የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ አገልግሎት

ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ አሁን ያለንበት ዘመን በሚገባ ያስገነዝባል። ቴክኖሎጂውን አነፍንፎና ተጠቃሚ ለመሆንም በርትቶ መስራት እስከተቻለ ድረስ የትኛውም አገልግሎት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆን ይችላል። የተለያዩ አገልግሎቶች ይነስም ይብዛ በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ እየተደረገ ነው።

በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆን በኩል ከአቅም ውስንነት፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ካለመተዋወቅና ከግንዛቤ ክፍተት የተነሳ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። ይህን ችግር በመፍታት በኩል መንግስት፣ ተቋማት ግለሰቦች የየበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። በተለይ ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ አምጥቶ ስራ ላይ ከማዋል አኳያ ዜጎች የሚያደርጓቸው ጥረቶች በአርአያነት ሊጠቀሱ ይገባቸዋል።

ቴክኖሎጂዎች በእጅጉ ከሚያስፈልጓቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞች ይጠቀሳሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማግኘት በኩል ግን ብዙ ይቀራቸዋል። አካል ጉዳተኞች ስራቸውን፣ መውጣት መግባታቸውን በአጠቃላይ ሕይወታቸውን ቀላል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጓቸው ይታመናል።

ይህ ችግር የገባቸው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አጋጣሚዎች በቴክኖሎጂ ወደ በለጸጉት ሀገራት የመሄድ እድል ሲገጥማቸው ‘ይህ ቴክኖሎጂ ለሀገሬ ያስፈልጋታል’ ብለው ቴክኖሎጂውንና እውቀቱን ይዘው ሲመጡ ይታያሉ። ይህን ጥረት ካደረጉት መካከል አቶ ሰለሞን አማረ አንዱ ነው።

የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ባለሙያው አቶ ሰለሞን የሰው ሠራሽ አካል ወይም የአካል ጉዳት አገልግሎት ሪሀቢልቴሽን ሙያን በእንግሊዝ የተማረ ሲሆን በረጅም ጊዜያት ቆይታውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ብዙ እውቀት ቀስሟል። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ የአካል ክፍላቸውን ላጡ አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

አቶ ሰለሞን ወደዚህ ሙያ የገባበትን አጋጣሚ ሲናገር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተማረ ባለበት ወቅት የሰው ሠራሽ አካል ወይም የአካል ጉዳት አገልግሎት በሚሰጥበት ሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት ለስራ ልምምድ በወጣበት አጋጣሚ በሙያው መመሰጡን ያስታውሳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሙያው ጋር አብሮ መሆኑን ይናገራል።

በሀገር ውስጥ በሙያው ሲሰራ ቆይቶ አጋጣሚውን አገኘና ለተጨማሪ ትምህርት እንግሊዝ ይሄዳል፤ በዚያም በዚሁ ሙያ ትምህርቱን ይቀጥላል፤ ለ14 ዓመታት እዚያው እየሰራ ይቆያል። በእንግሊዝ ሀገር ለአካል ጉዳተኞች ያለው ቴክኖሎጂ በጣም ጥሩ መሆኑ ሙያውን ዋና ምርጫው አድርጎ እንዲይዘው እንዳደረገው ይገልጻል።

‹‹በእንግሊዝ በጣም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አይቻለሁ፣ በቆይታዬም ጥሩ ክፍያም አገኝበት ነበር፤ ሥራውም ውስጣዊ እርካታ የሚፈጥር ስለሆነ በዚያው ቀጠልኩ›› የሚለው አቶ ሰለሞን፣ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ሥራውን የመስራት ሀሳብ እንደነበረው ያስታውሳል። ወደ ሀገሩ ሲመለስ ይህን ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር እንዳይቸገር በእንግሊዝ ያገኛቸውን ለቀጣይ ስራው ይጠቅማሉ ያላቸውን ቁሳቁሶች ለ11 ዓመታት ያህል አጠራቅሞ ይዞ መምጣቱን ያመለክታል።

ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰም በቀድሞ ሰሙ ሰውሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት በአሁን ስሙ ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳት ድርጅት ውስጥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በዚሁ ተቋም እየሰራ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ለሥራው እውቅና እንደሰጡትም ይናገራል። ሀገር በቀል የሆነ ተቋም እንዲኖር፣ ለስራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከውጭ እንዲገቡ በማድረግ ድርጅቱ በአዲስ መልክ እንዲድራጅና እንዲቋቋም አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያስረዳል።

ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ራሱን አሳምኖ መምጣቱን የሚናገረው አቶ ሰለሞን፤ ይህም ያገጠሙትን ቢሮክራሲዎች በትእግስትና በጥበብ እያሳለፈ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንደጠቀመው ያስረዳል። አሁን ባለበት ስራም አንድ ዓመት ያህል እንዳስቆጠረ ገልፆ፤ እየሰጠ ባለው የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አገልግሎት በጦርነት፣ በመኪና አደጋ እንዲሁም በስኳር በሽታና በመሳሰሉት ምክንያቶች አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ተጠቃሚዎች እንደሆኑም ይጠቅሳል።

አቶ ሰለሞን እንደሚያስረዳው፤ በሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች ከወገብ በላይ እና ከወገብ በታች ተብለው በሁለት ይለያሉ። ከወገብ በላይ የሚባለው እጁ ለተቆረጠ የሚሰጥ ሲሆን ከወገብ በታች የሚባለው ደግሞ እግሩ ለተቆረጠ ሰው የሚሰጥ አገልግሎት ነው። አገልግሎት እየሰጠ ያለው በተለይ ከጉልበት በታች የሆነ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረሰብ ክፍሎች የሚሰጠውን የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ነው።

‹‹ይህንን ብዙዎች በተለምዶ አርተፊሻል እግር ይሉታል፤ ግን አይደለም፤ ይህ ሰው ሰራሽ አካል ዋናው እግር ባይሆንም እውነተኛ እግር ነው /ትክክለኛ ስያሜውም ሰው ሠራሽ እግር ነው ›› ሲል ያብራራል። ሰው ሰራሽ እጅ ለመስራት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሶ፤ ለእዚህ ስራ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል ይገልጻል። ከዚያ ይልቅ እግር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።

‹‹ይህን አገልግሎት ባለን የቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም የምንሰራ ስለሆነ ቢያንስ አካል ጉዳተኛውን ሊያራምድ የሚችል፣ ወጥቶ የሚገባበት እና ሥራ የሚሄድበትና የሚሮጡበት እናደርጋለን፤ እያደረግን ነው›› ይላል። ያደጉት ሀገራት ጤነኛ እግር የሚሰጠውን አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ሰው ሰራሽ እግር እየሰሩ መሆናቸውንም ያመለክታል። ያንን ደግሞ ወደፊት እንደርሰበታለን የሚል ተስፋ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ይናገራል። አሁን ላይ ግን የሚያራምድ፣ የሚያስሮጥና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሊያከናወን የሚችልን ሰው ሰራሽ እግር እየሰራ መሆኑን ያስረዳል።

አሁን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚባሉት መቶ በመቶ ከውጭ አገር የሚመጡ መሆናቸውን አስታውሶ፤ ስራው እነዚህን የሚተኩ የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀምን ደግሞ የግድ መሆኑን ይናገራል። ‹‹ወደ ፊት እኛ ከእንግሊዝ ሀገር የአመጣናቸውን ምርቶች ናሙና ለሀገር ውስጥ አምራቾች እየሰጠን ተቀድተው እንዲሰሩልን እያደረግን ነው›› ሲል ጠቅሶ፣ ትክክለኛ የዚያን ምርት አይነት ባይመጣም ለኢትዮጵያ በሚመጥን መልኩ እየተሰራ ጥቅም ላይ እያወለ መሆኑን ያስገነዝባል። ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያትም 75 በመቶ ያህል ምርቶችን ከሀገር ውስጥ እንጠቀማለን ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሀገር ውስጥ ምርቶችን በሚፈልገው ልክ እያደረገ ጥቅም ላይ እንደሚያውል አቶ ሰለሞን አመልክቶ፤ ለአብነትም ኤርጌንዶ የተሰኘ ድርጅት ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ፕላስቲኮችን እንዲሰራ በማድረግ እየተጠቀመ መሆኑን ይጠቅሳል።

አቶ ሰለሞን እንዳብራራው፣ ሰው ሠራሽ እግር ለመስራትም አልሙኒየም፣ ካልቦኔት ፋይበር፣ ግላስ ፋይበር ኬሚካሎች እና የመሳሳሉት ያስፈልጋሉ፤ እነዚህን ግብአቶች ሀገር ውስጥ ለማግኘት ያስቸግራል። ቢያንስ ኬሚካሎቹ ከውጭ መምጣት አለባቸው፤ ይሁንና ሌሎቹ ግብዓቶች ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ይቻላል። በትክክለኛው የሰው ሠራሽ አገልግሎት ሰው ሰራሽ አካል ከተሰራ በኋላ ቢያንስ በየሦስት ወሩ ክትትል ማድረግ አለበት። ልክ አንድ ሰው ሕመም ሲኖርበት በየሦስት ወሩ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ሁሉ፣ የሰው ሠራሽ አገልግሎት ማግኘት ያለበት ሰውም በየሦስት ወሩ ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል። በዚህ ሂደትም የሚቀሩና የሚታዩ ለውጦች ስላሉ ታይተው የሚሰሩበት ሁኔታ አለ።

ሰው ሰራሽ አካሉ በየሦስት ወሩ የሚታደስና የሚቀየርበት ሁኔታ እንዳለም ይናገራል። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሶ፣ ለምሳሌ ሕጻናት ሊያድጉ፣ ሊከሱና ሊወፍሩ ስለሚችሉና ሰው ይህ በሚሆንበት ወቅት ሰው ሰራሽ አካል ሊጠባቸው እንዲሁም ቁመቱ ሊያጥር እንደሚችል ገልጧል፤ ይህ ሲሆን መቀየር እንዳለበት ተናግሮ፣ ለሌሎች ሰዎችም እንዲሁ ሊጠባቸውና ሊሰፋቸው ስለሚችል ሊታይና ሊቀየር ይገባል ሲል አስገንዝቧል ።

አቶ ሰለሞን ቴክኖሎጂ በየጊዜ እየፈጠነ ባለበት በዚህ ዘመን እንደ ሀገር እኛ ወደኋላ ቀርተናል ሲል ጠቅሶ፣ አሁን በጀመርነው ፍጥነት መሄድ ከቻልን ግን እዚያ ላይ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም ባይ ነው። ስራው ያሉትን ባለሙያዎች ወደ ሥራ ማስማራት፣ ስልጠና መስጠት እና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማድረግን እንደሚጠይቅ አስገንዝቧል፤ ከሁለትና ከሦስት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ጥሩ ለውጦችን ማየት እንደምትችል ተስፋ እንዳለው ይጠቁማል።

‹‹በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አካል የሚያስፈልጋቸው የተለያየ አይነት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው›› የሚለው አቶ ሰለሞን፤ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው ሕጸናት፣ ከተለያዩ በሽታዎች ጋር በተያያዘ በተከሰተ ደም መርጋት የተነሳ እግራቸው የተቆረጠ አዛውንቶች፣ በስኳር ሕመም፣ ካንሰር እና ጦርነት፣ በአውሬ መበላት፣ በጥይት መመታት እና በሌሎች አደጋዎች ምክንያት አካላቸውን ላጡ ዜጎች የሰው ሠራሽ አካል አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑንና በዚህም ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ያስረዳል።

አቶ ሰለሞን እንደተናገረው፤ በግሉ እስካሁን 155 ያህል ሰዎች ዘመናዊ የሰው ሰራሽ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ይህ አገልግሎት ወደ ገንዘብ ቢለወጥ ከ65 ሚሊዮን ብር ያወጣል። ይህንን አገልግሎት ያገኙ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ ሁሌም ይመርቁታል። አንድ አገልግሎቱን የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያው ቀን ልኬቱ ይወሰዳል፤ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ሰው ሰራሽ አካሉ ይገጠምለታል፤ ከዚያ በኋላ ወደቤቱ ሄዶ እንዲለማመድ ይደረጋል።

የሰው ሠራሽ አካል የሚሰራላት ታካሚ መጀመሪያ ከቁስል፤ ኢንፌክሽን እና ከመሳሳሉት ጋር የተያያዙ ነገሮች እንዳሉበትና እንደሌሉበት ይፈተሻል። ይህንን ሂደት ከጨረሰ በኋላ ይለካል፤ ከተለካ በኋላ ይሰራለትና አንዴ ከተለማመደ በኋላ ወደ ቤቱ ሄዶ እንዲለማመድ ይደረጋል። መለማመዱ እንደግለሰቡ ሁኔታ የተለያዩ ጊዜያትን ሊወስድ ይችላል። ቶሎ ቆሞ የመሄድና መራመድ ፍላጎት ያለው ሰው በሚገባ ከተለማመደ በፍጥነት መራመድ ይችላል።

‹‹ወደ ውጭ ከመሄዴ በፊት ከምሰራቸው ስራዎች ይልቅ አሁን የምሰራው በጣም የተሻለ፤ ሰው ሰራሽ አካል ተደርጎለት በአንድ ቀን ቆሞ የሚሄድና ቶሎ የሚራመድ ሰው አለ። ከዚህ በፊት ግን በፍራቻ ከ15 እስከ 20 ቀናት ድረስ የማይራመዱ ሰዎች ነበሩ። የአሁኖቹ ቁሳቁስ ይመቻሉ፤ ስራ ጥሩ ለውጥ ያመጣ ሆኖ አግኝቼዋለሁ›› ሲል ያብራራል።

አገልግሎቱን አንዴ ካገኙ ሰዎች በሦስት ወሩ ተመልሰው ክትትል ማድረግ እየተጠበቀባቸው የማይመጡ እንዳሉ ጠቅሶ፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰው ሰራሽ አካሉ የሚወሰድባቸው እየመሰላቸው ነው ይላል። ይህንንም ‹‹አንድ የአገልግሎቱን ተጠቃሚ ደውዬለት መጥተህ ልይልህ ስለው ኧረ አይሆንም፤ መልሰህ ልትወስድብኝ ነው ብሎኝ ቀርቷል›› ሲል በማስረጃ አስደግፎ ገልጾታል።

አቶ ሰለሞን በሥራው አሳዛኝ ገጠመኝ እንዳለውም ያስታውሳል፤ ‹‹የካንስር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ሰው ሰራሽ አካሉ ተሰርቶላቸው እየጠበቁ እና እየተለማመዱ እያለ፣ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ጓጉተው እያሉ የካንሰሩ ሕመም ጠንቶባቸው ሕይወታቸው ያለፈበትን ሁኔታም አለ›› ይላል።

ይህንን ሰው ሰራሽ አካል አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች በራሱ አቅም በተቻለው መጠን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየረዳቸው መሆኑንም አቶ ሰለሞን ጠቅሷል። ይህን ለማስፋት የሌሎች አቅም ያላቸው ሰዎችና ድርጅቶች እገዛ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል። በተለይ ምንም አይነት የፋይናንስ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ተጋግዞ መርዳት ካልተቻለ በእሱ አቅም ብቻ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል ይጠቁማል። ነገ ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆኑ ምንም ዋስትና እንደሌለው አስገንዝቦ፤ መንግሥትና ባለሀብቶችም ለእዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ ነው ያሳሰበው።

አቶ ሰለሞን የሰው ሰራሽ አካል አዲስ ማዕከል እያቋቋመም ነው። በአዲስ አበባ ገላን ጉራ አካባቢ እያስገነባ ያለው የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የሚያደርግ የሰው ሠራሽ አካል ድጋፍ ማዕከል በሚቀጥለው ዓመት ስራ እንደሚጀምርም ጠቁሟል። ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባ የመጀመሪያ ሥራው የሚያደርገው ባለሙያዎችን ማሰልጠን ሲሆን፤ ቁሳቁስን ማምረት፣ ለስራው የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ እንዲሁም አገልግሎቱን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ እቅድ አለው።

‹‹በሰው ሠራሽ አካል አገልግሎት ላይ መንግሥትን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው የበኩሉን ሊወጣ ይገባል›› ሲል አስታውቆ፤ አሁን እያደረገ ካለውም በላይ የሀሳብ፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ቢሳተፍ ብዙ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ነው አቶ ሰለሞን ያስገነዘበው።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You