ለበጀት አጠቃቀማችን ውጤታማነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል!

የሙስና ወንጀል አፈጻጸም ከሀገር ሀገር፣ ከቦታ ቦታ እና ከሌሎችም በርካታ ምክንያቶች አኳያ የሚለያይ ቢሆንም፤ ሙስና አይፈጸምበትም የሚባል ሀገር አለ ብሎ ለመናገር ግን የሚያስደፍር አይደለም። ሙስና እንደየ ሀገሩ እና የፖለቲካ ስሪቱ የተለያየ ስልትና መንገድ ተከትሎ የሚፈጸም ከመሆኑ አኳያም ደግሞ ስለ ሙስና በተለያዩ ምሁራን የተለያየ ትርጉም ሲሰጠው ይስተዋላል።

በዚህም የተነሳ የተለያዩ ፀሀፊዎች ስለሙስና ምንነት የተለያየ ትርጉም ሰጥተዋል። ትርጓሜውና ገጽታው ምንም ይሁን ምን ግን፣ ሙስና ከድህነት ለመላቀቅ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረግ ትግልን በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታተን ተግባር መሆኑ የታመነ ነው። እናም የልማትና የእድገት ፀር የሆነው ሙስናን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ሀገራት ለሚያራምዱት ልማት መሳካት ወሳኝ እንደሆነም ይታመንበታል።

ሙስና ለእድገት እንቅፋቶች ናቸው ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ሙስና ከኢኮኖሚያዊ ልምሻ ፈጣሪነቱ ባሻገርም፤ የሕዝብን ደህንነት እና የተረጋጋ ኑሮን ያናጋል፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን ያደርጋል፤ የዜጎችን የወደፊት ተስፋን ያጨልማል፤ የሀገራት የመልማት እቅድን ያሰናክላል።

ሙስና በዚህ ልክ የሚገለጽ የሀገርና ሕዝብ ሕልውና አደጋ ከሆነ ታዲያ፤ ይሄንን ችግር መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ከየሀገራት መንግሥታትና የሚመለከታቸው አባለድርሻዎች የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ አንድም ሙስና ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ቀድሞ ለይቶ መከላከል ሲሆን፤ ተፈጽሞ ሲገኝም በሙሰኞች ላይ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ነው። ይሄ ግን ከፍ ያለ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።

ምክንያቱም ሙስናን መዋጋት በራሱ ትልቅ ፈተና በመሆኑ ነው። የሆነው ሆኖ ሙሰኞችን በሕግ በመጠየቅ ሙሰኞች የዘረፉትን ገንዘብና ንብረት እንዲመልስ ማድረግ አንዱ ሀገርና ሕዝብን ከአደጋ መታደጊያ ስትራቴጂ ሲሆን፤ ይሄ ሙስናን ለመዋጋት ከሚወሰዱት ርምጃዎች የመጨረሻው ደረጃ እንደሆነ በዘርፉ የሚሠሩ ምሁራን ይናገራሉ። እንደምሁራኑ ትንተና ሙሰኝነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት የመከላከል ተግባር ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ይኖርበታል።

ሙስናን ከመዋጋት አኳያ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው፣ ሙስናን ቀድሞ መከላከል ነው ሲባል ወንጀሉ ከመፈፀሙና የሕዝብ ሀብት ከመባከኑ በፊት የማከም ሥራ ነው። ሆኖም ይሄ ከፍ ያለ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋትን ይጠይቃል። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሙስና ዓለማአቀፋዊ ክስተት እየሆነ ከመምጣቱ ባለፈ፣ ከድህነት ለመላቀቅና ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ለመገንባት የሚደረግ ትግልን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ የሚገኘው። ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብን ደህንነትና የተረጋጋ ኑሮን ያናጋል። የመልካም አስተዳደር እጦትን ይወልዳል አለፍ ሲልም የሀገርን የመልማት እቅድ የሚያሰናክል እኩይ ተግባር ነው።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እአአ በ2022 ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ዴንማርክ፣ ፊንላድ፣ ኒውዚላንድ እና ሲንጋፖር ሙስናን ትርጉም ባለው መልኩ የታገሉ ሀገራት ሲል የገለፃቸው ሲሆን፤ ሱማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቬንዚዌላ፣ የመንና ሊቢያን ደግሞ ሙስናን ፀጋ ብለው የተቀበሉና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሀገራት ሲል አስቀጧቸዋል።

በሀገራችን ኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፋ የመጣውን የሙስና ተግባር ለመከላከል በ1993 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 235/1993 በፌዴራል ደረጃ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋቀሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። ይሄ ኮሚሽን በክልሎችም ቅርንጫፍ ከፍቶ እየሠራ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ እስካሁን በመከላከል ረገድ ሰፊ ሥራዎች ሠርቷል።

ለአብነት፣ በ2015 በጀት አመት ኮሚሽኑ በተቀበላቸው ከአንድ ሺህ 400 በላይ ጥቆማዎችን መሠረት የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራዎች ተከናውነው በርካታ የሕዝብና የሀገርን ሀብት ማዳን ተችሏል። በገጠርና በከተማም ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ ድርጊቶችን ማስቀረት ችሏል። ይሄ ማለት ግን ሙስና መገለጫው የመሬት ወረራ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ይልቁንም ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ከራሷም ከአበዳሪዎችም ብላ በምታመጣው ዓመታዊ በጀት ላይም የረዘመ እጁ ጎልቶ ይታያል።

ዛሬ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደሀገር ያላት የበጀት አቅም ፈርጥሞ ወደ ትሪሊዮን ብሮች ተጠግቷል። ይሁንና ሀገሪቱ ያለባት የበጀት አጠቃቀም ችግር ከፌዴራል መንግሥት ካዝና የሚበጀቱ ቢሊዮን ብሮች ለታለመላቸው ዓላማ እንዳይውሉ መሰናክል ሆኗል። ከሳምታት በፊት የወጣው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲትና ክዋኔ ሪፖርት ደግሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት እንዳመላከተው በ2015 በጀት ዓመት ባለ በጀት የመንግሥት ተቋማት ላይ በተካሄደ ኦዲት ብዛት ያላቸው የአሠራር ክፍተቶችና የፋይናንስ ጉድለቶች ተገኝተዋል። የኦዲት ግኝቶቹ ደግሞ በፌዴራል መንግሥት በጀት ላይ ያተኮሩ ናቸው። መሰል አሠራር እስከ ታች ድረስ ሊወርድ ይገባል። ክልሎችም የራሳቸው በጀት ስላላቸውና የራሳቸውን በጀት ስለሚጠቀሙ ከክፍተቶቹ እንድንወጣና እንዲታረሙ ያለውን ውስን ሀብት ደግሞ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ እንዲውል በማድረጉ በኩል በትኩረት እንዲሠራበት ነው።

ከዚህ አኳያ ለ2017 በጀት ዓመት ከተበጀተው 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪ የሚውል ነው። 283 ነጥብ 2 የሚሆነው ደግሞ ለካፒታል ወጪ እንደሚውል የበጀት ክፍፍል ሪፖርቱ ይጠቁማል። በተጨማሪም ለብሄራዊ ክልላዊ መንግሥታት፣ ለድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአጠቃላይ በጀቱ ወደ 236 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድርሻን ይይዛሉ።

በጀት ደግሞ የሀገር የደም ስር ነው። ለወደፊቱ የሚመጣን ገቢና ወጪን የሚተነብይ የገንዘብ እቅድ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ትሪሊዮን የቀረበ በጀት መድባለች። ሆኖም በጀቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በተለያዩ መዋቅሮች የቁጥጥር ሥራ እንደሚከናወን የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል። የተመደበው ገንዘብ ለታለመለት ግብ እንዲውል አሠራርንና ሕግን በተከተለ መልኩ ተቋማት ሊሠሩ ይገባል።

የሀገራችን በጀት አጠቃቀም ከካቻምናው ዓምና፣ ከኣምና ዘንድሮ ለውጦች የታዩበት ነው። ግን ደግሞ አሁንም በቅጡ ያልተስተካከለው የኢትዮጵያ የበጀት አጠቃቀም ሥርዓት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መዥገር ሆኖ የሚመጥ ብቻ ሳይሆን፤ የብልፅግናዋም መሰናክል ከመሆን አልፀዳም። ይህንን የሀገር እድገት ፈተና ለመቅረፍና የበጀት ሥርዓት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በበጀት አባካኞች ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥርዓት እየተተገበረ ይገኛል።

አንዳንድ ገንዘብን አምላካቸው ያደረጉ በስራውም ብቃትና ብስለት የሌላቸው በማወቅም ባለማወቅም የሚፈፅሟቸው ግድፈቶች አሉ። ይህንን ለማረም የሚወሰዱ ርምጃዎች የሚወሰዱ እርምቶች እንዲሁ ወንጀል ስለተፈፀመ በስሜት ተነሳስቶ ሳይሆን የሕግ ማእቀፍ የያዘ መሆን አለበት። ትልቁ ነገር የተዘረፈ የሀገር ሀብት ወደ ሕዝብ የሚመለስበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። መላውን ሕዝብ በሚጠቅም ሁኔታ ጥቂት ዘራፊዎችን ወንጀለኞችን በሕግ ጥላ/ ማዕቀፍ አውሎ የሚወሰዱ ርምጃዎች ሊኖሩ ይገባል። እስካሁን የተወሰዱ ርምጃዎች ቢኖሩም በቂ አይደለም።

የፀደቀው የ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከባለፈው የ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ170 ቢሊዮን ብር ማለትም በ21 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያሳየ ነው። በዚህ ደረጃ ከፍተኛ እድገት የታየበት የሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት ታዲያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማፋጠን እንዲያስችል እንዲሁም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ድህነት ተኮር ለሆኑ ተግባራት ትኩረት የሰጠ እና ፕሮግራም በጀት አሠራርን የተከተለ እንዲሆን አስፈፃሚ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የበጀቱ መጨመር በመልካም የሚታይ ቢሆንም በጀቱን ለተቀመጠለት ዓላማ ከማዋል አንፃር ግን ችግሮች እንደሚስተዋሉ የዋና ኦዲተር መሥሪያቤት የሚያወጣቸው የሂሳብ ምርመራ ውጤቶች ያሳያሉ። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመንግሥት ተቋማት ላይ ባካሄደው የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስ ጉድለቶችን የሚያመላክት የኦዲት ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል።

ከደምብና መመሪያ ውጪ ክፍያ የፈፀሙ ተቋማት 16 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የግዢ አዋጅ፣ደምብና መመሪያ ያልተከተሉ ግዢዎችን የፈፀሙ ተቋማት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በኦዲት መገኘቱን ሪፖርቱ ያስረዳል። ከተደለደለላቸው በጀት በላይ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የተጠቀሙም መሥሪያ ቤቶችም አሉ።

ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ለሌብነትና ስርቆት ምቹ መደላድል በመፍጠር ሀገሪቱ ወደ ኋላ እንደትመለስ ከማድረግ ባለፈ ሆን ብለው ፕሮጀክቶችን በማስረዘምም ጭምር ሀገሪቱ ከድህነት እንዳትወጣም እያደረጉ ነው። በተጨማሪም ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡ አላስፈላጊ ስብስባዎችንና አላግባብ የሆነ አበል በመክፈል በጀቱን የሚበዘብዙ ተቋማት እንዳሉ እሙን ነው። በተቋም ውስጥ ለማይሰራ ግለሰብ ጭምር ደመወዝ የሚከፍሉ መሥሪያ ቤቶች እንዳሉም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል።

ይህ ደግሞ ከሕዝብ የሚሰበሰበው ገንዘብ በአግባቡ ልማት ላይ እንዳይውል እያደረገው ነው። ሌብነት እና ስርቆትን የሚያመጣው አግባብ ያልሆነው የበጀት አጠቃቀምን የሚከተሉ ተቋማትና ሃላፊዎች ላይም መንግሥት ተከታትሎ ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።

ያ ካልሆነ ግን መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊነትና ውጤታማነትን ለማጠናከር የበጀት መጠኑን መጨመሩ ዋጋ አልባ ይሆናል። ስለዚህ በጀትን ከሙስና ብልሹ አሠራር በመከላከል በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር እንዲቻልም ጥብቅ የሆነ የፋይናንስ ፖሊሲ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። ይህንን በጀት በአግባቡ ለሚፈለገው አላማ እንዲውል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥብቅ የድጋፍና ክትትል ሥራ መሥራት ያስፈልገዋል። የበጀት አጠቃቀም ተጠያቂነት በሚያሰፍን ሥርዓት ሊመራ ይገባል።

የበጀት አጠቃቀም ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው። የአምና ሪፖርት እንደሚጠቁመው ወደ 350 ሚሊዮን የበጀት ጉድለት ነበር። ይህ የበጀት ጉድለት በተለያየ ምክንያት የሚፈጠር ነው። ይህንን አሻሽሎ አስፈፃሚ አካላት በጀትን በቁጠባ ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም ብቻ ማዋል እንዲችሉ ኢኮኖሚያችንን ማህበራዊ ጉዳዮቻችንን ታሳቢ አድርገው ተፈፃሚ ማድረግ አለባቸው።

ተጠያቂነት ከሌለ ማንም ሰዉ ያሻውንና የፈቀደውን እንዲሠራ ምክንያት ይሆናል። አንድ ሰው ያሻውን ሲሠራ የማይጠየቅ ወይም ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነ ደግሞ ሙስና ተከስቶ ሀገር ያፈርሳል፣ ያልሰራ ይከብራል። ይህ እንዳይሆን የተጠያቂነት አሠራርን ማስፈን ያስፈልጋል።

ዴሞክራሲ የሚዳብረው ኢኮኖሚ፣ የሚያድገው የልማት ፍላጎቶቻችን ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ሲቻል ነው። አስፈፃሚ አካላት በታማኝነት ለሕዝብ ጥቅምና ጥቅም ብቻ በተፈቀደ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት በሚፈቅደውና ሕጉን ተከትለው ማስፈፀም አለባቸው።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You