላው ውጤታማ የሆነ የግብይት ሥርዓትም ከሰላም ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክተው፤ ዛሬ የተሸመተውን ነገ ለመሸመት ሲሞከር እጅግ ከናረ ስርዓት አለ ማለት አይቻልም። አሳማኝ ፍትሃዊ የግብይት ሥርዓት ሳይኖር ሰላም ይኖራል ማለት አይቻልም ይላሉ። ጨምረውም አንድ አገር ላይ ሥራ አጥነት እና ሥራ ፈትነት እያለ ሰላም አለ ማለት አይቻልም። ሻጭ እና ገዢ በተረጋጋ መልክ ካልተገበያየ ሻጭ እንደፈለገ ሥራውን እየዘጋ ሻጭ ብቻ ሃብት ካካበተ እና ፍትሃዊ የሃብት ስርጭት ከሌለ ሰላም አለ ማለት አይቻልም ብለዋል።
ሃብት መኖሩ ብቻ ሳይሆን ሃብቱ በአግባቡ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሁሉም ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል። ይህ ሳይሆን ሰዎች በፆታቸው፣ በዘራቸው፣ በብሔራቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸው፣ በሃይማኖት እና በእምነታቸው ምክንያት አድሎ ከተፈፀምባቸው የሃብት፣ የጤና የትምህርት፣ የፍትህ አገልግሎት በእኩልነት ካልተገኘ ሰላም መደፍረሱ እንደማይቀርም ያመለክታሉ።
እንደ አባተ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ሰዎችን እየጎዳ ያለው ፍትሃዊ የሃብት ሥርጫት እንጂ ድህነት አይደለም የሚል እምነት አለ። አንድ ቦታ ላይ በዝቶ አንዱ እንደፈለገ እየተንደላቀቀ ሲጠጣ፤ ሌላው ደግሞ የሚቀምሰው የሚበላው ሲያጣ ሰላም መደፍረሱ አይቀርም። ስለዚህ አንድ አገር ሰላም እንዳላት የምትመዘነው በዚህም ጭምር ነው።
የሌሎችን መብት ማክበር እና ማስከበር ሲኖር፤ በውስጥ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት ጋር በሰላም መኖር ሲቻል፤ አንድ አገር ሰላም ናት ማለት ይቻላል። እንደዚህ ሳይሆን ሰላም አለ ማለት አይቻልም የሚሉት አባተ (ዶ/ር) ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በግልፅ ጦርነት እና ግጭት መኖሩ ይታወቃል። ባለፈው ጦርነት ከ20 ቢሊየን በላይ ቁሳዊ ውድመት እና ወደ ሚሊየን የሚጠጋ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። አሁንም በአማራ እና በኦሮሚያ ያለው ግጭት ይታወቃል። ወንድም ከወንድሙ ጋር እየተገዳደለ ነው።
ከዚህ አንፃር ሲታይ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላም የለም። በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም በዓለምም ሰላም የለም የሚሉት አባተ (ዶ/ር)፤ በዓለም ላይ 132 አገሮች በጦርነት እና በግጭት ውስጥ መሆናቸውን ያብራራሉ። 17 ነጥብ 5 ትርሊየን ዶላር ባለፈው ዓመት ለጦርነት መዋሉን ጠቅሰው፤ በራሺያ እና በዩክሬን መካከል፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በየቀኑ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት እየዋለ ነው። እነርሱን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች ባለው ጦርነት ሳቢያ 13 በመቶ የዓለም አጠቃላይ ምርት ለጦርነት እየዋለ እና ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ስደት ዓለምን እያስጨነቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አባተ (ዶ/ር) መፍትሔ የሚሉትንም ሲጠቁሙ፤ የሰላም ምንጭ እያንዳንዱ ሰው በመሆኑ ሰዎች ሰላም እንዲኖራቸው ፈጣሪያቸውን ከመለመን በተጨማሪ የሰላም ባለቤት ራሳቸው መሆናቸውን ማመን አለባቸው። በሌላ በኩል ከታች ጀምሮ ሥርዓት ያለው ትምህርት መሠጠት አለበት። የሰላም ትምህርትን ጨምሮ ማስተማር ያስፈልጋል።
ከግለሰብ በተጨማሪ በመንግስት ደረጃም በዋናነት ከብጥብጥ፣ ከአመፅ፣ ከግጭት እና ከጦርነት ነፃ መሆን ብቻ ሳይሆን ፍትሓዊነት እንዲነግስ፣ ከላይ እስከ ታች የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ጥረት ማድረግ አለበት። ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መኖር አለበት። ሰላም ናቸው ተብለው የተጠቀሱት አገሮች መጀመሪያ የሕግ የበላይነትን አስፍነው ነው። በእዚህ ላይ ቤተእምነቶች መስራት አለባቸው። ወንጀለኛን እና ወንጀልን እየደበቁ ሰላም ማምጣት አይቻልም። ይላሉ።
መሠረታዊ የሆኑ የሰዎች ፍላጎቶች ሊሟሉ ይገባል። ማንኛውም ከግለሰብ እስከ መሪዎች የሰው ልጅ በዘሩ፣ በብሔሩ፣ በፖለቲካ አመለካከቱ የሚፈረጅበት ሁኔታ መቆም መቻል አለበት። ያለበለዚያ የጦርነት አዙሪት ውስጥ መግባት የግድ ይሆናል። አንዱ ሲመጣ ሌላው ሲተካ የጦርነት አዙሪቱ መቀጠል የለበትም። ለእዚህ ሕዝቡም ሆነ መንግስት ሁሉም በየበኩሉ መሥራት ይጠበቅበታል።
‹‹በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የሚፈጠርበት አንደኛው ምክንያት አፍሪካ ቀንድ ላይ በመገኘታችን፣ ብዙ ሕዝብ ስላለን፣ ለቀኝ ባለመገዛታቸው ምክንያት እንዳንስማማ እየተጋጨን እንድንኖር የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው።›› የሚሉት አባተ ዶ/ር፤ በተለያየ መልክ በማጣላት እና በማጋጨት የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ስለዚህ ከዚህ ተግባር ራስን ማቀብ ያስፈልጋል። ነገሮችን በተቻለ መጠን በውይይት እና በድርድር ለመፍታት መሞከር ይበጃል ብለዋል።
እንደ አባተ (ዶ/ር) ገለፃ በምንም መልኩ ቢሆን፤ ጦርነት ጦርነትን ከመውለድ ውጪ ሰላም አያስገኝም፤ ስለዚህ ከጦርነት እና መሳሪያ ከመማዘዝ ወጥቶ የውይይት ሃሳብን መቀበል ይሻላል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ብዙ ሃብት እና ንብረት ወድሞ ብዙዎች አልቀው ሁሉም ነገር የተፈታው በውይይት ነው። ስለዚህ በጉልበት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ለሰላም መቆም ይበጃል።
መጥፎ ሰላም የለም። ጥሩ ጦርነት የሚባል ነገርም የለም። ሁልጊዜም ከጦርነት ይልቅ ሠላም መቅደም አለበት። ስለእዚህ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተ እምነቶች፣ ትምህርት ቤቶች ሁሉም ሰላምን መርህ አድርገው ታግለው መቆም አለባቸው ብለዋል።
የሰው ልጅ ሶስት ዘመናትን አልፏል። የመጀመሪያው የጉልበት ዘመን፣ ቀጥሎ የመሳሪያ ዘመን ሶስተኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ ዘመን አሁን የቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ነን የሚሉት አባተ (ዶ/ር)፤ ‹‹አሁን ያለንበት ዘመን በድርድር እና በውይይት የሚታመንበት ነው። ነጮቹ አፍሪካውያን በጉልበት እና በጡቻ ከማሰብ አልወጡም ይላሉ። ልጆቻችን እንዲህ እንዳይባሉ አስቀድመን አስበን መስራት አለብን።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግለሰቦች ሰላም አድጎ የአገር ሰላም ይሆናል። የግለሰቦች ሰላም ደግሞ የሚመጣው በመረጋጋት፣ በትዕግሥት፣ በመከባበር፣ በርኅራኄ፣ በደግነት፣ ራስን በመግዛት፣ በድፍረት፣ ልክን በማወቅ፣ በይቅር ባይነት፣ በእኩልነት እና ትልቅ ቦታን በመመልከት ነው።
ምሁራን እንደሚያመለክቱትም ሆነ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ሰለም የሚጀምረው ከግለሰብ ነው። የግለሰብ ሰላም እያደገ ወደ ሰፈር እና ወደ አገር የሚያድግ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ሰላም ማድረግ ይጠበቅበታል። አለፍ ሲልም ማህበራዊ ትስስር እና ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነትም የሠላም መሠረት በመሆናቸው በእኩልነት እና በፍትሃዊነት ዙሪያ ህግን መሠረት ባደረገ መልኩ በስፋት መስራት ይገባል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም