ፕሮጀክቶች ላይ የታየው ስኬት በሌላውም እንዲደገም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀገርን የማስዋብ ፕሮጀክት የጀመሩት በ2011 ዓ.ም ሸገርን ለማስዋብ ‹‹ገበታ ለሸገር›› የተሰኘ የእራት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ነበር፡፡ በዚህ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ከባለሀብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ የከተማዋን ደረጃ ማሳደግ፣ ኢኮኖሚዋን ማነቃቃትና የከተማዋን ቱሪዝም መጨመር፣ የወንዞች ዳርቻ የሪል ስቴት ባለቤትነትን ዋጋ ማሳደግ ተችሏል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር በአስገራሚ ፍጥነት የሸገር እና የእንጦጦ ፓርኮች ተጠናቀው ለጎብኚዎች ክፍት ሲደረጉ የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ ክስተት ተፈጥሯል፡፡ ብዙዎች በመዲናዋ ውበት ከመደመም አልፈው ፕሮጀክቶቹ የተሠሩበት ፍጥነትና የፕሮጀክቶቹ አመራር ላይ ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም። የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ አንድና ሁለት ፕሮጀክቶችም በገበታ ለሸገር የተከናወኑና የከተማዋን ገፅታ በእጅጉ የቀየሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ መግባት በርካታ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከማስቻል ባለፈ የከተማይቱም ገጽታ መቀየር እንደሚቻል በማሳየት በቀጣይ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ መንገድ ጠርጓል። እነዚህ ተግባራት የፈጠራ ክህሎት መነቃቃትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓላማ ያላቸውን ዕቅድ አቅዶ የማስፈጸም አቅም ታይቶባቸዋል።

ከሁሉም በላይ ትክክለኛ አመራር ካለ በውጤታማነት በመጓዝ ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የሚያስችሉትን የኢትዮጵያን የተትረፈረፉ ሀብቶች የሚያመላክቱ ተምሳሌታዊ ማሳያዎች ሆነዋል። የፕሮጀክት ሃሳቡ አመንጪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር “ገበታ ለሀገር” የተሰኘ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይፋ በማድረጋቸው ከቤት እስከ ሀገር ለሚደረገው ብልጽግና ከ “ገበታ ለሸገር” ውጤታማነት በመነሳት ሌሎች ፕሮጀክቶችን በሕዝብ ተሳትፎ በማጀብ ውጤታማ ለማድረግ የታለመ መርሀ ግብር ተጀመረ፡፡

ይህ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ዙር ከአዲስ አበባ ውጪ ሶስት ቦታዎችን ከአማራ ክልል ጎርጎራ፣ ከኦሮሚያ ክልል ወንጪ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮይሻን ለማልማት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ሥራ በመግባት ውጤታማ ለመሆን ተችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥራውን የሚመራና የሚያስተባብር ከመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተውጣጣ ኮሚቴም በማዋቀር ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ሃላፊነት እንዲወስዱ ማድረጋቸው ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ፕሮጀክቶቹን ተፈጻሚ ለማድረግ ከማኅበረሰቡ የሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍ በጥቅሉ ከገበታ ለሀገር ቢያንስ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ይገኛል ተብሎ ተጠብቋል፡፡ በዚሁ መነሻነትም የወንጪና ኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለጎብኚዎች ክፍት መሆን ችለዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች በአካባቢዎቹ የነበሩ ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ጎልተውና ፈክተው እንዲወጡ ከማስቻላቸውም በላይ በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮችም ጭምር በተለያየ መልኩ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የተረመረቀው የጎርጎራ ፕሮጀክት ደግሞ እጅን በአፍ ያስጫነና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ጨፍ የደረሰበትን ክስተት አሳይቷል፡፡

አሁን ደግሞ ገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ‹‹ገበታ ለትውልድ›› ወደተሰኘ ፕሮጀክት ተሸጋግሯል፡፡ “ገበታ ለትውልድ” የተሰኘው አዲስ ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ለማልማት ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ገልፀዋል፡፡

በዚህም እስካሁን ባለው ሂደት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ለፕሮጀክቶቹ የሚውል 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በገበታ ለትውልድ ስምንት ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀው ከስምንቱ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ በግል ባለሀብቶች እንደሚለሙም አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹም በዋናነት በትግራይ ክልል “ገራ አልታ”፣ በኦሮሚያ ክልል “ጅማ” በአማራ ክልል “ሃይቅ” በደቡብ ክልል “አርባ ምንጭ”፣ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች እንደሚተገበሩ ነው የተናገሩት። በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዳሴ ግድብ አካባቢና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች በግል ባለሀብቶች እንደሚለሙ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን ቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ በማነቃቃት ዜጎችን ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን ለፕሮጀክቶቹ እውን መሆን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንግዲህ ገበታ ለሸገርም ሆነ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተከናወኑት በሕዝብ ንቅናቄና ድጋፍ እንዲሁም በዜጎች ተሳትፎ ነው፡፡ ዜጎችንና ባለሀብቶችን በማስተባበር እንዲህ አይነት ድንቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚቻለው ደግሞ ድንቅ የአመራር ጥበብና ለፕሮጀክቶቹ ቀና መሆን ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ከነዚህ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያ ሕዝብንና ባለሀብቶችን አስተባብሮ በርካታ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለፕሮጀክቶች በቶሎ መጠናቀቅና እውን መሆን ቁርጠኛ መሆንና ጠንካራ የአመራር ብቃት መኖር ወሳኝ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

አሁን የገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ወደ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እንደመሸጋገሩ ከዚህ በፊት በነበሩት ፕሮጀክቶች የታየው ድንቅ የአመራር ብቃትና ዜጎችንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረጉ ሥራ በዚህም ፕሮጀክት ይደገማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያውያንም እነዚህን ድንቅ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው በማየታቸው አሁንም ለሚከናወኑት ፕሮጀክቶች ድጋፋቸውን እንደሚቸሩ አያጠያይቅም፡፡

ከዚህ ባሻገር እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም፣ አውቀትና ችሎታ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማመንጨትና መገንባት እንደሚችሉ ያሳዩበት እንደመሆኑ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበሩት ፕሮጀክቶች ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ከዚህ የበለጠ አስደማሚ ፕሮጀክቶችን እንደሚገነቡ ይጠበቃል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቷን ከማሳደግ አኳያ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም፡፡

እስካሁን ድረስ በአብዛኛው የገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ትኩረታቸው በከተማ ገፅታ ግንባታና፣ በሕዝብ መዝናኛና በቱሪዝም ገቢ ማመንጨት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን እስከቻሉ ድረስ በእንዲህ አይነቱ የፕሮጀከት አካሄድ መሠረት ፕሮጀክቶቹን ሥራ ላይ በማዋል በሌሎችም ዘርፎች ላይ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡

ስለዚህ በተለይ በመአድን ዘርፍ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአሳ ሀብት ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ወተትና በሌሎችም የግብርና ዘርፎች ላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ባለሀብቶችን በማስተባበር የሀገር ኢኮኖሚ የሚቀይሩ ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል፡፡ ለዚህ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የጀመሩትን ፕሮጀክት መነሻ በማድረግና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በነዚህ ዘርፎች ላይ በመቅረፅ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል፡፡

ከገበታ ለሸገርና ለሀገር ፕሮጀክቶች ተሞክሮ በመውሰድ ክልሎች ሕዝባቸውንና ባለሀብቶቻቸውን በማስተባበር በክልላቸው ያለው የተፈጥሮ ፀጋ ወደ ኢኮኖሚያዊ በረከት መቀየር ይችላሉ፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በማእድንም፣ በኢንዱስትሪም፣ በግብርናም ያሉ ፀጋዎችን በእንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶች መቀየር ይችላሉ፡፡ ለዚህ ታዲያ የየክልሎቹ አመራሮች ቁርጠኝነትና የአመራር ጥበብ ወሳኝ ይሆናል፡፡

‹‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋምና›› ነው ነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሳቸው ተነሳሽነት ከኢትዮጵያ ከተማ ሸገር ብለው የጀመሩት ፕሮጀክት ዛሬ ላይ አድጎ ወደ ሀገርና ትውልድ ተሸጋግሯል፡፡ ስለዚህ በየደረጃው ያሉ የክልልም የሆነ የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ባለሀብቶችና መላው ኢትዮጵያውያን ተባብረው አዳዲስ የፕሮጀክት ሃሳቦችን በማመንጨት የሀገራቸውን ኢኮኖሚ የማሳደግ ድርሻ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜው ነገ ሳይሆን አሁን ነው!!

ሙዘይን ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You